>

"እኒህ ሰዎች ከራሳቸውም፣ ከአገርም ፣ ከሕዝብም የተጣሉ ናቸው...!!!" (አቡነ አትናቲዮስ)

“እኒህ ሰዎች ከራሳቸውም፣ ከአገርም ፣ ከሕዝብም የተጣሉ ናቸው…!!!”

 

አቡነ አትናቲዮስ


*….  “እህቶቻችሁን መድፈር እንስሳዊ ጠባይ ነው፤ ሀብት መዝረፍ ውንብድና ነው፤ ቤት እያንኳኩ የሰው ገንዘብ መዝረፍ ሌብነት ነው፤ ይሄ ሁሉ የክርስቲያን ጠባይ አይደለም፤ የሙስሊሙም ጠባይ አይደለም!

አባትነት ልጅን አንጾ ለቁምነገር ማብቃት ብቻ ሳይሆን፤ ስለ ልጅ ራስን አሳልፎ መስጠት ነው። በሃይማኖት ደረጃ ሲሆን ደግሞ ከዚህ ከፍ ያለ ኃላፊነትን መወጣት ይጠይቃል። ምዕመናንን ከጥፋት መንገድ መክሮ፣ አስተምሮና ገስጾ ከመመለስ በዘለለ፤ ምዕመናንን ሊጎዳ ከሚችል ማናቸውም ነገር ከፊት ቀድሞ መከላከልን፤ ስለ ሕዝባቸው ሲሉ ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል። በዚህ ረገድ የአሸባሪው ሕወሓት ወራሪ ኃይል ወደ አማራ ክልል ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ ከገባ ጀምሮ በርካታ ንጹሃንን ሲጨፈጭፍ፤ ቤተ እምነቶችን ሲያወድምና አገልጋዮችን ጭምር በግፍ ሲገድል ሰምተናል፤ ተመልክተናልም።

ይህን ሁነት ከፊት ሆነው የተጋፈጡ፤ ስለ ሕዝባቸውና ሃይማኖታቸው ከፊት ቀድመው የታገሉ አባቶችንም አሳይቶናል። ከእነዚህ አባቶች መካከል ደግሞ የደቡብ ወሎ ሃገረስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ አትናቴዎስ አንዱ ናቸው። አቡነ አትናቴዎስ፣ ደሴ በአሸባሪው ቡድን ስትያዝ ለቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አዲስ አበባ ነበሩ። ሆኖም ደሴ መያዟን ሲሰሙ ሕዝባቸውን ትተው ስብሰባ ላይ መቀመጥ፤ አዲስ አበባ መቆየት አልተቻላቸውም። አዕምሯቸውም ከህዝባቸው ጎን ሆነው እንዲያጽናኑ አዘዛቸው እና አደረጉት።

አቡነ አትናቴዎስ ስለጉዳዩ እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ፤ እነዚህ ኃይሎች ወደ ደሴ መቅረባቸውን ስሰማ አዲስ አበባ ለሲኖዶስ ስብሰባ ነበርኩ። ሆኖም አመጣጣቸው ሰላምን ያዘለ አለመሆኑን፣ ያገኙትን ሁሉ ዝም ብለው የሚያጠፉና የሚያበላሹ መሆኑን ሰማሁ። ከዚያ የተነሳ ወደ ደሴ ለመመለስ አሰብኩኝ። በህመሜ ምክንያት ቀደም ሲል ከደሴ ወደ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባም ወደ ደሴ የምመላለሰው በአውሮፕላን ነበር። በዛን ሰዓት ግን አውሮፕላን ቢጠየቅ አልተገኘም። ጉዞ ስጀምር ያሰብኩት በየመንገዱ እያረፍኩ፣ እየቆየሁ እመጣለሁ ነበር። እግዚአብሔር ስለፈቀደልኝ ደሴ በአንድ ቀን ገብቼ አደርኩ።

ምንም እንኳን ከህመሜ አኳያ የምፈልገውን ያህል ተዘዋውሬ ምዕመናንን ማጽናናት ባልችልም፤ መምጣቴ ለምዕመናን ብዙ እረፍት እንደሆናቸው አምኛለሁ። እዚህ ስመጣ ብዙዎቹ ደስ አላቸው፤ ብዙዎቹም ተጽናኑ። የተባሉት ሰዎችም አመጣጣቸው ሰላምን ያዘለ አልነበረም። እንደሰማሁት የመጡት ለበቀል ነው። ደግነቱ አገሪቱን እንደፈለጉ ብድግ አድርገው ለመውሰድ አልቻሉም እንጂ፤ አገሪቱን እንደ እቃ አንስተው መውሰድ ቢችሉ ኖሮ ወደኋላ አይሉም ነበር።

እኔ እንደመጣሁም አሉ የሚባሉ ባለስልጣኖቻቸውን አስጠርቼ እኔጋ መጥተው አነጋገርኳቸው። ‹‹እናንተ የክርስቲያን ልጆች ናችሁ፤ ክርስቲያኖች ናችሁ፤ ነገር ግን እንደሰማሁት እህቶቻችሁን ትደፍራላችሁ፣ ይሄ የእንስሳ ጠባይ ነው፤ የሰው ጠባይ አይደለም። ሁለተኛም፣ የድርጅቶችን ሃብት እየዘረፋችሁ ትወስዳላችሁ፣ ይሄም ውንብድና ነው። በየመንደር እየሄዳችሁም እያንኳኳችሁ ገንዘብ ትወስዳላችሁ፤ ይሄ ሌብነት ነው። እንዲህ ያለው ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋራ ያጣላችኋል። ውጤታችሁም ሊያምር አይችልም። ስለዚህ ልታውቁት ይገባል። እንዲህ አይነት ያለ ነገር ሁሉ ተገቢ አይደለም፤ እናም የሰው ሀብት አትዝረፉ፣ አትውሰዱ፣ የወሰዳችሁትም ካለ መልሱ፤” ብዬ አስገነዘብኩ።

