>
5:16 pm - Tuesday May 24, 0129

ለነገ፤ ዛሬ ዝግጅት የማድረግ ግዴታ! (አንዱ ዓለም ተፈራ፤)

ለነገ፤ ዛሬ ዝግጅት የማድረግ ግዴታ!

አንዱ ዓለም ተፈራ፤  


በትናንት እውነታ ማማረር አንድ ነገር ነው። ዛሬ ላይ ተቀምጠን ነገ ለውጥ እንዲመጣ መፈለግ ሌላ ነገር ነው። ዛሬ ላይ በተከሰቱ ቀውሶች ተጠምዶ፤ በዛሬ ክንውኖች ረክቶ ወይንም ተበሳጭቶ ማደር፤ ሌላ ነገር ነው። ለውጥ ፈላጊ ደግሞ፤ ከዚህ ያለፈ ኃላፊነት አለበት። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀቅ፤ በመንግሥት ደረጃም ሆነ ባጠቃላይ በለውጥ ፈላጊ ድርጅቶችና በታታሪ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ውስጥ፤ ከዛሬው እውነታ ተነስቶ፤ ለነገው የፍላጎት መዳረሻ በቂ ዝግጅት ማድረጉ ላይ፤ ዳተኝነት አይሎ ይታያል። ጣሊያን በአፄ ሚኒሊክ ተገርፎ ሲመለስ፤ ደግሞ ሊመጣ ይችላል ብሎ አለመዘጋጀታችን አንዱ ነው። የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ እየቀረበ መሄዱን አመላካች ብዙ ነገሮች እየታዩ፤ መከተል ስለሚገባው መንግሥትም ሆነ ሥርዓት አለመዘጋጀቱ ሌላው ነገር ነበር። ደርግ አረመኔነቱ እየከፋና የመውደቂያ ጊዜው እየቀረበ ሲሄድ፤ መከተል ስላለበት መንግሥትም ሆነ ሥርዓት ዝግጅት ማነሱ፤ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የውድቀት ቀናት እየቀረቡ ሲሄዱ፤ መከተል ስላለበት በቂ ዝግጅት አለመደረጉ አሁን ላለንበት ሁኔታ ዳርጎናል። አሁንም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ባደረገው ወረራ እየተከተለ ያለውን ሀቅ፤ ባብዛኛው የዕለት ተዕለቱን በመከታተልና ለዛሬ ብቻ የሚሆን አስተዋፅዖ በማድረግ ተጠምደናል። ነገ ለሚከተለው ግን ውይይቱ አልተከፈተም። የዚህ ጽሑፍ ማዕከላዊ ማጠንጠኛው ይሄ ነው።

ለነገ የአገራችን የፖለቲካ እውነታ ተግባሩም ሆነ ዕቅዱ፤ በርግጥ የመንግሥት ክፍል አለያም በተወዳዳሪነት የቀረበ የፖለቲካ ድርጅት ባለቤትነቱን ይወስዳል። ሆኖም ግን፤ እንደ ኢትዮጵያዊያን፤ ሁላችንም ብንሆን፤ ለአገራችን የነገ የፖለቲካ ክስተት ኃላፊነት አለብን። ሊከተሉ ከሚችሉት መክካከል ሁለቱን ላንሳ። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለፖለቲካ ጠቀሜታው ሲል ወይንም በውጪ መንግሥታት ተፅዕኖ ምክንያት፤ ከፀረ-ኢትዮጵያዊያንና ፀረ0ኢትዮጵያው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ድርድር አድርጎ፤ የተገኘውን ድል ዋጋ ቢያሣጣው፤ ወይንም ከተከዜ ወዲያ እንደፈለጋችሁ ቢል፤ ምን ይከተላል? በአንጻሩ ደግሞ፤ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፤ ማለትም ብልፅግና፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መደምሰስን የራሱ የግል ክንውን በማድረግ፤ አሁን ያለውን የትግሬዎች ነጻ አውጪ ግንባር የፖለቲካ ፍልስፍና፣ የአስተዳደር ዘይቤና ሕገ መንግሥት ቢገፋበት፤ ምን ይደረጋል? በተለይ ደግሞ በአንድ መልኩ ወይንም በሌላ፤ ተቃዋሚዎችን አዳክሞም ሆነ አጥፍቶ የአምባገነን መንግሥት ቢሆን ምን ይከተላል? ይሄን ለመመርመርና እንዲከተል የምንፈልገው ሥርዓት ሀቅ እንዲሆን ምን ማድረግ እንደሚገባ ለማወቅ፤ የግድ የፖለቲካ ሊቅነትን አይጠይቅም። ከትናንቱ መማር ብቻ ነው ያለብን። ከትናንት መማር ያልቻለ፤ የትናንትን ጥፋት መድገሙ አጠያያቂ አይሆንም። ዛሬ ቀን በቀን በሚካሄዱ የፖለቲካ ክንውኖች ተጠምደን ነገን መጠበቁ፤ በለመድነው የአዟሪት መንገድ መጓዝ ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ያለነው በአጠቃላይ፤ በኅብረትም ሆነ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እየመራን፤ የዛሬን ችግር ዛሬ መፍታት ብቻ ሳይሆን፤ ለነገም መዘጋጀት ግዴታችን ነው።

