>

ነገረ ዐ.ብ.ን ....!!! (ልኡል አምደጽዮን)

ነገረ ዐ.ብ.ን ....!!!

ልኡል አምደጽዮን

ይብዛም ይነስም ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) በኋላ የዐማራ ሕዝብን ለመጀመሪያ ጊዜ በዐማራነቱ ወክሎ ለመታገል የተመሰረተው የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዐ.ብ.ን) ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከታዩ ተወዳጅ፣ አነጋጋሪ፣ አስደናቂና አወዛጋቢ የፖለቲካ ማኅበራት መካከል አንዱ እንደሆነ አይካድም፡፡
ዐ.ብ.ን ‹‹ተስፋችን፣ መዳኛችን፣ ወኪላችን፣ ክፉ አይንካብን …›› ያሉት/የሚሉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላትና ደጋፊዎች (ዐማራ ያልሆኑና ማንነታቸውን በዐማራነት መግልጽ የማይፈልጉ ብዙ ሰዎች ጭምር) ያሉትን ያህል ‹‹የነገሥታቱ ስርዓት አስቀጣይ፣ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ፣ የነፍጠኞችና የትምክህተኞች ማኅበር፣ ዐይንህን ላፈር …›› ያሉት/የሚሉት ብዙ ነቃፊዎችም ያሉት ፓርቲ ነው፡፡
ፓርቲው ድጋፉንም ነቀፋውንም እያስተናገደ፣ ብዙ ከፍታዎችንና አልፎ አልፎ ደግሞ ጥቂት ዝቅታዎችንም እያሳየ፤ በ6ኛው ሀገራዊ ‹‹ምርጫ›› በመሳተፍ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛውን ድምጽ ማስመዝገብ የቻለ ተቃዋሚ ኃይል ለመሆን በቅቷል፡፡ በክልል ም/ቤትም ሆነ በፓርላማ የዐብንን ያህል መቀመጫ ያገኘ ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም፡፡
ፓርቲው በበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የወሰዳቸው አቋሞች ቀደም ሲል ከነቀፉት አካላት ጭምር ክብር አስገኝተውለታል፤‹‹ዐማራ እኮ ምንም ዓይነት ተዐምር ቢፈጠር ኢትዮጵያን አይረሳም›› አስብለዋል፡፡
ብዙ አስደናቂ አቋሞችንና አፈፃፀሞችን እያሳየ የመጣው ዐ.ብ.ን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድክመት ተስተውሎበታል፡፡ በእርግጥ መድከምና መበርታት በየትኛውም መስክ ያሉ ተፈጥሯዊ ነገሮች ናቸው፡፡ የዐማራ ሕዝብ ከዐ.ብ.ን ብዙ ነገር በሚጠብቅበት በዚህ ወቅት ፓርቲው ተዳክሞ መታየቱ ጭንቀትን እንደሚፈጥርም ግልፅ ነው፡፡ ስለሆነም ፓርቲው ድክመቶቹን በፍጥነትና በብስለት አስተካክሎ የሕልውና አደጋን ጨምሮ በርካታ ችግሮች የተጋረጡበትን የዐማራን ሕዝብ መምራት ለነገ ሊለው የማይገባው አንገብጋቢ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ሰሞንኛው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ፍርሃት፣ ምክርና ተቃውሞም ከዚሁ የመነጨ ነው፡፡
በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ለአደባባይ የማይበቁ አንዳንድ ምስጢሮች እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡ በግልጽ የታዩና ፓርቲውን አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች ግን ዝም ተብለው ሊታለፉ አይችሉም፡፡ ከዚህ አንፃር ዐ.ብ.