>

ወያኔ ትግሬ በኢትዮጵያ ምድር ህልው ሆኖ መኖሩ ላገር አንድነትና  ለሕዝብ ደኅንነት ሥጋት አይደለም እያላችሁን ነው? (ይኄይስ እውነቱ)

ወያኔ ትግሬ በኢትዮጵያ ምድር ህልው ሆኖ መኖሩ በራሱ ላገር አንድነትና 

ለሕዝብ ደኅንነት ሥጋት አይደለም እያላችሁን ነው?

ከይኄይስ እውነቱ


የኢትዮጵያን መንበረ መንግሥት በታሪክ አጋጣሚ፣ በጉልበትና ሸፍጥ የያዘው ኦነጋዊው ኦሕዴድ ባወጣው መግለጫ ‹‹…ሕወሓት የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነትን አለማስጋቱ እስኪረጋገጥ ድረስ የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር ‹አስፈላጊ› ያለዉን እርምጃ መውሰዱን አያቋርጥም። ›› ይለናል፡፡ ይህንን አባባል በግልባጩ ስንወስደው ሥጋት ካልሆነ ግን ቢኖር ችግር የለብንም የሚል አንደምታ እንዳለው አስተዋይ ሰው ይረዳዋል፡፡ ወያኔ ትግሬ/ሕወሓት ኢሕአዴግ የተባለው የምውታን ‹ሸንጎ› ተሰባስቦ ሽብርተኛ ከመባሉ በርካታ ዓመታት በፊት ዓለም ይህንን ሰይጣናዊ ድርጅት በሽብርተኞች መዝገብ ውስጥ እንዳሠፈረው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ሰይጣናዊውን ዓለም የሚመሩት ምዕራባውያኑ ለጥቅማቸው ሲሉ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንደሚያደርጉ ደጋግመው ነግረውናልና ዛሬም ከዚህ አጋንንታዊ ኃይል ጋር ባንድነት እጃቸውን በኢትዮጵያ ላይ አንሥተዋል፡፡ ፍጥረታት ሁሉ የሚታዘዙለት÷ በቀል የኔ ነው ያለና ብድራትን የሚከፍል እግዚአብሔር አምላክ በልዩ ልዩ መቅሰፍት እየጎበኛቸው ነው፡፡ ይህም የምጡ መጀመሪያ እንጂ ገና አልተነካም፡፡ 

በፍጹም ጥላቻና አረመኔነት የአገርን ህልውናና አንድነት የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማናጋት የተደራጀ አሸባሪ ቡድን አይደለም ከኢትዮጵያ ምድር ከዓለም ሁሉ መጥፋት ያለበት መሆኑ ከቶውኑ ጥያቄ ውስጥ መግባት ይኖርበታል? ወይስ ሌላ ዙር ጥፋት እስኪፈጽም ይጠበቃል? አሁንም የፖለቲካ ቊማር ታሳቢ ተደርጎ ከሆነ የአማራው ሕዝብ ፍዳው ገና አላበቃም ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በቅድሚያ አጠገቡ ያለውን በወያኔው ብአዴን ላይ ይወቅበት፡፡ ሥልጣን ላይ ያለውን ተረኛ አካልም ማንነቱን በሚገባ ተረድቶ አካሄዱን በጥንቃቄ ይከታተል፤ከሁሉም በላይ ደግሞ ራሱን በኅቡም ሆነ በገሀድ አደራጅቶ በተጠንቀቅ መገኘት ይኖርበታል፡፡ የአውራጃና የመንደርተኝነት ነፋስ ካለስገባ ለራሱ ህልውና ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ምክንያተ ድኂን የሚሆን ኃይል ከዛ አካባቢና ሕዝብ ሳይገኝ አይቀርም፡፡

ደጋግሜ እንደገለጽሁት ባላፉት ሦስት ዓመት ተኩል ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ቢኖራት ኖሮ ከመነሻውም አገርና ሕዝብ ዐውዳሚ ጦርነት ውስጥ ባልገባን ነበር፡፡ የግድ ቢሆን እንኳ ብቃት ባለው ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራር ባነሰ መሥዋዕትነትና ንብረት ውድመት ባጭር ጊዜ ማጠናቀቅ የሚቻልበት ዕድል ነበር፡፡ ባለመፈለጉም ጆሮን ጭው የሚያደርግ የወገንን ዘግናኝ እልቂት ለመታዘብ በቃን፡፡ ጥንትም ዛሬም ብሔራዊ ማንነቱ (ኢትዮጵያዊነቱ) ከደሙ ጋር የተዋሐደው የአማራ ሕዝብ ለወያኔ ብቻ ሳይሆን ለመንፈስ ልጁ ለኦሕዴድም ደመኛ ጠላቱ በመሆኑ እንደ ገና ዳቦ በሁለት ወገን እሳት ለኩሰውበት ሀገር-አልባ ተቅበዝባዥ እንዲሆን አሁንም በብርቱ እየሠሩ ነው፡፡ ጥፋቱ የተደገሰለት በብዙ ግንባር ነው፡፡ አረመኔውና ፈሪው ኦሕዴድ (ኦነግ) በጎጃም መተከል፣ በወለጋና ወያኔ ‹ኦሮሚያ› ብሎ በፈጠረው ግዛት ውስጥ ሕፃናትን፣ ሴቶችን እና አረጋውያንን በመጨፍጨፍና በገፍ በማፈናቀል፤ ወያኔ ትግሬ አማራ የተባለን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት ሌት ተቀን በመሥራት፤ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለሙ ሁሉ ማፈሪያ የሆነው (እናቶቻችን ምነው ውኃ ሆኖ በቀረ የሚሉት ዓይነት) የወያኔው ብአዴን ደግሞ ለሁለቱም አሸባሪ ኃይሎች በድርጊትም ሆነ በዳተኝነት ዐቅሙን ሁሉ አሟጦ ዘላለማዊ አሽከርነቱን በተግባር በማስመስከር ‹ባልተቀደሰ ጋብቻ› እየሠሩ ነው፡፡ ከመነሻው ከጠላት ወያኔ ጋር ጦርነት ሲካሄድ በኦሕድዴ አገዛዝ ሙሉ ዕውቅናና እገዛ የሚመራው አሸባሪው ኦነግ አማራውን ያሳድድ ይጨፈጭፍ ነበር፡፡ አሁንም ቀጥሏል፡፡ አስቀድሞ ጠላት ‹አብቅቶለታል› ከተባለ በኋላ በስንቅና ትጥቅ እንዲሁም በሞራል ጥንካሬ እንዲደራጅ ፋታ በመስጠት ይቅር የማይባል ‹ስህተት› በመፈጸም፤ በመቀጠልም ኦነጋዊ በሆኑና ብቃት በሌላቸው ወታደራዊ አመራሮች ድክመት ወይም የታቀደ በሚመስል ዳተኝነት፤ በመጨረሻም የጠላትን ኃይል ተከታትሎ እንደማጥፋት ከነ ስንቅና ትጥቁ እንዲያፈገፍግ ማድረግ ምን ትርጕም ሊሰጠው እንደሚችል የጦር ጠበብትነትን አይጠይቅም፡፡

ኋላ ቀሩ የጐሣ ሥርዓት መጨረሻው ሕዝብን በዘር በሃይማኖት ከፋፍሎ ብሔራዊ አንድነትንና አብሮነትን ማጥፋት፤ ተሠርቶ ያደረን አገር በታትኖ ርስ በርሳቸው የሚናቆሩ እጅግ ደካማ የመንደር አገዛዞችን (balkanized ‘states’) መመሥረት መሆኑ ላይ የምንስማማ ከሆነ፤ ለእኔ በወያኔ ትግሬ እና በአዋልዱ ኦሕዴድ/ብአዴን/ደኢሕዴን/‹አጋሮች›፤ በኦነግ (ባሁኑ ጊዜ የኦሕዴድ ሌላ ገጽ ነው) እና መሠረታቸው የጐሣ ፖለቲካና ሥርዓት የሆኑ ቡድኖች መካከል መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ በተለይም በወያኔ እና ኦሕዴድ (ኦነግ) መካከል ለአማራው ሕዝብ፣ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እና የአማራው ብለው በሚያስቡት ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ባላቸው ጥላቻ ልዩነት የላቸውም፡፡ ለዚህም ነው ባንድ መጣጥፌ እንዳገለጽሁት ኢትዮጵያን የገጠማት እጅግ የከፉ አጋንንት በመሆናቸው በዘልማድ እንደሚባለው አንዱን (‹ጉዳቱ ያነሰውን›) ለመምረጥ የምንገደድበት ሁናቴ የማይሠራው፡፡ ለዚህም ነው ምርጫው የቅደም ተከተል ጉዳይ ብቻ የሚሆንብን፡፡

ሥልጣን ላይ የተቀመጠው አገዛዝ  ከጠላት ወያኔ ትግሬ ጋር ያልተቋጨውን ጦርነት በሚመለከት ቀድሞም ሆነ አሁን እምነት የሚጣልበት አይደለም፡፡ አገዛዙ ውሸትና ቅጥፈት የባሕርይው በመሆኑ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ/ሕዝብን ለማደንዘዝ ካልሆነ በቀር የሚያወጣቸው ሕጎች፣ መግለጫዎች እና የሚያሰማቸው ዲስኩሮች ሕዝብን ይታደጋሉ፤ ብሔራዊ ጥቅምን ያስጠብቃሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ የአገዛዙ ማናቸውም ርምጃዎች መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው ሥልጣኑን አስጠብቆ ባለፉት ሦስት ተኩል የሰቈቃ ዓመታት የጀመረውን ‹የኦሮሙማ ፕሮጅክቱን በእነ ሽመልስ እና አዳነች እንዲሁም በታማኝ አሽከሮቹ ብአዴን በኩል ማስፈጸም ይመስለኛል፡፡ ተግባራዊ ምስክሮቹም መሬት ላይ አፍጠው አግጠው ይታያሉና፡፡ ለአብነት ያህል ኦነግን ሽፋን አድርጎ በአማራው ሕዝብ ላይ በታቀደና በተደራጀ መልኩ የሚካሄደው ጭፍጨፋና ማፈናቀል፤ የፍትሕ አስተዳደርና ተጠያቂነት ተስፋ በሚያስቈርጥ ሁናቴ መጥፋታቸው፤ ጐሣና እምነትን መሠረት አድርጎ በሥልጣን ድልድል፣ ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር፣ በትምህርት ሥርዓቱ፣ በመንግሥት ሠራተኞች ምደባ ወዘተ. የሚታየው ዓይን ያወጣ ተረኝነት፤ በሕገ ወጥ የመሬት ቅርምትና በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የታየውና የቀጠለው ሸፍጥ፤ በተዋሕዶ ሃይማኖት ላይ – በካህነት፣ ምእመናን፣ በአድባራትና ገዳማት፣ ሀብትና ቅርሶች – የተፈጸመው መጠነ ሰፊ ጥፋት እና በአስተዳደሯ ላይ እየተፈጸመ ያለው ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት፤ ብሔራዊ መለያዎች የሆኑ ተቋማት ላይ በጀብደኝነት የተደረጉ ውሳኔዎችና ታሪካዊ ቅርሶችን ማጥፋትና ለማጥፋት የተደረጉ ሙከራዎች ወዘተ. ይጠቀሳሉ፡፡

ታዲያ ይሄ አገዛዝ ጦር የሰበቁትን ሽብርተኞቹን ወያኔ ትግሬን እና አነግን (ኦሕዴድ ኦነግ በመሆኑ ራሱን እንዴት ያጠፋል) አጥፈቶ ሰላምን ለማስፈን፣ የአገር አንድነትንና ሉዐላዊነትን ለማስከበር የሚታመንበት ይህ ነው የሚባል ያለፈ የስኬት ታሪክ ወይም ግኝት/መልካም አፈጻጸም (track record) አለው? 

