>

ዓይኑን በጨው ያጠበው ትሕነግ (ነስረዲን ኑሩ)

ዓይኑን በጨው ያጠበው ትሕነግ
ነስረዲን ኑሩ

መቼም አሸባሪው እና ወራሪው ትሕነግ በአስራ አንደኛው ሰዓት ላይም ሆኖ እያሰማን ያለው ጉድ እንኳንስ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ለምድር ራሱ እንግዳ ክስተት ነው።
ይህ ቡድን ለማሰብ እንኳን የሚከብዱ ግፎችን ክቡር በሆነው የሰው ልጅ ላይ ፈጽሟል፣ ከታላላቅ ፋብሪካዎች አንስቶ እስከ ኩሽና ሊጥ ዘርፏል፣ ከእንቦቀቅላ ህጻናት እስከ መነኩሴ ደፍሯል፣ ቤተክርስቲያናትን አውድሟል ቅዱስ ቁርአን አቃጥሏል… ወዘተ።
በዚህ ሰይጣናዊ ተግባሩ የሰው ልጅ በዚህ ልክ ክፉ ሊሆን እንደሚችል ለዓለም አሳይቶም ተአምር አስብሏል።
የዚህ አሸባሪ ቡድን ሌላኛው መገለጫ ቅጥፈት ሲሆን ከአረመኔነት ስብዕናው ባልተናነሰ በውሸት የሚስተካከለውን ማግኘት ይከብዳል።
በአንድ ወቅት የመከላከያ ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀኔራል አበባው ታደሰ አሸባሪ ቡድኑ ሞቶም ቢሆን መዋሸቱን አያቆምም ማለታቸው ምን ያህል የቡድኑን ስሪት እና ባህሪይ ጠንቅቀው እንደሚያውቁት በተለይ ሰሞናዊ መግለጫዎቹ አረጋግጠዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተመራው ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የተደቆሰው አሸባሪው ትሕነግ፤ በወረራ ከሰፈረባቸው የአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎች ተቀጥቅጦና ተጠራርጎ እየወጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቤተመንግሥታቸው ወጥተው ከግንባር የተገኙት እና ዘመቻውን የመሩት ወራሪ ቡድኑን ከወረራቸው አካባቢዎች ጠራርጎ ለማስወጣት ብቻ ሳይሆን ትሕነግ ዳግም ለኢትዮጵያ ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ መገኘቱን ለማረጋገጥ ጭምር ነው፡፡
ይህ ዘመቻ እቅድ ተነድፎለት፣ ግብ ተቀምጦለት፣ ለእቅዱ ስኬት የሰው ኃይልና አስፈላጊው ሎጀስቲክስ ተመድቦለት የተገባበት እንደመሆኑ የተመዘገበውም ድል ተጠባቂ ነበር፡፡
ምክንያቱም በሙሉ አቅሙ ከተንቀሳቀሰው የኢትዮጵያዊን ጥምር የፀጥታ ኃይል ፊት ሊቆም እና ሊገዳደር የሚችል ኃይል እንደሌለ አይደለም ወንበዴው ትሕነግ ዓለምም ያውቀዋል፡፡
በዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የተደቆሰው ትሕነግ ሽንፈቱን ለመደበቅ፤ ‹ያደረግነው ስልታዊ ማፈግፈግ ነው፤ በአዲስ መልክ ጠላትን እንደቁሰዋለን› ሲል ተከታዮቹን አጭበርብሯል፡፡
እየገፋ የሚመጣን ነፍሰጡርነት መደበቅ እንደማይቻለው ሁሉ ቀናት ውለው ሲያድሩና የሸብር ቡድኑ የበለጠ እየተቀጠቀጠ ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮ ሲሆን አይኑን በጨው ያጠበው ትሕነግ፤ ‹ጦሬን ከአማራና አፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ወጥቶ ወደትግራይ እንዲገባ አዝዣለሁ› በማለት አልተሸነፍኩም ሊለን ዛሬም እየጣረ ነው፡፡