ን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠሙት ችግሮች የሰለጠነ ውይይት ተደርጎባቸው አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፓርቲው ስለዐማራ ሕዝብም ይሁን ስለሀገራዊ ጉዳዮች ምን እያሰበ እንደሆነ ማወቅ አልተቻለም፡፡ ለአብነት ያህል መንግሥት ‹‹ሰራዊቱ መቀሌ አይገባም›› ሲል እንኳ፣ ዐብን ምንም አላለም!  ቢያንስ ቢያንስ ‹‹የመንግሥት ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ሕዝባችን ግን ተደራጅቶና ታጥቆ በተጠንቀቅ እንዲቆም እናሳስባለን›› ብሎ ማሳሰብ የለበትም ነበር??? ነ በ ረ በ ት! ይህ በእውነቱ በጣም በጣም ነው የሚያሳዝነው! [በነገራችን ላይ’ የፓርቲው የፌስቡክ ገጽ ለመጨረሻ ጊዜ ጽሑፍ የተለጠፈበት ከአንድ ወር በፊት (Nov. 26) ነው፡፡ በዚህ ወቅት እኮ ሕዝቡ እንዲደራጅ፣ እንዲረዳዳ፣ እንዲዘጋጅ … በየሰዓቱ ማሳሰብና ማንቃት ነበረበት፡፡ በዚህ ጊዜ ያልተንቀሳቀሰ መቼ ሊንቀሳቀስ ነው? መግለጫ መስጠት እኮ ለአባላቱ/ለደጋፊዎቹ/ለሕዝቡ ቀላል ነገር አይደለም!] ይህ ብቻም ሳይሆን መንግሥት ወደፊት በሚወስናቸው ውሳኔዎች ላይ ፓርቲው ከዐማራ ሕዝብ ጥቅም አንፃር ምን ዓይነት አቋም እንደሚይዝ አልታወቀም፡፡
በተለጣፊነት የሚታማው ኢ.ዜ.ማ እንኳ ያለምንም ይሉኝታ/ፍርሃት ‹‹መንግሥት መከላከያ ሰራዊቱን የማያስጠቃና አደጋ ላይ የማይጥል ውሳኔ ይወስናል ብለን ብናምንም ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጅ ግን እናሳስባለን፤ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የምታገኘው ህወሓት ሲቀበር ብቻ ነው›› የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡
[በነገራችን ላይ’’ ኢዜማ የመንግሥት ሹመት ሲቀበል የተከተለው አካሄድ በአርዓያነት የሚወሰድ ነው፡፡ 1ኛ. ፓርቲው የ‹‹ሹመት እንስጣችሁ/አብረን እንስራ›› ጥያቄ ከመንግሥት ሲቀርብለት ጠቅላላ ጉባኤውን ጠርቶ ስለጉዳዩ አወያይቶ በአብላጫ ድምጽ አስወስኖ ነው ሹመቱን የተቀበለው፡፡ 2ኛ. የፓርቲው ዋና ዋና አመራሮች ሹመቱ ውስጥ ስለሌሉበት የፓርቲው ስራ እንደተለመደው እንዲቀጥል አስችሎታል … የትምህርት ሚ/ር ተደርገው የተሾሙት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የፓርቲው መሪ እንጂ ሊቀ መንበር ስላልሆኑ በኢ.ዜ.ማ አሰራር መሰረት ሹመታቸው በፓርቲው የስራ እንቅስቃሴ ላይ እክል ይፈጥራል ተብሎ አይታሰብም]
እናት ፓርቲም በሚኒስትር ደኤታ ደረጃ የተሾመች አባል አለችው፡፡ የ‹‹አብረን እንስራ›› ጥያቄ ሲቀርብለት ግን ለሹመት ያቀረበው የፓርቲውን ሊቀ መንበር ወይም ምክትሉን አይደለም፡፡ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፤እሱ እንኳ ከነጭራሹም ጥያቄውን የተቀበለው አይመስለኝም፡፡
ዐ.ብ.ን ግን የ‹‹ሹመት እንስጣችሁ/አብረን እንስራ›› ጥያቄ ከመንግሥት ሲቀርብለት ስለጉዳዩ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እንኳ አልተወያዩበትም! በፓርቲ ደረጃ ውሳኔ ማግኘት ያለበትን ጉዳይ በግለሰቦች ፍላጎትና ወሳኝነት ብቻ ማስፈፀም  ሕዝብን መናቅና መካድ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ሌላው ስህተት ፓርቲው ለሹመት ያቀረበው የፓርቲውን ዋና ስልጣን (ሊቀ መንበርነትና ም/ሊቀ መንበርነት) የያዙትን ሰዎች ነው፡፡ የብልጽግናን የስልጣን ግብዣ የተቀበሉት አመራሮች ሹመቱን ሲቀበሉ የፓርቲ ኃላፊነታቸውን ማስረከብ ነበረባቸው፡፡ ግን ያን አላደረጉም፡፡
የራሱን ፓርቲ ዋና ዋና ሰዎች ለሌላ ፓርቲ (ለብልጽግና) ዓላማ አስፈፃሚነት ያቀረበው ፓርቲ ዐ.ብ.ን ብቻ ነው፡፡ ይህ ስህተት ደግሞ ይኸው የምናየውን ድክመት ፈጠረ፡፡ ሹመት የተሰጣቸው የዐ.ብ.ን አመራሮች ከፓርቲ ኃላፊነታቸው ተነስተው ባልተሾሙት መተካት ነበረባቸው/አለባቸው፤ሹመኞቹ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ሊቀጥሉ ይችላሉ። በአጠቃላይ ዐ.ብ.ን የመንግሥትን/የብልጽግናን የ‹‹አብረን እንስራ›› ጥያቄን ሲቀበል ጥያቄውን የተቀበለበት መንገድ ትልቅ ስህተት ነበር! ይህ ደግሞ ከሌሎች ተጓዳኝ ምክንያቶች ጋር ተደምሮ ፓርቲውን ‹‹ጭራሽ የለም/ጠፋ›› እስከመባል አደረሰው፡፡ በእኔ እምነት ፓርቲው ዓላማውን የዘነጋ ሆኗል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳዯቸውና እያራመዷቸው ያሉት አቋሞችና ሃሳቦች የዐማራን ሕዝብ የሚከፋፍሉና ፓርቲውን የሚያዳክሙ ናቸው፡፡ ከዐማራዊ አደረጃጀቶች ይልቅ ክፍለ ሀገራዊና ንዑስ ክፍለ ሀገራዊ መቧደኖችን በይፋ ሲያበረታቱ መስተዋላቸው፣ ችግር ያልሆኑና ፈፅሞ ያልተፈጠሩ ነገሮችን እንደችግር በማንሳት የዐማራን ሕዝብ አንድነት አደጋ ላይ ሲጥሉ መታየታቸው እጅግ አስደንጋጭ ነው!
እዚህ ላይ ‹‹የዐ.ብ.ን አመራሮች ከ‹ወሎ ኅብረት› ሰዎች ጋር መወያየታቸው እንደነውር መቆጠር የለበትም›› በማለት ከላይ የጠቀስኳቸውን የአመራሮቹን ስህተቶች ለማደባበስ የሚሞክሩ ወገኖች አሉ፡፡ ነገሩ እንደዚያ አይደለም! (የፓርቲው ሊቀ መንበር) በለጠ ሞላ እና (ምክትል ሊቀ መንበሩ) የሱፍ ኢብራሂም ከወሎ ኅብረት ጋር መወያየት ብቻም ሳይሆን ከፈለጉ የኅብረቱ አባል የመሆን መብትም አላቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ግለሰቦች የዐ.ብ.ን ዋነኛ አመራሮች ሆነው ሳለ የዐማራን ሕዝብ አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ሃሳብ የማራመድ እንዲሁም ወሎን ከዐማራነት የሚነጥል እሳቤ የማቀንቀን በአጠቃላይ የዐ.ብ.ንን ዓላማ የዘነጋ ተግባር የመፈፀም መብት የላቸውም!!! ይህ የማይታለፍ ቀይ መስመር (RED LINE) ነው!
የዐ.ብ.ን አመራሮች መነሻቸውም መድረሻቸውም የዐማራ ሕዝብ ጥቅምና መብት መከበር መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም! በታይታ፣ በሴራ፣ በግል ዝናና በሌሎች ምክንያቶች የሚፈፅሟቸው ስህተቶች ይቅር የሚባሉ አይሆኑም፡፡ ዓላማቸውን ዘንግተው “የተለመደው ማደንዘዣ” ውስጥ ለመግባት ከፈለጉ ዐ.ብ.ንን ለ’ቀው ‹‹የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ ነን›› የሚሉ ቡድኖችን መቀላቀል ይችላሉ፡፡
ሌሎች ችግሮችም አሉ! …  
ይባስ ብሎም ‹‹ፓርቲው ችግር ውስጥ ስለገባ ማስተካከያዎችን ያድርግ›› ተብሎ ለቀረበው ተገቢ ጥያቄ አመራሮቹ የሚሰጡት ምላሽ ከጥያቄውና ከችግሩ ጋር ተያያዥነት የሌለውና ተገቢነት የጎደለው ሆኖ ታዝበናል፡፡ ‹‹የዐማራን ሕዝብ አትከፋፍሉ፣ ወደ ቀድሞ ጥንካሬያችሁ ተመለሱና ሕዝቡን ምሩት›› ለሚል ጥያቄ ‹‹የጎጃም ሕዝብ አንድ እንጀራ ሲጠይቁት ሁለት አድርጎ የሚሰጥ ቸር ሕዝብ ነው … በጎጥ እየተሴረብን ነው›› የሚል ረብ ምላሽ መስጠት ንቀት ነው!