ለማጠቃለል የሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ እንዲሉ ይህ የጐሣ አገዛዝ የጐሣ ሥርዓቱን ከነ ሕጋዊና አስተዳደራዊ መዋቅሩ ለመለወጥ ዝግጁነት ይቅርና ፍላጎት አለው? ከ5-6 ሺህ ዓመታት የሚገመት ታሪክ እንዳላት የሚነግርላትን ጥንታዊ አገር የማያውቁና ማወቅም የማይፈልጉ ዘረኞች በሠለጠኑባት ኢትዮጵያ ለጐሣ ሥርዓት መደላድል የፈጠረውንና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባዕድ የሆነውን የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› በመጥቀስ ትግራይ የኢትዮጵያ አካልነቷ ቀርቶ ትሂድ/ትገንጠል የሚሉ ዐላዋቂና ሰነፍ ባለሥልጣናት መኖራቸው ላገር ማፈሪያና ውርደት ነው፡፡ ‹ነፃነቷ› ባርነት ከሆነባት ኤርትራ ለመማር አቅቶን እንዲህ ከአእምሮአችን እንለይ? ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገር የባሕር በር እና ታላቁንና ታሪካዊውን የደብረ ቢዘን ገዳም ያሳጣ የእብሪተኞች ውሳኔ እንዴት ማስተዋል ተሳነን? አሁንም አንዳንድ የአእምሮ ድኩማኖች ሕዝቡን ሳይሆን መሬቱን ነው የምትፈልጉት የሚል የስንፍና ንግግር ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማንም የሚሰጠው ወይም የሚነፍገው ማንነት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መኖርን የመረጠ በውስጥም ሆነ በውጭ ያለ ወገን ሁሉ ከራስ ካሳር እስከ ራስ ዱሜራ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ከነ ሙሉ ክብሩና ኩራቱ መብቱና ግዴታው መኖር ይችላል፡፡ የአብሮነትን ጥንካሬ፣ የመከፋፈልን ድክመት ለማወቅና ዐውቀንም ካለንበት ድንቊርናና ዕብደት ወደ አእምሮ ለመመለስ ከበቂ በላይ ተሞክሮዎች አሉን፡፡

ኦሕዴዳዊው አገዛዝ ኢትዮጵያዊ ጠባይ ቢኖረው ኖሮ ገና ከጅምሩ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ዘር ማጥፋት እየፈጸመበት ያለው የአማራ ሕዝብ ያሳየውን ያልተቆጠበ ድጋፍ ስንቅ አድርጎ በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ከተፈጸመው እልቂትና ውድመት ባነሰ መሥዋዕትነት መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ይችል ነበር፡፡ እንደኔ ትሁት እምነት አንዳንዶች ሰበብ ከሚያደርጉት የአገራዊ ህልውና አደጋ ይልቅ ውኃ የሚያነሳው (በአመራሩ በኩል ያለው ሥር የሰደደ ወያኔያዊ ውርስ እንደተጠበቀ ሆኖ) በዋናነት የዓላማ አንድነት፣ የቊርጠኝነት፣ ብስለትና፣ አስተዋይነት (lack of unity of purpose, will power and wisdom) ጉድለቶች ይመስሉኛል፡፡

ስለሆነም አገዛዙ የቀደመ ስህተት ዳግም ላለመፈጸም የሚል ሰንካለ ምክንያቱን ወደ ጎን አድርጎ (ብረትን ለፈለጉት አገልግሎት የሚያውሉት በጋለበት ጊዜ ነውና) ሕዝባዊ ኃይሉን እና ሠራዊቱን አስተባብሮ ወያኔን መቅበር፣ የዘረፈውን ንብረት ሁሉ ለባለቤቱ ሕዝብ መመለስ፣ በቊጥጥር ሥር የዋሉትን እና የሚውሉትን የሲቪልም ሆኑ ወታደራዊ አመራሮች ለፍርድ ማቅርብ፣  ወያኔ ትግሬ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በዝርፊያ ያቋቋማቸውን የፓርቲ ኢኮኖሚ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በመውረስ በጦርነት ለተጎዱት ወገኖች ማቋቋሚያ እንዲውል ማድረግ (ቢያንስ አንድ ድርጅት ሽብርተኛ ከተባለ በኋላ የወንጀል ፍሬዎቹን ይዞ እንዲቈይና እንዲጠቀምበት ማድረግ በራሱ ሌላ ወንጀል ነው)፣ በትግራይ ክፍለ ሀገር ሕግና ሥርዓት እንዲመለስ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ግን ጥንቃቄ አያስፈልግም ወደሚል የተጣመመ ትርጕም መወሰድ የለበትም፡፡ አገዛዙ ‹የአገርና የሕዝብ ደኅንነት ኃይል› አለኝ ካለ ሥራው ምን ይሆን? የግለሰብን እና የኔ የሚለውን ቡድን ደኅንነትና ጥቅም ማስጠበቅ ብቻ ይሆን?

በመጨረሻም አገዛዙ ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያነት የዕርቅ፣ የድንበር፣ ወዘተ. ኮሚሽኖች እያለ የማይሠሩ አካላትን በማቋቋም አገራዊ ሀብትን ማባከን ማቆም ይኖርበታል፡፡ ማንም ሰው በራሱ ጉዳይ ዳኛ ሊሆን አይችለም የሚለውን ዓለም አቀፍ የሕግ መርህ በማስታወስ የኦሕዴድ አገዛዝ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋምም ሆነ በዓዋጁ የተዘረዘሩትን ተግባራት ለመምራትና ለማስፈጸም የሞራል ብቃት የለውም፡፡ በእውነት ኢትዮጵያዊ አጀንዳ አለኝ የሚል ከሆነ በቅድሚያ ጦርነቱን (በራሱ ኦነጎች የሚካሄደውን ጭምር) አጠናቅቆ አገራዊ ሰላም በማስፈን በጦርነቱ ሁለንተናዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን ዘላቂነት ባለው ሁናቴ ማቋቋም፤ በመቀጠልም የመከላከያ ሠራዊቱን በኢትዮጵያዊ አቋም (‹ልዩ ኃይል› የሚባለውን የየክፍለ ሀገራቱን ሕገ ወጥ ኃይል በአገራዊ አስተሳሰብና ተጨማሪ ሥልጠና በማነፅ በሕጋዊነት ወደ መከላከያ ሠራዊቱ እንዲቀላቀል በማድረግ) በማጠናከር በድንበራችን ውስጥ ሽብር እየፈጠረ የተቀመጠውን የጠላት የሱዳን ኃይል በቅድሚያ በዲፕሎማሲ ሙከራ አድርጎ ካልተሳካ በኃይል ማስወጣት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በኋላ ከሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል የሚውጣጣ ነፃና ገለልተኛ አካል የሚመራው አገራዊ ጉባኤ ጠርቶ በዚህ አካል አስተባባሪነትና በሕዝብ ተሳትፎ የሚቀረፁ አንኳር ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ የሽግግር ፍትሕ (በማድበስበስ ሳይሆን በዐደባባይ ዕርቅ/ይቅርታ/ፍርድ) በማስፈን ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል፤ ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች ደግሞ ከፖለቲካ ሸፍጥ በፀዳ ውሳኔ ሕዝብ እንዲፈታ ማድረግ ቀዳሚ ጉዳዮች እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ እነዚህ መፍትሄዎች ስንጮኽ የከረምንባቸውና አድማጭ ያጡ እንጂ አዲስ አይደሉም፡፡ ምናልባት አጥብቆ በር ከማንኳኳት ብዛት ጭንጫውን ልብ በጎ የሚያስመለክት ቅዱስ መንፈስ ከጎበኘው በሩ የሚከፈትበት ዕድል ይኖር ይሆን? በሚል አስተሳሰብ የሚደረግ ሙከራ መሆኑን አንባብያን እንድትረዱልኝ በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡

Filed in: Amharic