ስልታዊ ማፈግፈግ በማድረግ በአዲስ ጥቃት ልመጣ ነው ብሎ የትግራይን እናቶች ጥያቄ ሊያፍን የሞከረው የሽብር ቡድኑ፤ አሁን ላይ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ አጋሬ ለሚላቸው አካላት በድርድር ስም የአድኑኝ ተማፅኖውን እያቀረበ ነው፡፡
ቅጥፈት የማያልቅበት ትሕነግ ፉከራና ቀረርቶውን ዘንግቶ ባለፉት ጥቂት ቀናት አሜሪካን ጨምሮ አውሮፓዊያን ወዳጆቼ በጠየቁኝ መሰረት ለሰላምና ድርድር ስል ከአፋርና አማራ ክልሎች ለቅቄ ወጥቻለሁ በማለት ነው አሁንም አልተሸነፍኩም እያለ ያለው፡፡
ሆኖም ይህ እስከመቼ ያዛልቀዋል?፤ ‹ካሸነፍን ልጆቻችን የት አሉ?› ማለት ለጀመሩት የትግራይ እናቶችስ ልጆቻቸውን ከወዴት ወልዶ ሊያሳቅፋቸው ይችላል? የሚለው ነገ ከነገወዲያ የሚታይ ነው፡፡
ነጫጮቹ ትሕነጎች ማርቲን ፕላውት፣ ጄትል ትሮንቮል፣ ራሺድ አብዲና መሰሎቻቸው እንዲሁም ግዙፎቹ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጥብቅና የቆሙለትን የሽብር ቡድን የሚያድነው ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ካረጋገጡ በኋላ እንኳን ከመዋሸት አልቦዘኑም።
አሸባሪው፣ ወራሪው፣ ጅምላጨራሹ፣ አስገድዶ ደፋሪው፣ ዘራፊው፣ አውዳሚውና ጉግ ማንጉጉ ቡድን ተቀጥቅጦ፣ ተረግጦና ተሰብሮ ሳይሆን ለሰላምና ድርድር ካለው ፍላጎት ከወረራቸው አካባቢዎች እንደለቀቀ ዛሬም ሊሰብኩን እየደከሙ ነው።
ኢትዮጵያን በማፍረስ ዘመቻ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃኑን ክንፍ እየመሩ የሚገኙት ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ ሮይተርስ፣ ዘ ዋሺንግተን ፖስት እና ሌሎችም ይህንን የተለመደ የትሕነግ ቅጥፈት ሲያስተጋቡ ማድመጥ ምንኛ አሳፋሪ ነው?
በደረሰብን ሞት፣ ውድመት እና ጥፋት ሁሉ እጁን በረጂሙ ያስገባው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፤ በቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ በኩል በሰጠው መግለጫ ያረጋገጠው ነገር ቢኖር ከትሕነግ ጋር ፍቅር እስከ መቃብር መባባላቸውን ነው፡፡
መስሪያ ቤቱ ትሕነግ የኢትዮጵያዊያንን ዱላ መቋቋም አቅቶት አብዛኛው ኃይሉ ሙትና ቁስለኛ ሲሆን ቀላል የማይባለው ደግሞ የመንግሥትን ጥሪ ተከትሎ እጅ መስጠቱን የማያውቅ ይመስል፤ ‘ወዳጄ ትሕነግ ሆይ ለሰላም እና ድርድር ስትል መልቀቅህ ለሰላም ያለህን ቁርጠኝነት ያመላክታል’ ሲል የጋራ ሽንፈታቸውን ሐዘን ሊውጠው ተገዷል፡፡
በዚህም በርካታ የሰላምና ድርድር ልመናን ገፍቶ ጦርነት የከፈተው፣ ከወር በፊትም ‘ጦርነቱ አልቋል ከማን ጋር ነው የምንደራደረው‘ በማለት እብሪቱን ሲተፋ የነበረው ትሕነግና መሪው ደብረፂዮን አሁን ላይ በድርድር ስም ሊያመልጡ ሲጥሩ እየተመለከትን ነው፡፡
‘ለቅቄ ወጣሁ‘ የሚለው ትሕሕነግም ሆነ ይህን የሚያስተጋቡት የገደል ማሚቶዎች፤ የትሕነግ ኃይል በየት በኩል እንደወጣ፣ በምን ያህል ኮንቮይ ኃይልና ሎጀስቲክስ ጭኖ እንደወጣ የሚሰጡት የጽሑፍም ሆነ የምስል መረጃ ግን እስካሁን የለም፡፡ ምክንያቱም ለቅቆ ሳይሆን አልቆ ትራፊው ስለፈረጠጠ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የትሕነግ ተከፋይ የሞት ነጋዴዎች ረብጣ ዶላራቸው አይቋረጥባቸው እንጂ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ እየቀጠፉ ከፋያቸውን እስከ መቃብሩ መሸኘታቸው የሚጠበቅ ነው።
ከቀናት በፊት 360 ዲግሪ የተከበው እና የዘረፈውን ንብረት ቀርቶ ራሱን ይዞ መውጣት እንኳን በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ የገባው ዘራፊው ቡድን፤ በእውር ድንብር ወደ ላሊበላ ቢገባ ‘ቲዲኤፍ ዳግም ላሊበላን ተቆጣጠረ’ በሚል ርዕስ የፊት ገጾቻቸውን ያደመቁ የፅንፈኛ ምዕራባዊያኑ መገናኛ ብዙኃን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ላሊበላ ተገኝተው የገና በዓል በታሪካዊው ላሊበላ እንደሚከበር ሲያረጋግጡ ምነው ድምጻቸው ጠፋሳ?
‘የአሸባሪው ትሕነግ ግብአተ መሬት ተፈጽሞ ሳናይና ተዝካሩን ሳንበላ የጀመርነውን ቅጥፈትማ አናቆምም‘ ያሉ የሚመስሉት ሮይተርስ እና መሰሎቹ የላሊበላውን ጉዳይ ችላ ብለው ስለ ስልታዊ ማፈግፈግ፣ ስለ ሰላምና ድርድር እየደሰኮሩ ነው።
የሽብር ቡድኑ አሁን ላይ ለውጭዎቹ የሚያቀርበው ተማፅኖው ሁሉ ድርድር የሚል ይሁን እንጂ፤ በትግርኛ በሚያወጣው መግለጫ ዛሬም ‘ተነስ‘ እያለ ለተሸነፈው ጦርነት ዳግም ወጣቱን ለመማገድ እየቀሰቀሰ ነው፡፡
ትሕነግ ድርድር የሚለው የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ወደትግራይ እንዳይገቡ የሚል ስሌትን ይዞ ነው፡፡
በጦርነቱ የተገደሉበትን ታጣቂዎች አስከሬን ይዞ ወደ ትግራይ ክልል በመግባት ላይም ሲሆን፤ ዓላማው በከፍተኛ ግስጋሴ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይል ወደ ክልሉ ቢገባ፤ ‘መንግሥት ንፁሃንን እየገደለ ነው‘ በሚል በአስከሬን ሊነግድ እየተዘጋጀም ነው፡፡
ለዚህ ግን ምላሹ አጭር ነው፡፡ የግዛት አንድነትና ሉኣላዊነትን የመጠበቁ ኃላፊነት የኢትዮጵያ መንግሥት በመሆኑ ጦሩን በየትኛውም ቦታ ሊያስገባና ሊያሰፍር፣ የሽብር ቡድኑ ዳግም ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ሊያጠፋው ሙሉ መብት አለው፡፡
ይህን ሃቅ ደግሞ ታኅሣሥ 12 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ለሚኖሩ የተለያዩ አኅጉራት ዲፕሎማቶች ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን ግልፅ አድርገዋል፡፡
Filed in: Amharic