>

የሱዳን ጄነራሎች ወግ (A tale of Sudanese Generals) (ጌታቸው ወልዩ)

የሱዳን ጄነራሎች ወግ
(A tale of Sudanese Generals)
ጌታቸው ወልዩ 

-በአብሯደጎችና ኮርስሜት ጄነራሎች የምትሽከረከረው ሱዳን
ውድ የኢትዮጵያ ልጆችና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደ ምን ሰነበታችሁ? ቅዳሜ ታኅሳስ 16 ቀን 2014 ዓመተ ምህረት (እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር ዲሴምበር 25 ቀን 2021)፤ “በሌቦች አገዛዝ (ክሌፕቶክራሲ) ተገዝግዛ፤ ገደል አፋፍ ላይ የቆመችው ሱዳን ገመና” በሚል ርዕስ በሱዳን ጄነራሎችና ሰላዮች፣ የመረጃ መኮንኖችና ደኅንነት ባለሙያዎች በቅርምት የተያዙ 250 የሱዳን ኩባንያዎች ጉዳይ በተመለከተ፤ በተለመደው የብእር ትሩፋቴ የተወሰነ መረጃ እንዳቀበልኳችሁ ይታወቃል።
ጽሑፉም እጅግ አስተማሪ፣ አሳዋቂ፣ አንቂና አስጠንቃቂ ለመሆኑ ካገኘኋቸው ግብረ-መልሶችና አስተያየቶች ልረዳ ችያለሁ። ለአብነት ያህል በራሴ የፌስ ቡክ ገጽ ይህ ጽሑፍ እስከተሠራጨበት አጭር ጊዜ ድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የማጋራት (ሼር) መልእክቶች እንደተጠበቁ ሆነው በትንሹ ከ11ሺ የሚበልጡ አንባቢዎች እንደተከታተሉት ተረድቻለሁ። (ፎቶዎቹን ተጭነው ይመልከቱ)
በተጨማሪ “አዲስ ሚዲያ” ዩቱብ እንዳለ ጽሑፉን አቅርቦት ከ52 ሺ የሚበልጡ ተመልካቾች እንዳደመጡትና እንዳዩት የቁጥር መረጃዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል አገር ቤት የሚታተመው ሳምንታዊው አዲስ ጊዜ መጽሔት በተመሳሳይ ቀን ለንባብ አብቅቶት ብዙ ሺ አንባብያን እውቀትና ግንዛቤ ሊጨብጡበት ችለዋል።  እነዚህ እማኝነት ማስረጃዎች በሌሎች የተለያዩ ሚዲያዎች የተላለፉትን እንደማይጨምሩ እየገለጽኩኝ፤ ዛሬ ደግሞ ሱዳንን እንደ እንዝርት የሚያሽከረክሯት፤  በጥቅምና እከከኝ ልከክህ የተሳሰሩ፤ በጄነራል ማዕረግና በደኅንነት መዋቅር እንደ ጠፍር ገመድ የተጣመሩ፤ ጉደኛ የትምህርት ቤት ጓደኛሞች፣ አብሯደጎችና ጡረተኞች ገመና አወጋችኋለሁና እንደተለመደው እጅግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታችሁ ትከታተሉ ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ።
ውድ ወገኖቼ:- እንዲህ ሆነላችሁ? የቀድሞ የሱዳን ፕሬዚዳንት ሌተና ጄነራል ዑመር ሀሰን አልበሽር ሚያዝያ 3 ቀን 2011 ዓመተ-ምህረት ( እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ቀመር ኤፕሪል 11 ቀን 2019)፤ በአገሪቱ ወታደራዊ ኀይል መፈንቅለ-መንግሥት ተካሂዶባቸው  ከሥልጣን ተወገዱ። ከዚያም “ብድር በምድር” እንዲሉ፤ ሳይወዱ በግዳቸው፤ ባነገሷቸውና የማዕረግ እድገትና ሹመት በሰጧቸው ጄነራሎች ማጅራታቸውን ተይዘው እንደ ከብት እየተነዱ ዘብጥያ ወረዱ።
ፕሬዚዳንት አልበሽር ከሥልጣን መንበራቸው ከተመነገሉ በኋላ ወደ ሱዳን ሉዓላዊ /ወታደራዊ ሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር አዛዥነት ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የወጣው ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን በበኩሉ፤ “የሱዳን ሕዝብን ለማገልገል” በሚል ሽፋን ሥልጣኑን ለማጠናከርና የሹመኛ ጄነራሎችና ደኅንነት ሹማምንት ሀብት ክምችት ለማጎልበት የሚገርሙ እርምጃዎች ወሰደ፤ ሱዳን አገሩን እያንገዳገደ። አል-ቡርሃን የወሰዳቸው እጅግ አስገራሚ እርምጃዎች፤ በዚህ ጽሐፍ እንደ ጥጥ እየፈተሉ፤ እንደ ልቃቂት በውል በውል እየተጠነጠኑና እየተጠቀለሉ ቀርበዋልና ቀዳሚው እነሆ።
ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን ቅድሚያም እንዲህ አደረገ። አብሮ አደጎቹን፣ በአንድ ክፍል አብረውት የተማሩትን የትምህርት ቤትና የወታደራዊ ኮሌጅ ጓደኞቹን ጨምሮ ጡረታ ወጥተው የነበሩ የሥራ ባልደረቦቹን፤ በርካታ የሱዳን ጦር ኀይሎች “ኤስኤኤፍ” (The Sudanese Armed Forces-SAF) አዛዦች እና የቀድሞው የሱዳን ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት  አገልግሎት (The Sudanese National Intelligence and Security Service-
NISS) ሹመኛ ባለሥልጣናትን ከየቤታቸውና ንግድ ኩባንያቸው አስጠርቶ፤ ትእዛዝና መመሪያ ሰጥቶ፤ አዲስ ሹመትና ሥልጣን ሰጣቸው።  የሱዳንን ጉድ በአጽንኦት ለመቃኘት ይረዳ ዘንድ ለአብነት ያህል በቁጥር ሦስት ጄነራሎችን ለማሳያነት መርጫለሁ።
በቅድሚያ ግን ወድ ወገኖቼ፦ በኢትዮጵያ ከሚመሩትና ከሚያዙት ሠራዊት ጋር በአፈርና አቧራ ውስጥ፤ ከበረሃ አሸዋና ከምሲ እስከለየለት የጭቃ ማጥ አብረው እያደሩ ያዋጉ፤ የተራራ ከፍታና የመሬት መሰባበር፤ የአቀበት፣ ቁልቁለት፣ ጎርጅ፣ ሸለቆ፣ ዝርግ መሬትና ጫካ ትብብርን በጭራሽ ያልሰጉ፤ ውርጭ፣ ብርድ፣ ደጋ፣ ወይና ደጋና በረሃ የአየር ጸባይ ያልበገራቸው፤  የበረሃ ንዳድ፣ ሙቀት፣ ግለትና የውሃ ጥም ያልፈተናቸው፤ ግላዊ ጥቅምና ራስ ወዳድነት ያላጠቃቸው፤ በውጊያ ብቃታቸው አንቱ የተባሉ፤ ቀን ከሌት “ኢትዮጵያዬ!” እያሉ፤ የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉ፤ ለአገራቸው ክብር በኢትዮጵያ ሰንደቅ ተጠቅልለው የሞት ጽዋን የተጎነጩ፤ ለትውልደ-ትውልድ የአሸናፊነትና ጀግንነት ጽዋን የረጩ፤ ለኢትዮጵያና ሕዝቧ የታመኑ፤ በአፈርና ጭቃ ቤት የኖሩ፤  “ቃል፣ አገርና ሕዝብን መውደድ፤ ኀላፊነትን በብቃት መወጣት፣ እምነት፣ አደራ፣ ድል፣ ጀግንነትና መስዋዕትነት”  የሚሉ የከበሩ ቃላትን እንደ ዘመሩ ያለፉና እየዘመሩ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ቆራጥ ጄነራሎችን ጠንቅቄ እንደማውቅ ልነግራችሁ እሻለሁ።
ወደ ሱዳን ስወስዳችሁ ደግሞ ዘመነኛ የሱዳን በርካታ ጄነራሎች፤ በሚያዙት ሠራዊት መካከል ሲያልፉ ጦራቸው በተጠንቀቅ ቆሞ የብረት ሰላምታ ብቻ እንዲሰጣቸው የማይፈልጉ፤ በስጋትና ፍራቻ ርዶ ጠብ እርግፍ እንዲልላቸው የሚጓጉ፤ የአገሪቱ ሰንደቅ (ባንዲራ)  እንደ ዣንጥላና ድባብ ከላይ፣ ከግራና ቀኝ እንዲያጅባቸውና እንዲከባቸው የሚፈልጉ፤ ሠራዊቱን በአገራዊ ድጋፍ ሽፋን ባህር አሻግረው ለቢጤዎቻቸውና መሸጎጫ ወዳጆቻቸው ዐረብ አገሮች የፍልሚያ ሜዳ በቅጥረኛነት አሰልፈው ብዙ መቶ ሚሊየን ዶላር ወደ ካዝናቸው የሚያንጋጉ፤ በግል ጥቅምና ሽርክና የተሳሰሩ ነጋዴ ጄነራሎች እንደሆኑ ትረዳላችሁ።
በዚህም መሠረት፦ ከሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን ተሿሚ  ጄነራሎች መካከል:-ጄነራል ሞሐላብ ሐሰን አህመድን ባጭሩ አስተዋውቃችኋለሁ። ጄነራል ሞሐላብ ሐሰን አህመድ፤ በምኅጻረ-ቃል “ኤንሲፒ” የሚሰኘው፤ የቀድሞው መንግሥታዊውብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ (The National Congress Party) በጀት የሚበጅትለት፤ ወርቅ እያወጣና እያመረተ በመሸጥ አንቱታን ያገኘው፤ በመዝናኛ አገልግሎት ዘርፍ ተሠማርቶ ሁነቶች ሚፈጥረው የሰማዕታት ድርጅት (Martyrs’ Organization)  ኀላፊ ሆኖ በሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን የተሾመ፤ የአል-ቡርሃን ሎሌ ጄነራል ነው። አምላክ ያሳያችሁና አንድ የሰማዕታት ድርጅት በአገር አውራ ፓርቲ በጀት ሲበጀትለት፣ ወርቅ እያመረተ ሲሸጥና ሀብት ሲያካብት፤ ብሎም ሰማዕታትን መዘከር ሲገባው የመዝናኛ አገልግሎት ውስጥ ገብቶ በጥቅም ሲንቦጫረቅና በሽርክና በሀብት ማከማቸት ዙሪያ ሲሟገት?! አይ ጎረቤት ሱዳን!?
እናንተ በዚህ ስተገረሙ፤ ጄነራል ሞሐላብ ሐሰን አህመድና አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን በወጣትነታቸው ዘመናቸው ትውውቅ የነበራቸው፤ በአንድ ትምህርት ቤት አንድ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው መማራቸው የተመሠከረላቸው፤ በውትድርና ሕይወት በመኮንነት ማዕረግ አብረው የተንደረደሩ፤ የተመሳሳይ ወፍ ላባ እንዳላቸው የሚናገሩ፤ ጥቅምና ሥልጣን ያስተሳሰራቸው ጄነራሎች ስለመሆናቸው እኔ እነግራችኋለሁ።
ሌላኛው ጄነራል፦ ጄነራል አባስ አብድልአዚዝ ሲሆን፤ ጄነራል አባስ አብድልአዚዝ በምኅጻረ-ቃል “አርኤስኤፍ” (RSF) የሚባለውና በአሁኑ ወቅት ሱዳንን በጥባጩና ቦጥቧጩ፤ በግል ሀብት ማካበት በዝርፊያ ተርመጥማጩና ፈላጭ ቆራጩ፤ ሌተና ጄራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐሜቲ /ሔምዲቲ) እንደ ግሉ ጦር የሚያሽከረክረው የተጠባባቂ ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኀይሎች ጦር የቀድሞ አዛዥ ነበረ።
 ጄነራል አባስ አብድልአዚዝ፦ ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን የሱዳን ሉዓላዊ /ወታደራዊ ሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር አዛዥነት ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን አናት ላይ ወጥተው ፊጥጥ ሲሉ፤ ቅድሚያ የተጠራ፤ ለአል-ቡርሃን ታማኝነቱን በአደባባይ የሚመሰክር፤ በአሁኑ ወቅት አል-ሳቲ ኩባንያን እንደ ጎማ እንዲያሽከረክር፤ በሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-
ቡርሃን ተሹሞ የታማኝ ባለሟልነት ሥልጣንን እንደ ካባ የደረበ ጄነራል ነው።
አሁን ደግሞ ስለ ሌተና ጄነራል አል-ሚርግሃኒ ኢድሪስ ሱሌይማን ልንገራችሁ። ሌተና ጄነራል አል-ሚርግሃኒ ኢድሪስ ሱሌይማን፤ በቄራዎች አገልግሎትና ሌሎች በርካታ የንግድ ዘርፎች የተሠማራው የመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ኀላፊ ሆኖ በማዕረግ አቻው በሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን  የተሾመ ጄነራል ነው።
መታወቅ ያለበት ሌተና ጄነራል አል-ሚርግሃኒ ኢድሪስና  ሌተና ጄነራል አል-ቡርሃን ገና በሱዳን ወታደራዊ ኮሌጅ ሳሉ የሚተዋወቁ፤ በጓደኝነትና ቅርበት ረዥም አመታት የዘለቁ ጄነራል መኮንኖች የመሆናቸው ጉዳይ ነው።
የኋላ ኋላ ሌተና ጄነራል አል-ሚርግሃኒ ኢድሪስ የአል-ቡርሃን ትእዛዝ ፈጻሚነቱና አስፈጻሚነቱ በመታወቁ፤ አል-ቡርሃን ቁልፉን የወታደራዊ ተቋም አመራር ቦታ ሊያበረክትለት ችሏል።
እናም በተጠቀሱት የሌተና ጄነራል አል-ቡርሃን የተሾሙት ታማኝ ጄነራሎች በሚያጦዟት ሱዳን፤ “የወታደራዊና ደኅንነት (የመረጃ፣ ስለላና ፀጥታ) ተቋማት በርካታ ሹመኞች፤  በግልና በጋራ በወርቅ ማዕድን ማውጣት፣ ማምረትና ወደ ውጭ መላክ ተሠማርተዋል!” ስትባሉ ትገረሙ ይሆናል?
ግና የነዳጅ እጥረት እንደ ዳቦ እጥረት ሱዳንን ክፉኛ እየደቆሳት ሳለ፤ የነዳጅ ኩባንያዎችን ተቀራምተው ነዳጅ ከውጭ የሚያስገቡ፣ የሚያከፋፍሉና የሚሸጡ፤ የሱዳንን ሙጫ ጨምሮ “ገም ዐረቢክ”፣ ሰሊጥና ጦር መሣሪያዎች የሚነግዱ የወታደራዊና የደኅንነት ኩባንያዎች በሱዳን ውስጥ ደረታቸውን ነፍተው እንደሚንቀሳቀሱ፤ ብትሰሙ ምን ትሉ ይሆን?
 ይህ ብቻ እንዳይመስላችሁ? ሱዳንን የዳቦ ቅርጫት ሊያደርጋት የሚችል በመቶ ሺዎች ሄክታር የሚገመት ለም መሬት ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች፣ ኩባንያዎችና ቱጃር ባለሃብቶች ሸጠው ስንዴ የሚያስመርቱ፤ በተገላቢጦሽ ደግሞ “በራሴ ዳቦ ልብ ልቡን አጣሁት?!” እንዱሉ ስንዴ ከውጭ ወደ አገረ-ሱዳን የሚያስገቡ የወታደራዊና የደኅንነት ኩባንያዎች በጎረቤት ሱዳን ውስጥ እንዳሉ ያወቃችሁ ጊዜ በቁሟ እንደ ቦቆሎ ተግጣ በችግር ለምትዳክረው ሱዳን ታዝናላችሁ።
ጎበዝ!  በሱዳን በግልና በቡድን የሚተዳደሩ የወታደራዊና የደኅንነት ተቋማት ከውጭ አገር ተሽከርካሪዎችኝ (መኪናዎችን) አስመጥተው መሸጥን፤ በጭነትና ሊሙዚን መኪና አገልግሎት ዘርፍ መሠማራትን እንደ ቀላል ሥራ መቁጠራቸውን ስታውቁ “ወይ የሱዳን ነገር?” ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም።
እንዲሁም በኮንስትራክሽን (ግንባታ)፣ ሪል ስቴት ልማት፣ ውሃ ማውጣት፣ ማምጣትና ማሠራጨት፤ በባንክና ቴሌኮሙኒኬሽን፤ በአቪየሽን (በረራ)፣ ቱሪዝምና ፓርኮች ሥራ አመራር፤ በመዝናኛ አገልግሎት ዝግጅት ያላቸው የገዘፈ የሀብት ክምችት ድርሻ ስትመለከቱ ደግሞ “እግዚኦ!” ከማለት ወደ ኋላ አትሉም።
የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ደግሞ፤ የመከላከያ/የጦር ኀይል ኩባንያዎች የሚያመርቷቸው የአየር ማቀዝቀዣ (air conditions)፣ የውሃ ቧንቧዎች፣ መድኀኒትና የመድኃኒት መያዣ እቃዎች፣ የጽዳት እቃዎችና ጨርቃ ጨርቆች ውስጥ አያሌ የሱዳን ጄነራሎች እጃቸውን አስገብተው የለየላቸው ነጋዴዎች የመሆናቸው ነገር ነው። ቆይ ግን ጎበዝ! ለእነዚህ አይኘቶቹ ጄነራሎች ሱዳን አገራቸው አይደለችም እንዴ?
እሺ እቅጭ እቅጩን እንነጋገር ከተባለ እነዚህ የወታደራዊና የደኅንነት ተቋማት ሹመኞች የእምነበረድ ጡብ ማምረት፣ በቆዳ ፋብሪካዎች፣ ቄራ አገልግሎትና የአገሪቱን ገንዘብ  ውስጥ ሁሉ የግል ጥቅምና ሀብት ክምችት እጃቸው ያለበት መሆኑ አያስገርምም ትላላችሁ?
ለማንኛውም:- ሱዳን በጅምላ የሕዝብ ፍጅት የሚወነጀሉ ጎልማሳና አዛውንት ጄነራሎች (The Old Genocidal Military Generals) እየተመራች፤
በራሷ ባሳደገቻቸው ወይፈኖችና ባደለበቻቸው በሬዎች ክፉኛ እየተወጋች ያለች፤ እንደ ሸንኮራ አገዳ ታኝካ እየተተፋችና በልጆቿ አማካይነት በስለት ቢላ በመቀላት ላይ የሆነች ባለ ብዙ ፈተና አገር ነች።
ግና የሱዳን ጄነራሎች የሱዳንን ምጣኔ ሀብት ለምን ተቆጣጠሩት?
(Why the Sudan’s generals controlled the Sudan economy?)
የሆኖ ሆኖ ሱዳን በአሁኑ ጊዜ ግብጽ፣ አንዳንድ ወዳጅ መሳይ ዐረብ አገሮችና ምዕራባውያን በተዘጋጀላት ወጥመድ ውስጥ ገብታ የምትፈራገጥ አገር ሆናለችና እርምጃዋን በአንክሮ ማየት ለኢትዮጵያም እንደሚበጃት መጠቆም እሻለሁ። ማጠቃለያዬ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! የሚል መልእክቴ ሲሆን የኢትዮጵያ አምላክ አገረ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic