>

"ከስድስት ተደጋጋሚ ስህተቶቹ ያልተማረው ህወሓት ለሰባተኛ ስህተት እየተዘጋጀ ነው......!!!" (ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ )

“ከስድስት ተደጋጋሚ ስህተቶቹ ያልተማረው ህወሓት ለሰባተኛ ስህተት እየተዘጋጀ ነው……!!!”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 

አሸባሪው ህወሓት በተደጋጋሚ ከሰራቸውና ከፍተኛ ኪሰራ ካስከተሉበት ስድስት ስህተቶች መማር ተስኖት አሁንም ለሰባተኛ ስህተት እየተዘጋጀ ነው ሲሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ከህወሓት ስድስት ስህተቶች እኛ ትምህርት ልንውሰድ ይገባል በሚል የአሸባሪው ቡድንን ስድስት ስህተቶች ዘርዝረው ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ አሸባሪ ቡድን ግን ከቀደመ ስህተቱ ሳይማር አሁንም ለሰባተኛ ስህተት የትግራይ ወጣቶችን ህይወት ለማስቀጠፍና አካል ለማጉደል በግራ በቀኝ ሊነካካን ይፈልጋል ብለዋል።
ለውጡ እንደመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ እንዲያደርግልን ጠይቀን ሕዝቡም በደሉን ረስቶ በዳዮቹን አቅፎ ለመኖር ሲሰናዳ ያን የለውጥ ጉዞ ተቀብሎና ደግፎ መቆም ያልቻለው ህወሓት የመጀመሪያውን ታሪካዊ ስህተት ስቷል። ያገኘውንም ይቅርታ እንዲያጣና ከፍተኛ ጥፋት እንዲደርስበት ሆኗል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ብልጽግና ሲመሰረት ሕወሓት ከራሱ ክብርና ስም ዘሎ ለትግራይ ሕዝብ ለታገለለት ሕዝብ ቢቆረቆር ኖሮ አንድ ከብልጽግና አለመውጣት ምናልባት የከፋ እንኳን እንደሆነ ለሁለት ተከፍሎ ከፊሉ ብልጽግና ጋር መቆየት ቢችል ኖሮ በርካታ ዜጎቹን መታደግ ይችል ነበር። ይህን ማድረግ ባለመቻሉ የሌብነት ጥጉ ተከፍቶ እንዲታይና የጥፋቱ ጥግ ተከፍቶ እንዲታይ ማድረግ ስላስቻለ ብዙ ነገር አበላሽቷል ብለዋል።
ሶስተኛው የቡድኑ ስህተት ደግሞ ያካሄደው የጨረቃ ምርጫ እንደሆነና ይህ ምርጫም ከፍኛ ኪሳራን ያስከተለ ዋጋ እንዳስከፈለው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሰሜን እዝ ጥቃት የአሸባሪ ቡድኑ አራተኛ ስህተቱ መሆኑን አብራርተዋል።
መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌ የወጣበትን ውሳኔ ተከትሎ ህወሓት  ወጡልኝ ብሎ ከሚከተል ደጋግሞ ቢያስብ ኖሮ የብዙ ወጣቶች ሕይወት ከመቀጠፍ ይታደግ ነበር ይህንን ባለማድረጉ ግን ለአምሰተኛ ጊዜ ስህተት ሰርቷል ብለዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ወደ ደሴ ያለው ጉዞ ቁልቁለት ሆነልኝ ብሎ ሳይዘጋጅ ሳያስብ ራሱን በበቂ ሳያደራጅ እድል ቢቀናው እንኳን እንዴት አድርጎ አገር እንደሚያስተዳድር ሀሳብ ሳይነድፍ እንዲሁ በእውር ድንብር መጓዙ የቡድኑ ስድስተኛው ስህተት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ስላሸነፍክ ብቻ ከግብህ በላይ መጓዙ ተገቢ እንዳልሆነ በእጅጉ የተማርንበትና በመልሶ ማጥቃቱ ከአፋርና ከአማራ ክልል ካወጣነው በኋላ ተጨማሪውን ጉዞ አያስፈልግም ያልነው የእውር ድንብር ጉዞ ውጤቱ አደገኛ መሆኑን  ከህወሓት ስለተማርን ነው” ሲሉም ነው ያብራሩት።
አሁንም ወደትግራይ ክልል ዘልቀን የማግባበት በርካታ ምክንያቶች ያሉን ቢሆኑም  አንገባም ብለን ከቆምን በኋላና ነገሩን በተለየ መንገድ ለማየት ጥረት እያደረግን ባለንበት በዚህ ወቅት  አሁንም ህወሓት አላረፈም ሲሉም ነው የተናገሩት።
“አሁንም ህወሓት በግራ በቀኝ ሊነካካን ይፈልጋል። ለሰባተኛ ስህተት የሚጓዘው ህወሓት በፍጹም ድል ማግኘት የማይችል እንኳን ቢሆን በወጣት የትግራይ ልጆች ላይ በህይወት የመቀጠፍና የመቁሰል አደጋ የሚያስከትል ስለሆነ ሰባተኛ ስህተቱ መስመር ስቶ ሳይሄድ መማር የሚችልበት እድል  መፍጠር የራሱ ቢሆንም እንኳ እንደባላንጣ አትንኩን እረፉ ለማለት እወዳለሁ። የነካካችሁን እንደሆነ በተለመደው መንገድ የከፋ ቅጣት ይደርስባችኋል” ሲሉ አስታውቀዋል።(ኢ ፕ ድ)
Filed in: Amharic