>
5:21 pm - Saturday July 21, 8334

የሳውዲ ስደተኞች ድምጻችንን ይሻሉ ...!!! (ነቢዩ ሲራክ)

የማለዳ ወግ…

በህገ መንግስቱ ዜጎች እኩል ናቸውን ?? ‼
* የሳውዲ ስደተኞች ግን እኩል አይታዩም‼
* ዝም አልልም ፣ ዝም አትበሉ  ‼
ነቢዩ ሲራክ


ህልውና ዘመቻው መባቻ …
==================
  የሀገር ህልው አስግቶን ፊታችን አስቸኳይ ድምጽ ልንሰጣቸው የሚገባን በሳውዲ አረቢያ ያሉ ወገኖቻችን ድምጽ ከመሆን ተቆጥበን ባጅተናል። እነሆ የሀገር ህልውና  ዘመቻው በአብዛኛው መላ ተገኝቶለታል።   ዛሬ ከሳውዲ ወህኒ የከፋ ወህኒ እስር ቤት ለወራት የሚሰቃዩ ወገኖቻች የእኛን ድምጽ ይሻሉ ።
የሳውዲ ስደተኞች ድምጻችን ይሻሉ …
========================
    ዛሬም ስለ አቅመ ደካማ ስደተኞች ፣ ሴት ህጻናት ታማሚዎች በቂ ምግብ ፣ ውሃና ህክምናን የተነፈጉ ንጹሃን ወገኖቻች እንደ ዜጋ ያገባናል። ከሁሉም በላይ የሚያመው መከራና ስቃዩ ደርሶባቸው የተመለሱትን ጨምሮ እንደኔው ለሀገርና ለወገን ቀናኢ የሆነውን ስደተኛ አሳምረው የሚያውቁት እልፍ አዕላፍ ተመላሾች ዝም ያሉበት አባዜ አልገባኝም ። ምን የሚሉት የዝምታ አዙሪት እንደሆነ ከቶ ሊገባኝ አልቻለም  🙁
የአንድ ሀገር ሁለት ዜጎች ..
==================
ወገኖቸ ፣ 1 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ወደ ሀገሩ በክብር እንዲገባ በክብር ጥሪ ቀርቦለት እየገባ ነው። በአንጻሩ 100,000 አንድ መቶ ሽህ የሚሆን በሳውዲ ወህኒ በስቃይና በሰቆቃ ላይ ይገኛል። በ200 ሁለት መቶ ሽህ በላይ ከወህኒ ውጭ ያለ ዜጋም በሰቀቀን ኑሮን ሲገፋ መብት አስከባሪ የለውም ። ይባስ ብሎ ካሳለፍነው አንድ ወር ገደማ ጀምሮ  በኢትዮ የውጭ ጉዳይ ሚር ጥብቅ ትዕዛዝ የመጓጓዣ ሰነድ “ሊሴ ፖሴ ” እንዲቆም በመደረጉ ወደ ሀገር መመለሻ ጠባቡ እስከ ዛሬ ድርግ ተዘግቶበታል 🙁 በዚህ መልኩ የውጭ ጉዳይ ሚር መ/ቤት በአንድ ሀገር መብቱ የሚከበርለትና የማይከበርለት ሁለት አይነት ዜጎች እያሳየን ነውና አዝነናል ። የረባ የመብት ጥበቃ የማያደርገው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮ የዲያስፖራ ኤጀንሲ በሳውዲ አረቢያ ወህኒ የሚሰቃዩት ስደተኞች ለመታደግና የዜጋ ክብራቸው ሲገፈፍ እየተመለከተ ከበደል ላይ በደል እየፈጸመባቸው መሆኑን ስለ ሀቅ  በድፍረት እመሰክራለሁ።
ተገፊው ባለውለታ ስደተኛ …
===================
  በሳውዲና በቀረው አረብ ሀገር የሚገኘው ስደተኛ ለሀገርና ወገኑ ባለውለታ ሆኖ ሳለ ውለታው ተረስቶ የመብት አስከባሮ እንኳ አላገኘም ። ለእናት ሀገር ጥሪ ሲቀርብለት ቀድሞ ደራሹ የዛሬው ተገፊ ለወገን ደራሽ ቀናኢ ዜጋ ነው። በስቃይ ላይ ያለው ስደተኛ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው በተገባ ነበር ። ዳሩ ግን አልሆነም። ያም ባይሆን የሳውዲ ስደተኛ እንደ ዜጋ ተቆጥሮ ወደ ሀገር ቤት መመለሻው ጠባቡን መንገድ መዘጋጋት ባላስፈለገ ነበር።
   በአንድ ሀገር የሁለት ዜጎች አያያዝ እያየን ነው። ባለ ውለታው ስደተኛ ደራሽ አጥቷል። ከወደቀበት ተዘንግቶ ሰብአዊ መብቱ ሲጣስ ደራሽ የት ነህ የሚል ተወካይ የለውም ። በአንጻሩ የአውሮፖ፣አሜሪካ እና በቀረው አለም ያለው ዲያስፖራ ወደ ሀገር ይመለስ ዘንድ ጥሪ ቀርቦለት በመመለስ ላይ ነው። ዲያስፖራው ወደ ሀገር ሲመለስ ከክፍያ ነጻ ሻንጣ ይዞ ይገባ ዘንድ መንገዱ ሁሉ የዎት ሆኖለታል። ቀይ ያማረ የስጋጃ  ምንጣፍ ለክብሩ ተነጥፎ በደመቀ አቀባበል እነሆ  እየተደረገለት ነው።በህገ መንግስቱ ሁሉም ዜጎች ዜጋ እኩል ናቸው ቢልም የሳውዲ ስደተኞች ግን እኩል ሆነው አላየናቸውም። ይህ መሰሉ አሰራር ተገቢም ፍትሃዊም አይደለም።
   በሳውዲ ወህኒና ከወህኒ ውጭ ያሉ ወደ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ሀገር መመለስ ይፈልጋሉ ።  ተገፊ ዜጎች በውጭ ጉዳይ ሚር መ/ቤት ውሃ የማያነሳ ተራ ምክንያት የተዘጋባቸው የመመለሻ በር ይከፈት ፣ ስደተኞች ኩሩ ዜጋ መሆናቸው አስበን መብታቸው ይከበር ዝም አልልም በማለት እያንዳንዳችን ድምጻችን እናሰማ ስል ሁላችሁንም እማጸናችኋለሁ ።
ጆሮ ያለው ይስማ
=============
   የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሳውዲ ላሉ ዜጎች “እየተገበርኩ ነው” በሚለው ዜጋ መር ፕሎማሲው ሁነኛ ቦታ አልሰጣቸውም ። ይህ ሊታረም ይገባል።የሳውዲ ስደተኞች የተነፈጉትን መብት ሊከበርላቸው ይገባል።  ህገ መንግስቱ ማናቸውም ዜጎች በህግ ፊት ብቻ ሳይሆን መብታቸውን በማስጠበቁ ረገድ ድጋፍ ይደረግላቸው ዘንድ በግልጽ  ይደነግጋል።በህገ መንግስቱ የተቀመጠው የዜጎች መብት በሳውዲ አረቢያ ነዋሪ በሆኑ ስደተኞች ላይ ተደጋግሞ ተጥሷል።
   በምንመራበት ህገ መንግስት ዜጎች ሁሉ እኩል ናቸው ካልን በሳውዲ ነዋሪ ስደተኞች መብት ተገፍፈዋል። ኑሮን በሰቆቃ እየገፉ ያሉ ዜጎቻችን ይዞታ ከምንጊዜውም በላይ አሳሳቢ ጉዳይ ነውና ሆኖ ዜጎች በክብር ወደ ሀገር ይመለሱ ዘንድ የተዘጋባቸው በር ይከፈት ስል ዘንድ የዜጋ ድምጼን ዛሬም አሰማለሁ ‼
አዎ ፣ ስለ ተገፊ ወገኖቸ ዝም አልልም ‼
ጀሮ ያለው ይስማ …
ታህሳስ 18 ቀን 2014 ዓም
Filed in: Amharic