የማቀርበው ሃሳብ፤ የመንግሥት አፈ ቀላጤ ወይንም የተፎካካሪ ድርጅት አባል ሆኜ አይደለም። አይደለሁምና! የተነሳሁት የፖለቲካ ውይይት ለመጫር ነው። ሃሳቤ የሚከተለው ነው። ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ወይንም ብልፅግናን በሁሉም መንገድ ተነስቶ በጭፍኑ፤ ይሄን ሠሩ ወይንም ያን ሳይሠሩ ቀሩ ብሎ መኮነኑ፤ ትክክለኛ መፍትሔ አይደለም። በርግጥ የመንግሥትን የሥራ ድክመት መጠቆምና ትክክለኛ አቅጣጫውን ማመላከቱ ተገቢ ነው። ይሄ መኢሶን ከደርግ ጋር ወግኖ፤ ደርግን መምከርና ማረም ብሎ ለሥልጣኑ እንደተጠቀመበትና ብዙ ተራማጆችን እንደፈጀበት አይደለም። የብልፅግና ፓርቲ ከደርግ የሚለይበት ብዙ መንገድ አለ። እዚህ ላይ የብልፅግና ፓርቲ ፍጹም ነውና አትንኩት የሚል እምነት የለኝም። ነገር ግን፤ ባሁኑ ሰዓት፤ ከሁሉም የአገራችን የፖለቲካ ቅራኔዎች ሁሉ ዋናነቱንና የበላይነቱን የወሰደ ቅራኔ ጎልቶ፤ የነገዉን የአገራችን ሕልውና አደጋ ላይ የጣለው ሀቅ ግድ ስላለው ነው። የቅራኔዎች ቅደም ተከተል፤ ትኩረታችን የት ላይ መሆን እንዳለበት ያዛሉ። የአገራችን ችግሮች መፍትሔ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወይንም በብልፅግና ኪስ የሚገኝ፤ የግል ባለቤትነት የተፈረመበት አይደለም። በፓርቲው ፍላጎትና እምነት የተቀፈደደም አይደለም። መፍትሔው በማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ልብ ያለ ነው። ይህ ደግሞ፤ በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ አገር ወዳዶችንም ያጠቃልላል። 

አሁን አንዳንድ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በመንግሥት ላይ ውርጅብኝ ሲያበዙ አያለሁ። ትክክል ሆነም አልሆነም፤ ለምንቃወመው ማንኛውም ሃሳብ ወይንም ድርጊት፤ በመጀመሪያ አማራጭ የሆነ የተሻለና ሊተገበር የሚችል ሃሳብ ማቅረብ የግድ ነው። አሁን በሽብርተኛው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወረራ ላይ እየተካሄደ ያለው አገርን መከላከልና መልሶ ማጥቃት ትክክለኛና ተገቢ ነው። ይሄን አገር አፍራሽ ድርጅት መደምሰሱ ግዴታ ነው። ይሄ መከላከልና፤ ይሄን ድርጅት መደምሰሱ ብቻ በቂ አይደለም። ይሄ ድርጅት በአገራችን ላይ ያሰፈረው የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር ዘይቤ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የዚህ መከላከል አካል መሆን አለበት። ድርጅቱ ብቻ መፍለሱ፤ ነገ ተመልሰን ወደዚሁ እንዳንዘፈቅ ማስተማመኛ አይደለም። አገር እንዳትፈርስና ተመልሰን በዚሁ የመከፋፈል አባዜ እንዳንሽከረከር፤ የዚህን ድርጅት መሠረታዊ መቀመጫ አብሮ ማጥፋት ያስፈልጋል። ነገ አንዲት ኢትዮጵያ፣ አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አንድ መከላከያ፣ አንድ መንግሥት፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ፣ አንድ ራዕይ እንዲኖረን ከተፈለገ፤ ይሄ እንዳይሆን እንቅፋት የሆነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የተከለው መሠረታዊ እውነታ መፍረስ አለበት።

ሕገ-መንግሥት የአንድ አገር ገዥ መተዳደሪያ ደንብ ነው። አሁን በአገራችን ላይ ያለው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሕገ-መንግሥት ነው። በዚሁ ሕገ-መንግሥት ውስጥ፤ አገራችን በታጠሩ ክልሎች ተከፋፍላለች። ለያንዳንዱ ክልል የየግላቸው የማንነት ጌጥና ክብር ኩል የሚሆን ሰንደቅ ዓላማ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሠጥቷቸዋል። የይስሙላ እንጂ፤ ትክክለኛ አገር አቀፍ የሆነ መግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖር አደረገ። አንዱን ክልል የበላይ ሌላውን የበታች አደረገ። አንድ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ኖሮን፤ ሁላችን በአንድነት ተባብረን የምናውለበልበው አሳጣን። በኢትዮጵያዊነታችን፤ በየክልላችን እንጂ፤ በሌላው የትኛውም የኢትዮጵያ መሬት የመኖር፣ ሀብት የማፍራት፣ በኅብረተሰቡ ክንውኖች በኢትዮጵያዊነታችን የመሳተፍ መብታችንን ነፈገ። ይሄን ኢትዮጵያዊያንን የመከፋፈልና ኢትዮጵያን የማጥፋት ፍላጎቱን በሕገ-መንግሥቱ አስቀመጠ። አሁን በአገራችን ያለው የፖለቲካ ሀቅ ይሄ ነው። አሁንም አስተሳሰባችንን የሚገዛው ኦሮሞነታችን፣ አማራነታችን፣ ትግሬነታችን፣ ሶማሌነታችን፣ ሲዳማነታችን . . . ነው። ሁለት የማሰቢያ መንገዶች አይገዙንም። በትውልድ እዚህ ወይንም እዚያ ልንሆን እንችላለን። በኢትዮጵያ ስንኖር ግን ኢትዮጵያዊነታችን ብቻ ነው ገዢው። ለዚህ ኢትዮጵያዊያንን ማዕከል ያደረገ ሕገ-መንግሥት ያስፈልጋል።

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በአገራችን ውስጥ ላሉ አንዳንድ ችግሮች መፍትሄዎችን አቅርቧል። ከነዚህ ውስጥ አሁን እየተደረገ ያለውን ዘመቻ መምራቱ ይጠቀሳል። በዚህም በተወሰነ ደረጃ የሕዝቡን ድጋፍ አግኝቷል። በአንጻሩ ደግሞ፤ በመንግሥት ደረጃ ሊያደርግ የሚገባውን ሳያደርግ ቀርቷል። እዚህ ላይ እኔ በዋናነት የምጠቅሰው፤ በአማራው ላይ እየተደረገ ያለውን ጭፍጨፋ መታገሱ ነው። በተለይ ደግሞ፤ በኦነግ ሸኔና በኦሮሚያ አስተዳደር ውስጥ ባሉ አክራሪ አማራ ጠሎች፤ በወለጋ፣ በአርሲ፣ በሐረር፣ በሸዋና በወሎ፤ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የግዛት ዘመን ጀምሮ እስካሁን እየተባባሰ የሚካሄደውን አማራን የማጥፋት ዘመቻ ያላሳሰበው መሆኑ ነው። ይህ በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገ ፈቃድ ነው። ትግራይ ላይ ዘምቶ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን የደቆሰ ሠራዊት፤ ኦነግ ሸኔን የገባበቱ ገብቶ መደምሰስ ያቅተዋል የሚል እምነት የለኝም። በርግጥ የዚህን ሕገ-መንግሥት ጥልቅ ጉዳት ማስረዳቱ ከባድ አይደለም። የግድ መለወጥ አለበት የሚባለው ለዚህ ነው።

ዋናዎቹ የነገ ገዢ ጉዳዮች፤ አንደኛ፤ አስተዳደርን ከክልል ማንነት ነፃ አውጥቶ በአስተዳደር አመቺነቱ መተካት ነው። ይህ የነገ  የተስፋ ተግባር ሳይሆን የዛሬ ግዴታ ነው። ሁለተኛ፤ አጥፊዎች በሕግ የማይጠየቁበት ማንኛውም የመንግሥት ሂደት፤ አዳዲስ አጥፊዎችን አምራች ነው። ለተከሰቱ ጥፋቶች ተጠያቂዎች መኖር አለባቸው። ሶስተኛ፤ ነገ፤ እስከዛሬ የተደረጉ ጎጂ ድርጊቶች በሙሉ ተዘርዝረው፤ እንዳይደገሙ ተመክሮ የምናገኝበት እንዲሆን ያስፈልጋል።

ይህ ሁሉ የፖለቲካ አመራር ሠጪ ክፍልን ይጠይቃል። ለጊዜው በቦታው ያለው የብልፅግና መንግሥት ነው። ይሄን መንግሥት ለመግፋትም ሆነ ለመርዳት ደግሞ፤ መፍትሔ የምንላቸው ሃሳቦች በመካከላችን ሊሽከረከሩና ተቀባይነታቸው በሕዝብ መካከል ሊመዘን ይገባል። ውይይቱ እንዲያድግ እያንዳንዳችን በምንችለው እናግዝ።

Filed in: Amharic