እስክንድር ነጋ ከቃሊቲ መልስ በመድረክ የተናገረው፦
ጌጥዬ ያለው
በጣም በጣም አመሰግናለሁ። ለትህትና ብቻ አይደለም። በጣም አመሰግናለሁ። ንግግሬን የምጀምረው ራሴን በመውቀስ ነው። ይሄን ስብሰባ የጠራነው ትናንት ለዛሬ ረፋድ አምስት ሰዓት ነበር። የጀመርነው ግን ስድስት ሰዓት ነው። ለዚህ ጥፋተኛው እኔ ነኝ። ለትግል ስነ ምግባር (decipline) ወሳኝ ነው። ስብሰባ ላይ ሰዓት አክብሮ መገኘት የጥሩ ስነ ምግባር መገለጫ ነው። ድርጅቶች የሚሸነፉትም ከስነ ምግባር ጉድለት የተነሳ ጭምር ነው። ለዚህ ነው ራሴን የምወቅሰው።
በጋዜጠኝነት ሕንይዎቴ የመዝናኛ ጋዜጠኛ አልነበርኩም። ከፖለቲካው ጋር ቅርበት ነበረኝ። በዚህ የተረዳሁት ስነ ምግባር ወሳኝነት ያለው መሆኑን ነው። ለዚህ ነው ይቅርታ የምጠይቃችሁ።
ጥበብና ዲሲፕሊን ያለው ድርጅት ያስፈልጋል…!!!
እኔ ስለራሴ ለመናገር አልደፍርም። ይሄ የእኔ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ባህሪ ነው። “እኔ” ብሎ መናገርም አልተለመደም። ግን አንድ ተሞክሮ ላንሳ። እኔ በፕሬስ ውስጥ የጋዜጣ ድርጅቴን ስመራ የገነባሁት ጥሩ ነገር ዲሲፕሊን ነው። እኛ ጋ ጫት የሚቅም ጋዜጠኛ አይቀጠርም። ይሄ የመጀመሪያው ሕጋችን ነበር። ስኬታማ የሆንነውም ለዚህ ነው። ዲሲፕሊን አጉድየ ስገኝ እኔም መቀጣት አለብኝ፤ ይቅርታ መጠየቅ አለብኝ። ይሄ የድርጅታችን አሰራር መሆን አለበት።
ከዚህ በፊት ድክመቶች ብናሳይ መሪዎች ታስረዋል በሚል የጥፋት ማቅለያ ይሰጠናል። አሁን ግን መሪዎች ተፈተናልና ካለፈው የተሻለ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ከገጠሟት ችግሮች ተላቃ መቀጠል አለባት። ለዚህ ጠንክረን እንሠራለን። አዲስ አበባ ተኮር ፓርቲ የሆነው ለምርጫ ለመድስ በመንግሥት ተገደን ነው። ከዚህ በኋላ ግን በመላው ኢትዮጵያ የምንቀሳቀስ ሀገራዊ ፓርቲ እንሆናለን።
ባለፈው ጊዜ ፓርቲያችን ርዳታ ይዞ ሄዷል። ሁልጊዜ ግን እርዳታ እየያዝን አይደለም የምንሄደው። ጀግኖቹን እጅ ለመንሳት ነው የምንሄደው። በኢትዮጵያችን ጉዳይ ከሕዝብ ጋር ለመወያየት ነው የምንሄደው። ከፖለቲካ በላይ ኢትዮጵያን እንደምናስቀድም ለመንገር ነው የምንሄደው።
ኢትዮጵያን የምንገነባት በእያንዳዳችን ልብ ውስጥ ነው። መከላከያ መቀሌን ለቆ ወጥቶ ሕወሓት ደብረ ብርሃን ደርሷል። ጦርነቱ በድል ቢጠናቀቅ እንኳን ሌላ ዙር ጦርነት ይወለዳል። የኢትዮጵያን አንድነት ማስከበር የሚቻለው ግን በዴሞክራሲና ኢትዮጵያን እያንዳዳችን ልብ ውስጥ በመሥራት ነው።
አምስት የድርጅታችን አባላት አሁንም እስር ቤት ናቸው። የፓርቲያችን የግፍ እስረኛ እያለ እኛ እንቅልፍ የምንተኛ ከሆነ ስኬታማ አንሆንም። እያንዳዳችን እንደታሠርን አድርገን መታገል አለብን። የዛሬው ስብሰባ አንዱ አላማ ይህ ነው። ይህንን በሚመለከት ከሰኞ ጀምሮ የምንሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ። በሰላማዊ መንገድ እንሠራለን። ሌሎች ተፈተዋልና እነርሱም ነገ ይፈታሉ ብን ዝም አንልም። ይሄን ሓላፊነት ደግሞ ለሌላ ሰው መስጠት አልፈልግም። ራሴ ግንባር ቀደም ሆኘ እንሠራለን። ዋጋ የሚያስከፍል ከሆነም እኔ እከፍላለሁ።