>
5:13 pm - Saturday April 19, 3586

"ቤተ-እስራኤላዊያን ኢትዮጵያን አትንኩብን በሚል መንፈስ ተነስተዋል" (ኢዜአ) 

“ቤተ-እስራኤላዊያን ኢትዮጵያን አትንኩብን በሚል መንፈስ ተነስተዋል”
(ኢዜአ) 

ቤተ-እስራኤላዊያን “ኢትዮጵያን አትንኩብን፤ የእሷ ጥቃት የእኛም ጥቃት ነው” በሚል መንፈስ መነሳታቸውን የቀድሞው የእስራኤል ፓርላማ /ክኔሴት/ አባል ሽሎሞ ሞላ ተናገሩ።
ቤተ-እስራኤላዊያን ንግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰለሞንን ጠይቃ ስትመለስ አጅበዋት እንደመጡ የሚገልጹ መረጃዎች አሉ።
የእስራኤል ምኩራብ በባቢሎናዊያን ከመፍረሱ ጋር ተያይዞ ወደ ግብፅ የተሰደዱ፤ ከዚያም ክሊዮፓትራ ስልጣን እስከያዘችበት ጊዜ ቆይተው በአውግስጦስ ቄሳር በመሸነፏ ምክንያት ወደተለያዩ አገራት መሰደዳቸውም ይነገራል።
ንጉስ ካሌብ ግዛቱን ለማስፋፋት የመንን በወረረበት ወቅት እንደመጡም ይገለጻል።
ቤተ-እስራኤላዊያን በ14ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የተለያዩ ጽሁፎች የሚያመላክቱ ሲሆን፤ በሰሜንና በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ኖረዋል አሁንም እየኖሩ ነው።
በእስራኤል 140 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን ቤተ-እስራኤሎች እንደሚኖሩ እንደሚገመት የሚያሳዩ መረጃዎችም አሉ።
የቀድሞው የእስራኤል ፓርላማ /ክኔሴት/ አባል ሽሎሞ ሞላ ቤተ-እስራኤላዊያኑ አሸባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች የፈጸመው ግፍ እረፍት እንደነሳቸውና ልባቸውንም እንዳደማው ለኢዜአ ገልጸዋል።
ቤተ-እስራኤላዊያኑ ከኢትዮጵያ ጋር በደምና በአጥንት የተሳሰሩ መሆናቸውን፤ በታሪክም የኢትዮጵያን ነጻነት ለማስከበር ሕይወታቸውን መገበራቸውን ጠቅሰዋል።
ቤተ-እስራኤላዊያን ለኢትዮጵያ በመቆርቆር፤ “ኢትዮጵያን አትንኩብን የእኛ ናት በእሷ ላይ የሚደርስ ጥቃት በእኛ ላይ እንደደረሰ አድርገን እናየዋለን ነው” የሚሉት ብለዋል ሽሎሞ።
በእስራኤል የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላትም ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያና እስራኤል ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዳላቸው ነው ሽሎሞ የገለጹት።
ይሁን እንጂ ባለፈው አንድ ዓመት እስራኤል በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ “በይፋ አቋሟን አሳውቃ አታውቅም” ይህም በእስራኤል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በእጅጉ ያሳሰበ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት ህወሓትና ሸኔ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸሙትን ግፍና ያደረሱትን መከራ እስራኤል እስካሁን አለማውገዟ ተገቢነት የሌለው አካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል።
“እስራኤል አሸባሪ ቡድኖች የሚፈጽሙት የሽብር ድርጊት ገፈት ቀማሽ መሆኗን ታሪክ የሚያሳየው ነው፤ አሁንም ከእነዚህ የሸብር ስጋቶች አልተላቀቀችም” ነው ያሉት የቀድሞው የእስራኤል ፓርላማ አባል።
በእስራኤል የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት እስራኤል በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በሽብር ቡድኖቹ  ግልጽ የሆነ አቋሟን ማሳወቅ አለባት በሚል በቅርቡ የ’በቃ’ ወይም ‘#NoMore’ ሠላማዊ ሠልፍ ማካሄዳቸውን  ሽሎሞ አስታውሰዋል።
ኮሚዩኒቲው ለእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያኢር ላፒድ፣ ለመከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ እና ለእስራኤል ፓርላማ አባላት ደብዳቤ በመጻፍ አቋሟን እንድታሳውቅ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እስራኤል አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ የሚፈጽሙትን ድርጊት በማውገዝ ጠንካራ አቋም እንድትይዝ የዲፕሎማሲ ጥረት እየተደረገ እንደሆነና የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ግፊት በይፋ አቋሟን እስከምታሳውቅ ይቀጥላልም ብለዋል።
በአንጻሩ የእስራኤል ሕዝብ ለኢትዮጵያ ወዳጅ ነው፤ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ያከብራል ነው ያሉት ሽሎሞ ሕዝቧ በሽብር ድርጊት የደረሰበትን ጉዳት ስለሚያውቅ ሽብርተኝነት አጠብቆ እንደሚቃወምና አገራቸው ህወሓትና ሸኔን በይፋ ብታወግዝ ይህንኑ ተከትለው የሚፈጽመውን ድርጊት እንደሚኮንኑ ምንም ጥርጥር እንደሌለው ነው የተናገሩት።
በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት እስራኤል በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር መስኮች የጀመሯቸውን ስራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለዋል።
ቤተ-እስራኤላዊው የ56 ዓመቱ ፖለቲከኛ ሽሎሞ ሞላ እ.አ.አ ከ2008 እስከ 2013 የካዲማና ሃትኑዋ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በመወከል የእስራኤልን ፓርላማ /ክኔሰት/ ያገለገሉ ሲሆን፣ የፓርላማው ምክትል አፈ-ጉባኤ በመሆንም ሰርተዋል።
Filed in: Amharic