>

 የመከላከያ ሰራዊቱ  ወደ ትግራይ ክልል  እንዳይገባ ከመንግስት ውሳኔ ተላለፈ... (ኢፕድ)

 የመከላከያ ሰራዊቱ  ወደ ትግራይ ክልል  እንዳይገባ ከመንግስት ውሳኔ ተላለፈ…
ኢፕድ

ለዘመቻ ህብረ-ብሄራዊ ግዳጅ የተሰጠው የመከላከያ ሰራዊት ባለበት ስፍራ ረግቶ እንዲቆይ ከመንግስት ትዕዛዝ ተላለፈ። 
መንግስት ይሄንን ውሳኔ ያስተላለፈው ካለፈው ስህተት ለመማር፤ከሽብር ቡድኑ ሴራ ራሱን ለመጠበቅ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ከአሸባሪዎች ነፃ ያወጣቸውን ቦታዎች ይዞ እንዲፀና መወሰኑን መንግሥት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የመጀመሪያው ምዕራፍ በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
በዚህም አሸባሪው ኃይል ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊት በአማራ እና አፋር አካባቢዎች ወራሪውን ኃይል በማፅዳት አሁን የያዘውን አካባቢዎች ይዞ እንዲቆይ መንግሥት መወሰኑን ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
መንግሥት ለዚህ ውሳኔ የደረሰው በተለያዩ ምክንያቶች እንደሆነ ነው ያወሱት።
በዚህም ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ያጋጠመውን ችግር ታሳቢ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አንስተዋል።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ሊወጣ ሲል ሴረኞች ሕፃናትን መንገድ ላይ ማስተኛታቸውን፣ እንዲሁም እናቶች እና አረጋውያን ሠራዊቱ እንዳይወጣ ነጠላ አንጥፈው ሲለምኑ እንደነበር ተናግረዋል።
ነገር ግን በተቀነባበረ ሴራ በሰሜን ዕዝ ላይ አፀያፊ ድርጊት ሲፈፀም እነዚህ የትግራይ እናቶች እና አባቶች ድርጊቱን ከማውገዝ ዝምታን እንደመረጡ ገልጸዋል።
በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ መንግሥት ወደ ሕግ ማስከበር ግዴታ ሲገባ በትግራይ ክልል መጀመሪያ አካባቢ ትብብር ቢታይም በኋላ ላይ ሠራዊቱን ከኋላ የመውጋት እርምጃዎች መፈፀማቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ክስተት ዳግም እንዳይከሰት ጥንቃቄ መደረጉን ነው የገለጹት።
ሠራዊቱ ባለበት እንዲፀና ከተደረገበት ሌላኛው ምክንያት መንግሥት በሽብር ቡድኑ ሴራ ላለመጠመድ በመወሰኑ እንደሆነ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የተገደሉበትን በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱን አስከሬኖች ወስዶ በጅምላ በመቅበር በመንግሥት ላይ ለማላከክ የተዘጋጀ መሆኑን መረጃ እንዳለ ገልጸዋል።
በዚህም የተለመዱ ፍርደ ገምድል ውሳኔዎች ሀገራችን ላይ እንዲወሰኑ የታሰበ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁንም ቢሆን የሀገር ግዛት አንድነትን እና ሰላምን ስጋት ላይ የሚጥሉ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ መከላከያ ሠራዊቱ ለግዳጅ የሚሰማራ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታወቀዋል።
በሌላ በኩል በተለያዩ ጊዜያት የሽብር ጥቃቶችን እየፈፀመ ባለው አሸባሪው ሸኔ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
Filed in: Amharic