>

የድህረ ጦርነት እሳቤና የኛ ሁኔታ! (ቹቹ አለባቸው)

የድህረ ጦርነት እሳቤና የኛ ሁኔታ!
ቹቹ አለባቸው

እየተዋጋን የድህረ ጦርነት እሳቤና ትግበራን እዉን እናድርግ!!
 ሰሞኑን መንግስት በየደረጃዉ ማስኬድ የጀመረዉን መድረክ ተከትሎ የተለያዩ አሰተያየቶች ሲሰጡ እየተመለከትኩ ነዉ።  የመድረኩ ዋነኛ ጭብጥ ስለ “ድህረ ጦርነት” የሚመለከት አጀንዳን የሚያነሳ በመሆኑ ፤ በብዙ ወንድምና እህቶቸ ዘንድ ግራ መጋባት ፣በተወሰኑት ደግሞ ብስጭት አዘል አሰተያየት ታዝቢያለሁ። ሁሉም በሚባል ደረጃ ደግሞ ” እዉን ወቅቱ ስለ ድህረ ጦርነት የምናወራበት ነዉ ወይ? ጦርነቱስ ተጠናቋል ወይ? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄወችን እያነሱ ነዉ።
በእኔ እምነት እነዚህ ወንድምና እህቶቸ ከላይ ያነሳሁዋቸዉን ጥያቄወች እና ሀሳቦች ማንሳቻቸዉ ብዙም የሚነቀፉ አይደሉም። ሊነሱ የሚገባቸዉና ልንወያይባቸዉም የሚገቡ አጀንዳወች ናቸዉ ብየ አምናለሁ። እንዴዉም አንድ የአገሩ በተለይም የአማራ ክልል የሚያስጨንቀዉ ሰዉ ሁሉ ሊወያይባቸዉ የሚገቡ አጀንዳወች ናቸዉ እላለሁ።
በዚህ አጀንዳ ጉዳይ ለወደፊቱ በስፋት የምመጣበት ሁኖ ለጊዜዉ ግን ትንሽ ነገር ማለት ፈለግኩ።
# በመጀመሪያ ደረጃ ጦርነቱ አልቋል ወይ? ለሚለዉ ቁልፍ ጥያቄ የኔ መልስ የለም!ጦርነቱ ገና አላለቀም የሚል ነዉ። ጦርነቱ አለቀ የሚባለዉ እያልን እንደመጣነዉ” ትህነግ የአገር ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ሲደርስ ነዉ”። በእኔ እምነት የትህነግ  በአስተማማኝ ሁኔታ ተደምሷል የምለዉ ሁለቱ ወሳኝ አቅሞቹ ከሟሸሹ ብቻ ነዉ። እነሱም:-
1. የትህነግ ኮር አመራር ሲደመሰስ/ሲበተን፣
2. የትግራይ ህዝብ ከትህነግ አመራር የተለየ አቋም ላይ ሲደርስ ናቸዉ።
 እኔ እንደማምነዉ እነዚህ ሁለት  ሁኔታዎች ገና ተሟልዋል ሊባል አይችልም። በእኔ ግንዛቤ የመንግስት ሀሳብም ይሄዉ ይመስለኛል። ስለዚህ የወቅቱን የጦርነቱ “መቆም” ትዕዛዝ  ከዚሁ ጋር ማያያዝ የለብንም(ትህነግ ተሸንፏል ከሚል እሳቤ ጋር)።  ለጊዜዉ የጦርነቱ መቆም ምን አልባትም  ትህነግን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመደምሰስ የሚያስችል ዕድሎችን ለመፍጠር/ማመቻቸት ሊሆን እንደሚችል መገመት ስህተት አይሆንም።
# ቀጥሎ የሚነሳዉ መሰረታዊ ጥያቄ ታድያ ጦርነቱ ካላለቀ በአሁኑ ወቅት ስለ ምን “የድህረ ጦርነት አጀንዳ ይነሳል”? የሚለዉ ነዉ። በእኔ እምነት በደንብ ግልፅ መሆን ያለበት እና መብራራት እንዲሁም የተሟላ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባዉ ቁልፍና ወቅታዊ ጥያቄ ይህ ይመስለኛል።
አሁን የደረስንበት የጦርነት ደረጃ፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን  በተለይም በአማራ ህዝብ ዘንድ  የጦርነትና የድህረ ጦርነት አጀንዳዎች መሳ ለመሳ የሚከወኑበት ወቅት ስለመሆኑ ግንዛቤ መያዝና የጋራ  መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።
አሁን ላይ  ገና በጦርነት ዉስጥ ነን የምንለዉ ጦርነቱ ገና ስላልተጠናቀቀ ነዉ። ማሳያወቹም በርከት ያሉ የአማራ ህዝብና ግዛቶቹ ዛሬም በትህነግ ወረራ ስር ናቸዉ። እንዲሁም ትህነግ በአስተማማኝ ሁኔታ ገና አልተደመሰስም። በተለይም አመራሩ ስላልፈረሰና የትግራይ ህዝብም ሞቴን ከትህነግ ጋር ይሁን ከሚለዉ አዉዳሚ አመለካከትና ተግባሩ እስካልፀዳ ድረስ፣ ትህነግ ዛሬም ሆነ ነገ የአገራችን በተለይም የአማራ ስጋት ሁኖ የመቆየት አቅሙ ዛሬም እንዳለ ነዉ። በዚህ በኩል ለሰከንድም ቢሆን መዘናጋት አያስፈልግም። በዚህ በኩል በየትኛዉም ደረጃ የሚታይ መዘናጋት ካለ፣  አገሪቱን በተለይም አማራን ለባስ ዉድመት እንደማመቻቸት ይቆጠራል። ስለሆነም ለጦርነት ያለንን ዝግጅት የበለጠ ማጠናከርና አለመዘናጋት ዛሬም ያልተቋጨ  የቤት ስራችን መሆኑን አዉቆ መንቀሳቀስ ተገቢነት አለዉ።
ሌላዉ ወሳኝ እንደ ሀገር በተለይም ደግሞ እንደ አማራ ስለ ድህረ ጦርነት አጀንዳ ማንሳትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመር የግድ- የግድ ይለናል። ይሄን አጀንዳ የግድ ማንሳትና ወደተግባር እንድንገባ የሚያስገድዱን ቢያንስ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ:-
1. ይህ ጦርነት በድል መጠናቀቁ አይቀሬ ነዉ። ከጦርነት በሁዋላ ደግሞ የድህረ ጦርነት ተግባራት አይቀሬ ናቸዉ። ስለዚህ ስለ ድህረ ጦርነት ጉዳዮች ከወዲሁ ማሰብና መፍትሄወችን መተለም ብልህነት ነዉ። ይህ ሁኔታ ” ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥስ” ከሚል አባባል ያወጣናል። ይሄን አስቦ መንቀሳቀስ በጦርነት ሂደት ዉስጥም ተሁኖ እየታረሙ መሄድ የሚገባቸዉን ጉዳዮችም እያረሙ ለመሄድ ዕድል ይሰጣል።
2. በዚህ ጦርነት አብዛኛዉና በወረራ  ተይዘዉ የነበሩ የአማራና አፋር አካባቢወች ከወራሪዉና ዘራፊዉ  ሀይል ነፃ ሁነዋል። ስለዚህ እነዚህ የወደሙ አካባቢወች  መልሰዉ መገንባት ይኖርባቸዋል ማለት ነዉ። ይሄም ማለት በነዚህ አካባቢወች ቢያንስ በከፊል ድል ላይም ሁነን ቢሆን ስለ ድህረ ጦርነት አጀንዳ ማንሳት ብቻ ሳይሆን አጀንዳዉን መተግበር ግድ ይለናል ማለት ነዉ። አወ! በነዚህ አካባቢወች ጦርነቱ ያስከተለባቸዉን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለይቶ ለመፍትሄ መንቀሳቀስ ወቅቱ አሁን ነዉ እላለሁ።
በአጠቃላይ ወቅቱ ለአገራችን በተለይም ለአማራ ህዝብና መንግስት የጦርነትና የድህረ ጦርነት አጀንዳወች መሳ ለመሳ የሚሄዱበት ስለመሆኑ መግባባት ያስፈልጋል። ሁለቱም አጀንዳዎች LIVE  ናቸዉ። ስለዚህ ጦርነቱ በቅጡ ስላልተቋጨ በአንድ በኩል ስለ  ድህረ ጦርነት እሳቤና ትግበራ እየተነጋገርንና እየተገበርን   ፣በአንፃሩ ደግሞ ጠላት
የመንግስትን ባለህበት ፅና እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ  ትንኮሳ እንዳይፈፅም፣ከሞከረም ፣ በአስተማማኝ ሁኔታ መመከትና መደምሰስ የሚያስችለሰ ተግባራዊ  እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል። የመንግስት ወቅታዊ አቅጣጫም  ይህ ይመስለኛል።
እየተዋጋን የድህረ ጦርነት እሳቤና ትግበራን እዉን እናድርግ!!
Filed in: Amharic