>

"ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ....!!!' (አበበ ገላው)

“ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ….!!!’
አበበ ገላው

 

ከሁሉም በማስቀደም አንኳን ለብርሃነ ልደቱ ከእነ መላ ቤተሰብዎ በሰላም አደረስዎ ለማለት እወዳለሁ። ይቺን አጠር ያለች ደብዳቤ እንድጽፍልዎ ያነሳሳኝ ዋና ጉዳይ የሚከተለው ነው።
ኢትዮጵያ ከገባችበት ጥልቅ አገራዊ ቀውስ፣ ጦርነትና እልቂት ለማውጣት በአገራችን ብሄራዊ መግባባት ለማስፈን መንግስት እየወሰደ ያለው አንዳንድ እርምጃ ተገቢና ወቅታዊ በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባ እምነቴ ነው። በዚሁም መሰረት በእነ እስክንድር ነጋና በእነ ጃዋር መሃመድ የክስ መዝገብ ተከሰው በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ እስረኞች እንዲፈቱ መደረጉ ተገቢ መሆኑ ብዙም አያከራክርም የሚል እምነት አለኝ።
ይሁንና በተያያዥ ተሰብሰብው፣ አቅደውና ከፍተኛ ዝግጅት አድርገው ጥቅምት 24 2013 በውድቅት ለሊት በሰሜን ዕዝ ላይ የተቀናጀ ጥቃት እንዲሰነዘር ትእዛዝ በመስጠት በበርካታ ሺ የሚቆጠሩ የአገር መከላከያ አባላት ላይ ግድያ፣ ዘግናኝ ግፍ፣ የአካልና የስነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው የአንበሳውን ድርሻ የተጫወቱትን የአሸባሪው የህወሃት ከፍተኛ አመራር አባላት የሆኑትን እነ ስብሃት ነጋን መንግስት መፍታቱን ስሰማ የተሰማኝ ሃዘን እጅግ ጥልቅ ነው።
በእነዚህ ግልሰቦች ውሳኔ ምክንያት በህዝባችን ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍ ተፈጽሟል። ያም ሳያንስ በግለሰቦቹ ምክንያት አገራችን እስካሁን የጦርነት አረንቋ ውስጥ በመዳከር ላይ የምትገኝ ሲሆን ከመቶ ሺ በላይ ዜጎቻችን ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል። ሌሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአካልና የስነ ልቦና ጉዳት ሰለባ ከመሆናቸውም በላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምስኪን ወገኖቻችን ከቀያቸው በመፈናቀል ለችግር፣ ርሃብና ቸነፈር ሰለባ እንዲሆኑ ምክንያት ሆነዋል።
ከዚህም በላይ በበርካታ ሺ የሚቆጠሩ እናቶች፣ ህጻናትና አዛውንቶች ሰይጣናዊ መንፈስ በተጠናወታቸው የህወሃት ታጣቂዎች እንዲደፈሩና ለአካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ሰለባ እንዲሆኑ ምክንያት ሆነዋል። የግለሰቦቹ ተዘርዝሮ የማያልቅ ወንጀልና የሽብር ድርጊት ከማንም በላይ ለመንግስት ግልጽ ነው የሚል እምነት አለኝ።
በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ወንጀሎችን የፈጸሙና ወደፊትም ከመፈጸም ፈጽሞ የማይቦዝኑ ግለሰቦችን በዘፈቀደ መፍታት የህዝባችንን ጉዳት፣ ህመምና፣ ቁስል ፈጽሞ እያዩ እንዳላዩ ከማለፍ ወይንም ከማቅለል የማይተናነስ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት መሆኑን በሃቅ በመቀበል ውሳኔው በድጋሚ እንዲታይና ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን አይቶ እንዲወስን እንዲደረግ በተጎጂ ወገኖቻችን ስም እጠይቃለሁ። ከዚህም በተጨማሪ መንግስት በእርቅና ሰላም ስም የፍትህ ፈላጊውን ህዝብ ስሜትና ፍላጎቶች እንዲሁም የአገርን ደህንነት ከሚጎዳ ድርጊት መቆጠብ እንደሚገባው እንደ ዜጋ ለማስገንዘብ እወዳለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሆይ!
መደመር በሚል ርእስ ባሰተሙት መጽሃፍ ገጽ 108 የሚከተለውን ጽፈው ነበር። “አንድ መሪ የተከታዮቹን ስሜት ካልተረዳና የስሜቶቹን ምክንያትና የሚያስከትሉትን ውጤት ካልመረመረ የስሜት ልቀቱ ላሽቋል ወይንም የስሜት ድቀት ውስጥ ገብቷል ማለት እንችላለን። ህዝብና ተከታይ ሲከፋ ለምን እንደተከፋ መመርመር፣ የስሜቱን መጠንና አቅጣጫ ማጤን፣ እንዲሁም ስሜቱ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ መገንዘብ አስፈላጊ ነው።…የህዝብን ብሶትና ንዴት በወቅቱና በተገቢ ሁኔታ ያልተረዳ መሪ ህዝብን እየገዛ እንጂ እየመራ አይደለም።”
እኔም እርስዎ በራስዎ ብዕር ከጻፉት ቁም ነገር የተለየ ሃሳብ ባይኖረኝም ቃልዎ ከተግባር ጋር መጣረሱን አስተውለው የመንግስትዎን ውስኔ መልሰው ይመርምሩ። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ በቀልን ባይፈልግም ለዘመናት የተጠማውን ፍትህ ግን በፍርድ አደባባይ ማየትን እንደሚፈልግ አልጠራጠርም። ስለዚህም ይህ ውሳኔ የከፋ ጦስ ከማስከተሉ በፊት በጥሞና ተመርምሮ እንዲስተካከል ስል እንደ አንድ ፍትህ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ መጠየቅ እወዳለሁ።
ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን መንግስት ከፍተኛ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ኪሳራ ሊደርስብት እንደሚችል ፈጵሞ አያጠያይቅም። በመሆኑም ውሳኔውን መልሶ ማጤንና በአስቸኳይ መቀልበስ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ።
በተረፈ እንደ ታቀደው በጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ከክፍፍል ይልቅ ብሄራዊ መግባባት እንዲሰፍን ምኞቴን እገልጻለሁ።
Filed in: Amharic