>

"የሰሞኑ የመንግስት ውሳኔ በብዙ መንገድ ስህተት ነው፤ ማን አለብኝ ባይነትም ተንጸባርቆበታል....!!!" (ግዛው ለገሰ)

“የሰሞኑ የመንግስት ውሳኔ በብዙ መንገድ ስህተት ነው፤ ማን አለብኝ ባይነትም ተንጸባርቆበታል….!!!”
ግዛው ለገሰ

ውሳኔው በህግ ማዕቀፍ የተደረገ አይደለም። የፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የህግ አግባብን እንኳን ሳይነደፍ የተወሰደ ውሳኔ ነው። ባይሆን ኖሮ በይቅርታ በምህረት ክሱ በማንሳት የሚሉ ምክንያቶች አይቀርቡም ነበር፡፡
የፖለቲካው ውሳኔ አወሳሰንና አተገባበር ከዴሞክራሲያዊ ባህል ይልቅ ማናለብኝነትን ያሳያል። የህዝብን የልብ ትርታ ያለተመለከተ፣ የአገሪቱን አስቸጋሪ ግዜ ያላገናዘብ፣ ኢትዮጵያዊነትን ለመታደግ እየተገነባ ያለውን ተነሳሽነትና አንድነት ያላሰላ ውሳኔ ነው። ጉዳዩን ለህዝብ እይታም ይሆን የህዝብን ስሜት ለመለካት ምንም ጥረት አልተደረገም። በዴሞክራሲ የሚያምን መሪ ወሳኔዎች የሚኖቸውን አንድምታ የውሳኔያቸው አንድ ቀመር አድረገው ያያሉ፡፡ ወሳኞቹ ምን ታመጣላችሁ? በሚል እንጂ ተጠያቂነትን፣ ግልፅነትን እንደ እሴት የወሰዱ አይመሰልም።
ሽምግልና እንደነበር ብዙዎቻችን የምናውቀው ሃቅ ነው። ነገር ግን ሽምግልናው መደረግ የነበረበት የህግ ሂደቱ ካለቀ በኋላ መሆን ነበረበት። የስራ አስፈፃሚው በህግ ሂደቱ ጣልቃ መግባት መብት የለውም። የፍርድ ሚንስትሩም ክሱ የሚያነሳ ከሆነ ተጠርጣሪዎችን ለመክሰስ በቅ ምክንያት የለኝም ብሎ ተጠርጣሪዎችን ይቅርታ ጠይቆ መሆን ነበረበት።
ውሳኔውን ያጀበው የ”ድል” ጋጋታ አገሪቷን አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገብና መከላከያ መቀሌን ሲይዝ የነበረው ስህተት ሊደገም እንደሚችል አመላካች ነው። በብዙ ውጊያዎች ኢትዮጵያ ብታሸንፍም ጦርነቱ አላለቀም፤ ዛሬ የህወሃት ካድሪዎች ራያ ላይ ድል እንደተቀናጁ እየገለፁ ነው። በዚህ ሰዓት ድል አልተቀናጀንም!!
የተፈጠረው አውድ የመንግስት አመራር ጦርነቱን ከህወሃት ጋር በድርድር ለመፍታት ሃሳብ እንዳለው ፍንጭ የሚሰጥ ነው። ይህ ደግሞ ብዙ ቅራኔውች ይፈጥራል። የባሰ ጦርነትም ይወልዳል።
ጥያቂው አመራሮች ይማራሉ ወይ? ፓርላማው ስራ አስፈጻሚውን ቼክ ያደርገዋል ወይ? ከአፋርን ከአማራ የተመረጡ የፓርላም አባላት በፓርላም የህዝብ ተወካይነታቸውን ለማሳየት በጉዳዮች ላይ ክርክር ይጠይቃሉ ወይ? ተቃዋሚ ፓርቲዎችስ?
የሰሞኑ ውሳኔ የፍትህን በፖለቲካ ውሳኔ መዳጥ ከማመልከት ባለፈ የተፈጠረውን አንድነት አናግቶታል። ጥያቄው ይህ የአንድነት መሸርሸር ያገግማል ወይስ ይባባሳል ነው። ከተፈቱት ሰዎችና ከውሳኔው ግድሌሽነት አገሪቷ ወደ አሳሳቢ ሁኔት አንዳትሻገር እፈራለሁ።
ግን ተስፋ አንቁረጥ፣ አንድ ስህተት ጅምሮችን አያስቁሙን፣ ግን ጥንቃቂ እናድርግ እንደራጅ!
Filed in: Amharic