>

እየተራዘመ ያለዉ ጦርነት በአጭሩ ካልተገታ ምን ሊከሰት ይችላል...??? ( ሸንቁጥ አየለ)

እየተራዘመ ያለዉ ጦርነት በአጭሩ ካልተገታ ምን ሊከሰት ይችላል…???
ሸንቁጥ አየለ

አሁንም ቢሆን ህዉሃት ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ ይመስላል::የኢትዮጵያ መንግስት የጦርነት ሂደቱን የያዘበት መንገድ ደግሞ ሰዶ ማሳደድ አይነት ነዉ::ህዉሃት አንድ አካባቢን ገብቶ ካጠፋ እና ካወደመ ብኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ያንን አካባቢ ለማስለቀቅ ሌላ የጦርነት ዉድመት በዚያ አካባቢ ላይ ያዉጃል::
አካባቢዉን ቀድሞ ከመወረር እና ከመዉደም መጠበቅ እየተቻለ አካባቢዉ ከወደመ ብኋላ መልሶ ሌላ የዉድመት ጦርነት በመክፈት አካባቢዉን ለማስለቀቅ ስራ ይሰራል::ይሄም አካባቢዉን ይበልጥ ያወድመዋል::
አካባቢዉ ከወደመ ብኋላ ደግሞ አካባቢዉን መልሶ ለመገንባት በመንግስት በኩል ምንም አይነት ተነሳሽነት የለም::እንዴዉም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ መገንባቱ የክልሎች እዳ ሆኖ ሲቀርብ ይታያል::
ጦርነቱ በህዉሃት እና በብልጽግና መሃከል በወንበረ መንግስት የባለቤትነት ጥያቄ የተጫረ ሆኖ ሳለ ወንበረ ሰልጣኑን በማዕከል ደረጃ ማስጠበቅ የቻለዉ የብልጽግና መንግስት ግን የጦርነት ዉድመቶችን በጦርነት ወደ ወደሙት ክልል ህዝቦች የመግፋት አካሂያዱ በጣም ትክክል ያልሆነ ነዉ::
ለምሳሌም የአማራ ክልል በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን ለመገንባት ከጠዬቀዉ 500 ቢሊዮን ብር ዉስጥ የተፈቀደለት 0.33% ነዉ::ይሄም 1% እንኳን አይሆንም ማለት ነዉ::በጦርነት የተጎዳዉ ህዝብ ግን አሁን ዳስ እንኳን ሳይጣልለት መጠለያ ሳይኖረዉ ከሌሊት አዉሬዎች እና ከብርድ ጋር በሜዳ ተጥሏል::የሚልስ እና የሚቀምሰዉ አጥቶም በርሃብ ጠኔ ዉስጥ ነዉ::
በዬክልሉ ያለዉ ህዝብ ተመሳሳይ ነዉ::ይሄ እዉነታም በትግራይም:በአፋርም:በአማራ ክልልም ነዉ::ከዚህ ጦርነት ህዝቡ ምንም የሚያተርፈዉ ነገር አይኖርም::ከመጠማት እና ከመራብ እንዲሁም በሜዳ ከመበተን ብሎም ከሞት እና ከስደት በቀር ለህዝብ ምንም የሚተርፈዉ ነገር አይኖርም::ይሄም የከፋ የሚሆነዉ ይሄ ጦርነት እየተራዘመ ሲሄድ ነዉ::
ይሄ የጦርነት አካሂያድ እጅግ ብዙ ዉድመት በህዝቡ ላይ እያመጣ ነዉ::ጦርነቱ በዚህ አካሂያድ እጅግ የተንዛዛ እና ገና በርካታ ዉድመት የሚያመጣ ሲሆን ደግሞ የጦርነቱ አሰላለፍ ይለዋወጣል::
———
ይሄን የጦርነቱ አካሂያድ ይበልጥ ዉስብስብ የሚያደርገዉ ደግሞ የምዕራባዉያን አቋም ነዉ::ሰሞኑን የአሜሪካ መንግስት ለ17ኛ ጊዜ ዜጎቹን ከኢትዮጵያ እንዲወጡ እና ሀገሪቱ አሁንም የጦርነት ቀጣና እንደሆነች የሚያሳስብ መግለጫ አዉጥቷል::
ይሄም የሚያሳዬዉ የምዕራባዉያን ሀይሎች ጦርነቱ ላይ ያላቸዉ ግንዛቤ ጦርነቱ የተራዘመ እንደሚሆን ነዉ::ይሄም አቋማቸዉ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም::ይሄ ግንዛቤአቸዉም በተያያዥነት ከሚወስዱት የሀይል አሰላለፍ ጋር ሁሉ የተያያዘ ነዉ::
——-
ከዚህ አይነት የተራዘመ ጦርነት የትኛዉም አካባቢ አያተርፍም::ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የምታተርፈዉ አንዳች ነገር አይኖርም::የአማራ ክልል : የአፋር ክልል እና የትግራይ ክልል በዚህ ጦርነት ብዙ እጅግ ብዙ ወድመዋል::ይሄ ጦርነት በአጭሩ ካልተቀጨ ዉድመቱ ይቀጥላል::
በተወሰነ የዳሰሳ ጥናት የአማራ ክልል እንዳወጣዉ መግለጫ በጦርነቱ ምክንያት የአማራ ክልል በ30 አመታት እና በ40 አመታት ወደኋላ ሄዷል::ይሄም የጦርነቱ ዉድመት በሶስቱ ክልሎች ላይቆም ይቻላል::
ማጠቃለያ
ሁኔታዎች እንዴትም ሆነ በምንም መልክ ሊገለበጡ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል::ይሄም ማለት በርካታ ክልሎች ተያይዘዉ ወደ ጦርነት በመግባት ሀገራዊ ዉድመቱ የከፋ ሊሆን ይችላል::ስለሆነም ይሄ የተራዘመ ጦርነት በተሻለ መንገድ የሚቆምበት መፍትሄ መፈለግ አለበት::ስለሆነም እያንዳንዱ በዚህ ጦርነት የሚሳተፍ ሁሉ ይሄ የተራዘመ ጦርነት የሚያበቃበትን መፍትሄ መፈለግ አለበት::
ሌላዉ ቀርቶ ከዚህ ጦርነት አትራፊ ነን ብለዉ የሚያስቡ ሀይሎች ጭምር ይሄ ጦርነት በአጭሩ ካልተቋጭ በሂደት እነሱንም ጠቅልሎ እንደሚያጠፋቸዉ በመረዳት ይሄ ጦርነት በአጭሩ የሚቀጭበትን መፍትሄ በቅን ልቦና ማፈላለግ አለባቸዉ::
Filed in: Amharic