እንደምንሰማው ከሆነ የብሔራዊ መግባባት ውይይት በቅርቡ ይጀመራል እየተባለ ነው፡፡ ውይይቱን እንደቀላል ነገር እንዳትመለከቱት፡፡ ታዲያ ዐ.ብ.ን እንዲህ ዓይነት ደካማ አቋም ውስጥ ሆኖ ሳለ ለዐማራ ሕዝብ በውይይቱ ላይ ፍላጎቶቹን በግልጽ ቀርፆ የሚያቀርብለትና የሚደራደርለት ማን ነው? መቼም ‹‹ብአዴን/የዐማራ ብልጽግና/ ዐማራን ወክሎ ይወያያል/ይደራደራል›› እንደማትሉኝ አምናለሁ!
አሁን ባለው ዐማራዊ የመደራደር አቅም ወደ ብሔራዊ መግባባት ውይይት መሄድ የዐማራ ሕዝብ በ1983 ዓ.ም ከደረሰበት መገለልና ባለፉት 30 ዓመታት ከተቀበለው መከራ የባሰ ውጤትን ያስከትላል። ሁሉም ዐማራ ይህን መዘንጋት የለበትም! ላለፉት 30 ዓመታት ‹‹ሕገ መንግሥቱ ዐማራን አይወክልም … የሀገሪቱ አስተዳደራዊ መዋቅር ፀረ-ዐማራ ነው …›› እያልን ቆይተናል፤አሁን ደግሞ እንዲህ በደከመ አቋም ወደ ድርድርና ውይይት ሄደን፣ ሌላ ቁማር ተበልተን ቀጣዮቹን ዓመታትም ‹‹ስርዓቱ ፀረ-ዐማራ ነው›› እያልን ልንቀጥል ነው??? አንቀጥልም! ምክንያቱም እያለቀሱ ለመኖር እንኳ የሚያስችለንን በሕይወት የመኖር እድሉንም ማግኘት ስለማንችል!
ዐ.ብ.ንን ለማዳከምና ለማፍረስ ከዋናው ቤት እስከ ባሕር ማዶ ድረስ የተዘረጉ ፀረ-ዐማራ የክፋት እጆች አሉ፡፡ አንዳንድ የፓርቲው አመራሮችና አባላትም የእነዚህ ክፉ እጆች ተባባሪ ከመሆን ሊታቀቡ ይገባል፤ፓርቲውም በሳልና የዐማራ ሕዝብን ያስቀደመ ማስተካከያ ማድረግ አለበት!
‹‹ፓርቲው ችግሮች በርክተውበታልና መስተካከል አለበት›› የሚል ሃሳብ ሲነሳ ስለ ጉዳዩ ምንም ሳያውቁ ‹‹የጎጥ ጨዋታ ጀመሩ፣ የዐማራ አክቲቪስቶች ተቋም ማፍረስ ልማዳቸው ነው፣ ዐ.ብ.ንን ማንም ጎጠኛ አክቲቪስት ሲያፈርሰው ዝም ብለን አንመለከትም፤ዐብንዬ ባለህበት ቀጥል … ›› ብለው የሚጮሁ ብዙ ከንቱዎችንም ታዝበናል፡፡
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ነጥብ ‹‹የፓርቲውን መስተካከል እንፈልጋልን›› የሚሉ ሰዎች የየራቸው ፍላጎቶች እንዳላቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹ የፈለጉት ‹‹የፓርቲው አመራሮች ከእኛ ሰፈር መሆን አለባቸው›› ለሚል አሳፋሪ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በግለሰቦች ላይ ግላዊ ጥላቻ ያላቸውና ከግለሰቦቹ ጋር ጸብ ውስጥ የገቡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የፀረ-ዐማራዎች (ብአዴን፣ ህወሓት፣ ኦነግ…) ተልዕኮ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ነገሩን ባለመረዳት በስሜትና በአሽቃባጭነት ዝም ብሎ የሚነጉድ ነው፡፡ ‹‹ዝም እንበል›› የሚሉትም ስህተት ናቸው፡፡ ስለተናደዱ ብቻ ‹‹ፓርቲው ሞቷል›› እያሉ በንዴት የሚናገሩ ግን ለፓርቲው የሚቆረቆሩ ሰዎችም አሉ፡፡ ሆን ብለው ‹‹ሞተ›› ብለው የሚለፈልፉ የኦነግ/ሕወሓት ተላላኪዎችም አሉ፡፡
የእኔ ፍላጎት ፓርቲው፣ በተለይ በዚህ ወቅት፣ ለሕዝቡ እጅግ በጣም ስለሚያስፈልግ አውቀውም ይሁን ባለማወቅ ስህተት እየሰሩ ያሉ ሰዎችን በማስተካከል ወደ ዓላማው እንዲመለስና ጠንክሮ እንዲቀጥል ብቻ ነው!!! ነገሩ ሳይገባችሁ ጉዳዩ የጎጥ ጨዋታ ለመሰላችሁ ሰዎች ነገሩ የጎጥ ጉዳይ ቢሆን’ማ ለዐ.ብ.ን ሊቀመንበርም ሆነ ለምክትሉ (ለበለጠና ለየሱፍ) እኔ እቀርባቸዋለሁ እኮ፡፡
 … ዐ.ብ.ን አፋጣኝ ማስተካከያዎችን ማድረግ አለበት! …
የዐማራን ጥቅም ለማስጠበቅ አስደናቂ ስራዎችን የሚያከናውነው የዐማራ ማኅበር በአሜሪካ (Amhara Association of America) አባላትን ጨምሮ በርካታ ግለሰቦች ስለዐ.ብ.ን ወቅታዊ ቁመና (ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበት) ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ አንዳንድ የፓርቲው አመራሮችም ፓርቲው ማሻሻያዎችን አድርጎ በከፍታው እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ ፓርቲውም ይህን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ማስተካከያዎችን በማድረግ በብዙ መከራ ውስጥ ለሚገኛው የዐማራ ሕዝብ እውነተኛ ድምፅና ተሟጋች ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ስለሆነም በፓርቲው ላይ ከመጠን ያለፈ አላስፈላጊ ጫናን ላለመፍጠርና አጋጣሚውን ተጠቅመው ፓርቲውንና ሕዝቡን አደጋ ውስጥ ለመክተት የሚፈልጉ አካላትን ሴራ ለማምከንና የእኩይ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ ላለመሆን መጠንቀቅ ስለሚገባ በፓርቲው ላይ የምንሰነዝራቸውን ወቀሳዎችንና የምናነሳቸውን ጥያቄዎች ለጊዜው እንግታቸው! … እደግመዋለሁ…  በዐ.ብ.ን ላይ የምንሰነዝራቸውን ወቀሳዎችንና የምናነሳቸውን ጥያቄዎች ለጊዜው እንግታቸው! ከቀደሙት ስህተቶቻችን ልምድ መውሰድና መማር አለብን!
እንደመውጫ፡-
የዐ.ብ.ን አመራሮች የፌስቡክ አጠቃቀም ‹‹ሕፃናትን የሚያስመሰግን›› ስለሆነ ፓርቲው አመራሮቹ እንደፈለጉ ፌስቡክ ላይ እንዳይጽፉ የሚከለክል ጥብቅ የስነ ስርዓት ደንብ እንዲያዘጋጅ እመክራለሁ! የአመራሮቹ የፌስቡክ አጠቃቀም እንኳን ወዳጅን ጠላትንም የሚያሳፍርና የሚያሸማቅቅ ነው! እባካችሁ ሁሉንም ነገር ወደፌስቡክ እያመጣችሁ አታላዝኑ!
በተረፈ፣ ዐ.ብ.ን እንደዛሬው ሳይሆን አስደናቂና አስደሳች አፈፃፀም ያሳይ በነበረበት ወቅት እንኳ፣ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀቶችና አማራጮች ያስፈልጋሉ የሚል አቋም ነበረኝ፤ይህ አቋሜ አሁንም አልተቀየረም! የዐማራ ሕዝብን ትግል ለአንድ ፓርቲ (ለዐ.ብ.ን) ብቻ አምኖ የመስጠት እሳቤ ትክክል ነው ብለው የሚያስቡ ካሉ፣ አሁንም ቢሆን የችግራችን ጥልቀት አልተገለጠላቸውም ማለት ነው፡፡
ድል ለዐ.ብ.ን!
ድል ለዐማራ!
ድል ለኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic