እነ እስክንድር በተከሰሱበት ክስ እንዲከላከሉ ወይም በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን ለመስጠት ለጥር 25 ተቀጠረ….!!!
ባልደራስ
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ምስክሮች እማኝነታቸውን መርምሮ ፣እነ እስክንድር በተከሰሱበት ክስ ይከላከሉ ወይም በነፃ ይለቀቁ የሚል ብይን ለመስጠት ለጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ።
ዛሬ ታኅሣሥ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ቀሪ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮ የሆኑት 4ኛ ምስክር ” ፍጹም ተሰማ ” ቀርበው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ቀጠሮ ለ7 ጊዜ ቢሰጥም ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ምስክሩ ባለመቅረባቸው እኚህ ምስክር እንዲታለፉ ችሎቱ በዛሬው ቀጠሮ ብይን ሰጥቶበታል።
ቀሪ አስራ ሁለቱ (12) የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን በተመለከተ ፤ ዐቃቤ ሕግ በዛሬው ችሎች ለፍርድ ቤት እንደገለጸው ፤ ” ማንነታቸው በሚዲያ እንዳይገለጽ እና ስም ዝርዝራቸው ለተከሳሾች አስቀድሞ እንዳይደርሳቸው ” በማለት ያቀረበውን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉ የሚታወሰው ነው። የምስክሮች አቀራረብ አስመልክቶ ከዚህ ቀደም የተሰጠ ትዕዛዝ የጸና እንደሆነ በመግለጹ እና ዐቃቤ ሕግ ቀሪ አስራ ሁለት ምስክሮችን በግልጽ ችሎት ቀርበው እንዲመሰክሩ ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም በሰጠው ብይን መሠረት አቅርቦ ማስመስከር እንዳልፈለገ ተቆጥሮ የማሰማት መብቱ ይታለፉ በማለት ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ዐቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ላይ በግልጽ ችሎት አቅርቦ ምስክርነታቸውን እስካሁን ያሰጠው ካቀረባቸው 21 ምስክሮች ስድስት ብቻ ሲሆኑ ፤ የእነኚህን ምስክሮች እማኝነታቸው መርምሮ እነ እስክንድር በተከሰሱበት ክስ እራሳቸውን መከላከል ያስፈልጋቸዋል ወይም በነፃ ሊሰናበቱ ይገባል በማለት ብይን ለመስጠት ለጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል ።
በዚሁ የክስ መዝገብ ጎን ለጎን ደግሞ በ1ኛ ተከሳሽ አቶ እስክንድር ነጋ ላይ ከዚህ ቀደም በቂሊንጦ ወህኒ ቤት የተፈጸመውን ድብደባ በተመለከተ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ከተፈጸመው ድብደባ ጋር በተያያዘ ለፍርድ ቤት ያቀረቡትን ሪፓርት በተመለከተ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት በተመሳሳይ ለጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል ።