>

የትግራይ ሕዝብ አሸባሪው ቡድን ዳግም ሕፃናትን ለጦርነት እንዳይማግድበት ማስቆም አለበት....!!!  (ዶ/ር ለገሰ ቱሉ)

የትግራይ ሕዝብ አሸባሪው ቡድን ዳግም ሕፃናትን ለጦርነት እንዳይማግድበት ማስቆም አለበት….!!! 

ዶ/ር ለገሰ ቱሉ


የትግራይ ሕዝብ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ዳግም ሕፃናትን በጦርነት እንዳይማግድ የሽብር ቡድኑን የጦርነትና የግጭት አባዜን ማስቆም ይኖርበታል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ገለጸ፡፡

ከሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች በይቅርታ እየተፈቱ መሆኑን ተመልክቷል፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ ትናንት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የመከላከያ ሠራዊቱ እንዳይገባ የወሰነው የትግራይ ሕዝብ በመጀመሪያው ዙር ያባከነውን የማስተዋል ጊዜ ዳግም እንዲያጤናው እና ራሱን ከአሸባሪው ቡድን ነጥሎ ለጥቅሞቹና መብቶቹ መከበር እንዲቆም ተጨማሪ ዕድል ለመስጠት ሲባል ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ አሸባሪው ሕወሓት ቡድን ዳግም ሕፃናትን በጦርነት እንዳይማግድ የሽብር ቡድኑን የጦርነትና የግጭት አባዜን ማስቆም ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የትግራይ ሕዝብ በርካታ ማኅበረኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ እንዳለ መንግሥት መገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሕዝባችን አንዱ አካል በመሆኑ እነዚህ ችግሮቹ እንዲፈቱለት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ነው ያሉት ዶክተር ለገሠ፤ የትግራይ ሕዝብ እነዚህ ጥቅሞቹ እና መብቶቹ እንዲከበሩ ከፈለገ በጦርነት ብቻ የመኖር ፍላጎትና ጥማት ያለውን አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን መታገል እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል::

የትግራይ ሕዝብ ከአሸባሪው ቡድን ነጻ ለመውጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴም መንግሥት ከጎኑ እንደሚሰለፍ አስታውቀዋል:: የትግራይ ሕዝብ ለግል ፍላጎቱና የሥልጣን ጥሙ ሲል ሕይወቱ እንዲመሰቃቀል ያደረገውን የሽብር ቡድን ድርጊት ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በጥብቅ መቃወምና መታገል መጀመር እንደሚኖርበት አመልክተው፤ የትግራይ ሕዝብ ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ እንዲመለስ፣ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹ እንዲፈቱና ዘላቂ ጥቅሞቹ እንዲረጋገጡ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል::

በተለይም የማኅበረሰቡ አባል የሆኑ ምሑራን የትግራይ ሕዝብ በአሸባሪው ቡድን እየደረሰበት ካለው ፈርጀ ብዙ ችግር እንዲላቀቅ ኅብረተሰባዊ ግዴታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፤ ለጥቂት የአሸባሪ ቡድን አባላት ጥቅምና የስልጣን ጥማት ተብሎ ልጆቹ ወደ ጦርነት መማገድ እንደሌለባቸው ገልጸዋል::

ከአሸባሪው ቡድን ነጻ በወጡ አካባቢዎች ተመሰቃቅሎ የነበረው ሕይወትና ሁኔታ ወደ መደበኛ ባህሪው እየተመለሰ እንደሚገኝ ዶክተር ለገሠ አመልክተው፤ በእነዚህ አካባቢዎች በየደረጃው ያለው የመንግሥት አስተዳደር እንደገና በአዲስ መልክ ተደራጅቶ በተሟላ መልኩ ወደ ሥራ መግባቱንና ለተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል::

አሸባሪው ሕወሓት ቡድን ለዳግም ትንኮሳና ጥቃት ዝግጅት እያደረገ ነው፤ ዳግም የአገር ስጋት እንዳይሆን ምን እየተደረገ ነው? የሚል ለዶክተር ለገሠ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል::የእሳቸው ምላሽም እርግጥ ነው፤አሸባሪው ቡድን መኖር የሚችለው በጦርነት ብቻ ነው፤ ጦርነት ከሌለ የትግራይ ሕዝብ ልጆቻችን የት ደረሱ፣ እንደ ኤሌክትሪክ ፣ውሃና መንገድ ያሉ የመሠረተ ልማቶች እንዲሟሉለት ጥያቄዎችን ማቅረቡ አይቀርም ብለዋል:: ከዚህ አኳያም የሽብር ቡድኑ ያለው ብቸኛው አማራጭ የትግራይን ሕዝብ አደናግሮ ለመኖር ጦርነቱን ማስቀጠል መሆኑን አመልክተው፤ በአሁኑ ጊዜ የሽብር ቡድኑ አከርካሪው ስለተመታና የመከላከያ ሠራዊታችንም በተጠንቀቅ ላይ ስለሚገኝ የሚያሰጋ ነገር አይኖርም ብለዋል::

በአስቸኳይ አዋጁ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ የተጠረጠሩ ሰዎችን የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ማዋላቸው አስታውሰው ፤እነዚህ ሰዎች ከተለያዩ ሽብር ቡድኖች ጋር አብረው መሥራታቸው አገርን እንደ መካድ የሚቆጠር መሆኑን አምነውና በድርጊታቸው ተጸጽተው ይቅርታ በመጠየቃቸው መንግሥት ጉዳዩን በሆደ ሰፊነት አይቶት ከትናንት ጀምሮ ከእስር እየተፈቱ መሆኑን አስታውቀዋል::

የቀሩትም እንደ ሁኔታው የጥፋት ደረጃቸው እየታየ በቀጣይ የሚለቀቁ እንደሚሆን ገልጸው፤ቁልፍ የችግሩ ተዋንያን የሆኑት ደግሞ ጉዳያቸው ተጣርቶ ለፍርድ ቤት የሚቀርብ መሆኑንም አመልክተዋል:: የመንግሥት ዓላማ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም አስፍኖ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ማስቻል ብቻ ነው ያሉት ዶክተር ለገሠ፤ ይህን የሚገዳደር ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ከሕግ ተጠያቂነት አያመልጥም ብለዋል:: ሕዝቡም እስካሁን የሚያደርገውን ድጋፉን እንደ ወትሮው ሁሉ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል::

Filed in: Amharic