ከዚህ ባለፈም የተቸገሩትን መርዳት የቤተክርስቲያናችን ዓላማዋ ነው። ቤተክርስቲያን መስራት ከሚገባት አንደኛው የተቸገሩትን መርዳት ነው። በወቅቱ አብዛኛው ሰዎቻችን ደግሞ የተቸገሩት በሃብት ሳይሆን በሃሳብ ነበር። ሃሳቡ በራሱ ያስጨንቃቸው ነበርና አይዟችሁ፣ ተጽናኑ፣ ይህ አይነት ችግር ጊዜያዊ ነው፣ ጊዜያዊ ነገር ካለፈ በኋላ ሊታሰብ ይችላል፣ በጊዜያዊ ነገር አትቸገሩ አይዟችሁ፣ ተጽናኑ በርቱ እያልኩኝ ኮሚቴም አቋቁመን ለማንኛውም ነገር ሁሉ የሚሰሩ ኮሚቴዎች መርጠን አዘጋጅተን ይሰሩ ነበር።

እኔ ጤንነቴም ያን ያህል ስለሆነ አልፎ አልፎ በመካከላቸው እየተገኘሁ መመሪያና ምክር ለሁሉም እሰጥ ነበር። ይህን የማደርገው እስላምና ክርስቲያን ለይቼ አይደለም። በእኔ ዘንድ እንዲህ አይነት ነገርም የለም። ምክንያቱም ሁሉም ወገኖቼ ናቸው። እናም የምችለውን ያህል ሁሉንም አጽናና ነበር። የገቡትንም ኃይሎች ቢሆን እዚህ አካባቢ በነበሩበት ወቅት እኔ እቆጣቸው ነበር። ይሄን አትስሩ፣ ይሄን አታድርጉ፤ እላቸው ነበር። ነገር ግን ስሰድባቸውና ስገስጻቸው ቆይቼ እሺ ብለው ጉልበቴን ስመው ከሄዱ በኋላ ሰሩ የሚባለው ነገር ስሰማ በጣም የሚያሳዝን ነው።

በመሆኑም “እህቶቻችሁን መድፈር እንስሳዊ ጠባይ ነው፤ ሀብት መዝረፍ ውንብድና ነው፤ ቤት እያንኳኩ የሰው ገንዘብ መዝረፍ ሌብነት ነው፤ ይሄ ሁሉ የክርስቲያን ጠባይ አይደለም፤ ከዚህ ሁሉ መቆጠብ አለባችሁ። አመጣጣችሁ የምንፈልገው መንግሥትን ነው የሚል ቢሆንም፤ በሥራ ስትገልጹ ግን በጠቅላላ ህዝቡን ነው፤ ቤተክርስቲያንን ነው፤ መስጂድን ነው፤ ቤተክርስቲያንና መስጂድ ደግሞ ልዩነት የላቸውም፤ ልዩነታቸው በስም ነው። እውነት ነው ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ማደሪያ ናት፤ በቤተክርስቲያን የሚመለክ እግዚአብሔር ነው፤ በመስጂድም የሚመለክ አላህ የሚባለው አምላክ ነው፤ ስለዚህ ሁሉም የእግዚአብሔር ማደሪያ ስለሆነ ወደ እነሱ የምትዘረጉትን እጃችሁን ሰብስቡ፤” ነው ስላቸው የነበረው።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ሃሳባቸውና ስራቸው ይለያያል። በሃሳባቸው ቤተክርስቲያንን የሚወድዱ ክርስቲያኖች መሆናቸውን በቃል ይገልጻሉ። ተግባራቸው ግን እንደዚህ አይደለም። ሁሉን ሲዘርፉና ሲመቱ ነው የሚታዩት። አብያተ ክርስቲያናትን አፍርሰዋል። ለምሳሌ፣ ጨጨሆ መድሃኒዓለም የሆነው ይታወቃል፤ ሌሎች በርካታ ቤተክርስቲያኖችን አፍርሰዋል፤ መትተዋል። በመሆኑም አመጣጣቸው በጠቅላላ አገር ባዶ አድርጎ ለመሄድ ነው።

እነሱ የተጣሉት ከእግዚአብሔር ብቻ አይደለም፤ ከራሳቸውም ጭምር ነው። ባዶ እያደረጉ የመጡት የራሳቸውን አገርም ራሳቸውንም ነው። እነዚህ ሰዎች ዓላማቸው ምን እንደሆነም አይታወቅም። ከሁሉም ጋራ ነው የተጣሉት። ከራሳቸውም ጋር፣ ከአገርም ጋር፣ ከሕዝብም ጋር የተጣሉ ናቸው። በጠቅላላው እነዚህ ሰዎች ሃሳባቸው እና ሥራቸው፤ አነጋገራቸው እና ሥራቸው የተጣላ ነው፤ ግንኙነት የለውም፤ ሲሉ አስረድተውናል።

ወንድወሰን ሽመልስ

Filed in: Amharic