>
5:13 pm - Monday April 19, 8984

የኀዘን መልእክት! (ከቀድሞው የኢህዲሪ  ፕሬዝዳንት ሌ /ኮ መንግሥቱ ኃ/ማርያም - ገነት አየለ አንበሴ)

የኀዘን መልእክት

| ዛሬ የሚፈፀመውን የአምባሳደር  ዶክተር ካሣ ከበደን ዕረፍት በማስመልከት የቀድሞው የኢህዲሪ  ፕሬዝዳንት ሌ /ኮ መንግሥቱ ኃ/ማርያም  የሚከተለውን የኀዘን መልእክት አስተላልፈዋል:: 
” የጓድ ዶክተር ካሣ ከበደን ሕልፈተ ሕይወት በመስማቴ ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶኛል:: ጓድ ካሣ በሥራ ዘመናችን ሁሉ አንድም ቀን ያልተለየኝ የትግል አጋሬ ወንድሜ ነበረ:: እሱን የመሰለ ድንቅ የፈጠራ ችሎታ ያለው ታታሪ ሠራተኛና ሀገሩን የሚወድ ወንድማችን ሲለየን ኀዘኑ ከባድ ነው:: በቅርቡ የተለዩንን  ጓዶቼን በማስታወስ  ዛሬም ጓድ በማጣታችን በእጅጉ  አዝኛለሁ” ::
                     ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም
Via ገነት አየለ

ባለ ብሩህ አእምሮው አምባሳደር ካሣ ከበደ ….!!!

ገነት አየለ አንበሴ

ጊዜው ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ከደርግ አባላት እንዲሁም ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ያደረግሁትን ቃለ መጠይቅ በመፃፍ ሕትመቱን የማዘጋጅበት ወቅት ነበር :: ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በስተቀር አብዛኛዎቹ ገና ፍርድ ሳይፈረድባቸው በእስር ላይ የነበሩ በመሆናቸው ያደረግሁላቸውን ቃለ መጠይቅ ስማቸውን እንዳልጠቅስ ጓድ ቁጥር … እያልኩ ነበር :: በአገር ውስጥ በእስር ያሉትን ጠይቄ ስጨርስ አንድ ትልቅ ሰው እንደቀሩና ያለሳቸው ምስክርነት መጽሐፌ የተሟላ እንደማይሆን ተሰማኝ:: እኛ ሰው አምባሳደር ካሣ ከበደ ነበሩ::
የመንግሥቱ ወንድም ናቸው የሚባለው ሹክሹክታም በየጊዜው የምንሰማው ስለነበረ መንግሥቱን ጠይቄያቸው ከሰጡኝ መልስ በተጨማሪ እሳቸውም እንዲነግሩኝ ፈለግሁና ወደ ዋሽንግተን ዲሲ አቀናሁ:: ወዳጄ ነአምን ዘለቀ ነበረ ቃለ መጠይቁን እንዳደርግ ያመቻቸልኝ::
ቨርጂኒያ ሜሪላንድ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሄጄ አነጋገርኳቸው:: የተደላደለው ምቹ ወንበር ላይ ተቀምጠው አንድ በአንድ ጥያቄዎቼን ሲመልሱ በጣም ብልህ ሰው መሆናቸውን ተረዳሁ:: በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡት ትንታኔ የሚገርም ነበር ::  ስለሚናገሩት ነገር በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዳላቸው ከሚሰነዝሯቸው ሃሳቦች ጥልቀት መረዳት ይቻላል:: የተዋጣላቸው ዲፕሎማት ነበሩ የደጃዝማቹ ልጅ ጓድ ካሣ :: የማህበረ ሰብ ሳይንስ ምሩቅ ብቻ ሳይሆኑ በባለሥልጣንነታቸው ባበረከቱት አስተዋፅኦ ሳይወሰኑ እንደ ተራ ሶሻል ሠራተኛ ሆነው ይሰሩ ነበር ::  ዕረፍት የማያውቁ ታታሪ ሰው መሆናቸው ተመስክሮላቸዋል:: የታጠቅ ጦር ሠፈርን ከምስረታው ጀምረው የለፉበት ሲሆን የሕፃናት አምባን ሃሳቡን ከማፍለቅ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ደክመዋል::
መጽሐፉ ከታተመ ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ሳገኛቸው የመጽሐፉን ገፆች እያገላበጡ ሲያዩ ቆዩና
“እነዚህ ጓድ ቁጥር እከሌ ያልሻቸው እነማናቸው? አሉኝ ትንሽ ምፀት ያለባት ፈገግታ  እያሳዩኝ::
 እኔም አፀፋውን ለመመለስ “ባውቀው ምን አስደበቀኝ?” አልኳቸው እየሳቅሁ::
“ቆይ እንግዲያው እኔ ልንገርሽ” አሉና
ቁጥር …ያልሽው እከሌ ነው:: ይሄ ደግሞ እንትና ነው:: ጓድ እከሌን ነው ቁጥር .. ያልሺው? እያሉ አንድም ሳይሳሳቱ ነገሩኝ:: ማንም እንዳያውቀው የማዕረግ ቅደም ተከተላቸውን ሁሉ አዛብቼ የሰጠሁዋቸውን ቁጥር ወደ ጎን ትተው ከንግግራቸው ብቻ ግንዛቤ በመውሰድ ቁጭ ሲያደርጉልኝ ድካሜ ውሃ በላው ብዬ ክው አልኩ:: ሁሉም ሰው ሁሉ የሚያውቃቸው መሰለኝ:: ድንጋጤዬን ለመደበቅ የማደርገውን ጥረት ከፊቴ እያነበቡ ከት ብለው ሳቁብኝ:: ” እውነትም እኚህን ሰው ሞሳድ ነው ያሰለጠናቸው ” አልኩኝ በልቤ::
ነፍስዎ በአፀደ ገነት ትረፍ ጓድ ካሣ:
Filed in: Amharic