>

"አጣዳፊው የፌልትማን መልዕክት፣ የአብይ መልስና የስብሃት መፈታት....!!!" (ሞሀመድ ሱሌይማን)

“አጣዳፊው የፌልትማን መልዕክት፣ የአብይ መልስና የስብሃት መፈታት….!!!”
ሞሀመድ ሱሌይማን

አሜሪካ በኢትዮጵያ ክፉኛ ተቆጥታለች። በዚች “ደሀ” የአፍሪካ ሀገር፣ በአለም መድረኮች ያጋጠማት ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈቶቿ አልተዋጡላትም። በፀጥታው ም/ቤት ከ 12 ጊዜ በላይ፣ በአፍሪካ አህጉር ለበርካታ ጊዚያቶች፣ ኢትዮጵያ ፍልሚያውን በበላይነት መወጣት ችላለች። ማዕቀባዊ ማስፈራራቶች ሳያንበረክኳት፣ የሚዲያዎቻቸው የተቀነባበረ ጩኸትም ሳይነቀንቋት በያዘችው አቋማ ፀንታለች። ከሁሉ በላይ ደግሞ በሞንታርቦ አዲስ አበባ እንደ ካቡል ተከባለች፣ እንደ ባግዳድም አብቅቶላታል ትርክታቸው ሊያስደነግጣት ሳይችል ውሀ በልቶታል። ኤምባሲዎች ዝጉ፣ የውጭ ሀገር ነዋሪዎች ልቀቁ የሚለው የበቀቀን ጩኸታቸው እንደ ገደል ማሚቶ በባዶ ሸለቆ ወድቋል።
አሜሪካኖች የመጨረሻው ማለትም አዲስ አበባ ተከባለች የሚለው ውሳኔያቸው ላይ በቀላሉ አልደረሱም። ውሳኔው እንደ ፈጣሪ ከሚተማመኑት ሲ.አይ.ኤ የመጣ ነው። በሲ አይ ኤ አሰሳ ላይ የተመረኮዘ final assessment ነበር። 4 ኪሎ በ2 ሳምንት ውስጥ በሕወሀት እጅ ይወድቃል፣ አዲስ አበባም ከፍተኛ የሚባለውን የደም መፋሰስ ታስተናግዳለች የሚለውን የደህንነት መ/ቤታቸውን ድምዳሜ አልተጠራጠሩም። ሳይሆን ቀረ እንጂ። በዚህም ኢትዮጵያ አሸነፈቻቸው። ይሄ ሽንፈት ከሁሉም በላይ ያበሳጫቸው አእምሮዋቸውንም ያሳታቸው ነበር። it was the trigger point for them. ምክኒያቱ ደግሞ ሁሉም ነገር መቋጫውን ሊያገኝ ነው ብለው ያሰቡበት ስለነበርና ስለከሸፈ ነው።
ጄፈሪ ፌልትማን ልምድ ያለው ብልህ ዲፕሎማት ነው። ጦርነቱ ከተጀመረ በኢትዮጵያ ቀላል ለማይባሉ ጊዜያቶች ተመላልሷል። ነገሮችንም መስመር ለማስያዝ ጥሯል። አልተሳካለትም። ከብዙ መመላለስ በኋላ ግን የችግሩን ቁልፍ አግኝቶታል። የትብታቦውን ቁጥርጥር ጫፍ መዞ መያዝ ችሏል። በሰላሙ ጎዳና ላይ በዋናነት የተጋረጠውን እንቅፋት ማንነት አውቋል። ሕወሀት እንደሆነም የኋላ ኋላ ተረድቷል። ፌልትማን ከዚህ በኋላ ነበር፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን የመቆምና የመወገንን ምልክቶችን ያሳየው። በሁለት የተለያዩ መድረኮች ሕወሃትን የነቀፉ ንግግሮች አድርጓል። ሕወሃት የገባበት ጦርነት እንደ 83 እንዳልሆነና ይልቅ ኢትዮጵያን ዳግም የመያዝና የማስተዳደር ህልማቸውንና ቅዠታቸውን ትተው፣ ወደ መሬት እንዲወርዱ ወደ ቀልባቸውም እንዲመለሱ አስጠንቅቋል።
ይሄ ግን በዋሽንግተን ለሚገኙት አለቆቹ ቀይ መስመርን እንዳለፈ አድርገው እንዲወስዱበት ሆኗል። በዚህ አቋሙ በአንቶኒ ብሊንከንና በሱዛን ራይስ ጥርስ ውስጥ ሊገባ ችሏል። ሕወሃቶችም በደጋፊና ተከፋይ የፈረንጅ ወያኔዎች በኩል ፌልትማንን ሲተቹት ሰንብተዋል። እንዲያውም አሜሪካኖች በኢትዮጵያ የደረሰባቸውን ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ሽንፈቶች በዚህ ሰው ላይ ማሳበብ ጀምረዋል። ሕወሃት ላይ በያዘው አቋሙ የተነሳ ለኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካንን አካሄድ ቀድሞ በማሳወቅ ወጥመዶችን እንዲሻገሩ ሲያስችላቸው ቆይቷል ብለው እንዲጠራጠሩት ሆኗል። አልፈውም በዚህ ደምድመዋል። ይሄ ነው የሚሉት ማስረጃ ባያገኙበትም። ከዚህ በኋላ ነበር ጄፈሪ ፌልትማን በሱዳን ለማስደረግ የቻለውን መፈንቅለ መንግሥትና ለውጥ በኢትዮጵያ ሊደግመው ባለመቻሉ ተተኪውን መፈለግ የጀመሩት። እሱን ሊተካው የሚችል ለስላሳና ለዘብተኛ ሳይሆን አጥባቂና ጉልበተኛ hardliner ማግኘት ችለዋል። ከነበረበት ጡረታ በራሱ በባይደን ወደ ሥራ እንዲመለስ ተነግሮት ሀላፊነቱን መቀበሉን የሚናገረው ፌልትማን፣ በዘጠኝ ወሩ ነበር ከሥራ ገበታው እንዲሰናበት የተደረገው። ቀኑም በኢትዮጵያ ገና ነበር።
ነገር ግን ለሐሙስ ዕሮብ ምሽት ፌልትማን የመጨረሻው የነበረውን የስልክ ንግግር ከጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ጋር ማድረጉን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳወቀ። ከአብይ ጋር ዘለግ ላለ ጊዜ እንዳወሩ ተነግሯል። ጥያቄው ያወሩት ምንድነው? ጄፈሪ ፌልትማን የመጨረሻ በሆነው መልዕክቱ ለአብይ ምን ነገረው? አብይስ ምን አለ? በገና ቀንስ ባልተጠበቀና ሁሉንም ግራ ባጋባ መልኩ የሕወሃት አመራሮች እንዴት ሊለቀቁ ቻሉ? የሚል ነው። ሁሉም የሚጠይቀው ጥያቄ ሆኗል።
የአሜሪካንን በኢትዮጵያ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ መንግሥት ቀድሞ leak በማድረግና በማሳወቅ የጠረጠሩትና አሜሪካ ለተሸነፈችበት ተደጋጋሚ ዲፕሎማሲያዊ ፍልሚያዎች ምክኒያት ነው ያሉት ፌልትማን፣ ለአብይ ከባድ ማስጠንቀቂያን በስልክ ነግሮታል። በቶሎ አንድ ነገር አድርጎ እየመጣበት ያለውን በመንገዱ እንዲያስቀር ሹክ ብሎታል። ባይደንና ብሊንከን በኢትዮጵያ ቆሽታቸው እንዳረረ አልደበቀውም። በሕወሃት ሽንፈትና በትግራይ ተከቦ መቀመጥ የተነሳ በኢትዮጵያ ላይ የመጨረሻ የሚሉትን ካርድ የመዘዙ መሆኑን አጫውቶታል። በውስጥ ሰዎቻቸውና በእጅ አዙር ሲያስፈራሩበት የነበሩትን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶች፣ ኤምባሲዎቻችንን በመጠበቅና ዜጎቻችንን ለማውጣት በሚል ሰበብ በጅቡቲ ባዘጋጇቸው ኋይሎች በኩል ለመተግበር ዝግጅታቸውን እንደጨረሱ በግልፅ ነግሮታል። ይሄን ሊያዘገይ የሚችል ያለውን ጉዳይም በቶሎ እንዲተገብር ለአብይ መክሮታል። ምናልባት የህወሃቱን ስብሃትና አንዳንድ ጉምቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን በበዓል አሳቦ ከእሥር ቤት ቢያወጣ፣ አሜሪካኖችን አወዣብሮ ውሳኔዎቻቸውን ወደ መከለሱ እንዲሄዱ ሊያስገድዳቸው ይችል ይሆናል ብሎታል። አብይ ያደረገው ይሄንን ነው።
ወዲያውም ሕጋዊነትን ባልተከተለ፣ በምንም ባልተጠበቀና ሁሉንም ባስደነገጠ መልኩ እሥረኞች እንዲለቀቁ ሆኗል። ጃዋርና እስክንድር ትፈታላችሁ ሲባሉ ጠበቆቻቸው እንኳ  ያልጠበቁትና ቀድሞ ያልተነገራቸው ውሳኔ በመሆኑ ግር ተሰኝተው እንደነበር ተናግረዋል። አጣዳፊ እርምጃ ነበር። እንዲያውም ጃዋር ውሳኔው ያልጠበቀውና ድንገተኛ በመሆኑ መውጣት ፈርቶ ሳይወጣ ቀርቶ እንደነበር ተዘግቧል።
ፌልትማን ከብሊንከንና ቡድኑ ጋር ሸካራ ግንኙነት እንደነበረውና። እነሱም እሱን ብቃት እንደሌለው አድርገው እስከመቁጠር ደርሰው እንደነበር ያለ ጊዜው ከሥራ ገበታው በማባረር አስመስክረዋል።
የሆነው ሆነና ፌልትማን ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደቆየው አሁንም ለአብይ  ከነብሊንከን ወጥመድ ማምለጫ ያለውን ነግሮታል። አብይም የገባበት ወጥመድ ከባድ እንደሆነና መፈናፈኛ እንደሌለው በመረዳቱ ለማስተንፈሻ ያህል ልቀቅ ያለውን እሥረኛ ለቋል። በትናንቱ ንግግሩ ጠ/ሚኒስትሩ “እየመረረን የዋጥነው ነው” ያለው ይሄን አስገዳጅ ውሳኔ ነው።
አብይ የህወሃትን ሰዎች በመፍታት ላይ የወሰደው ውሳኔ በምንም አንግል ትክክል እንዳልሆነ ይሰማኛል። በፍፁምም አይደለም! ውሳኔው ሀገርና ህዝብን የከዳና በኢትዮጵያዊያን ደምና አጥንት የቆመረ ብቻ ሳይሆን በወንጀል ህግ እንደ መሪ ተጠያቂ የሚያስደርገው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
የአሜሪካኖቹን አመጣጥ ስብሃትን በመፍታት ለማስቀረት ከመሞከር ይልቅ ምናልባት በሌላ መንገድ  ቢሞክር ሊሳካለት ይችል ይሆን ነበር። ግን ደግሞ ከጉዳዩ አጣዳፊነትና ነገሩ ከመጣበት ፍጥነት አንፃር ሌላ መንገድ ለመፈለግ ጊዜ ሳይኖረውና ሳያገኝ ቀርቶ ይሆናል። ይህ ሆኗል። ከዚህ ውጭ ሰዎቹ እርጅና ስለያዛቸው፣ በህመም ስላሉ፣ ቤ/ክርስቲያን እንዲያስቀድሱ ና እንደ አባቶቻችን ምህረት ለመስጠት ሲባል ነው የለቀቅናቸው የሚሉት ምክኒያቶቹ ውሸት ናቸው። ያው ለኔ ቢጤው አይነት ሰው to the lay man የሚቀርቡ ማለፊያ ሰበቦች ናቸው።
አሁን በልዩ መልዕክተኝነት የተተካው እንደ ፌልትማን አይሁድ የሆነው ዴቪድ ሳተርፊልድ ሲሆን፣ በአቋሙ አጥባቂ የሚባል ነው። በቱርክ (ድሮን) የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን አገልግሏል። በኢራቅ፣ በሊባኖስ፣ በሊቢያና በመካከለኛው ምስራቅ አጠቃላይ ለ 40 አመት በስራ ቆይቷል። አሁን በኢትዮጵያ ጉዳይ ተሿሚ ሆኗል። ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል? አብረን የምናየው ይሆናል።
Filed in: Amharic