>

የፌደራል መንግስት ህወሓትን “ያለበት ድረስ ሂዶ ማጥፋት አለበት...!!!”  (ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ)

የፌደራል መንግስት ህወሓትን “ያለበት ድረስ ሂዶ ማጥፋት አለበት…!!!” 
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ማዕከላዊ መንግስት ህወሓትን “ያለበት ድረስ ሂዶ ማጥፋት አለበት” ሲል አስታወቀ። ፓርቲው የኢትዮጵያ መንግስት የመከላከያ ሰራዊቱን ባለበት ጸንቶ እንዲቆይ ያስተላለፈውን ውሳኔንም ነቅፏል።

ባልደራስ ይህን ያለው፤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእስር ላይ የነበሩ አራት አመራሮቹ ከተፈቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ዛሬ ሐሙስ ጥር 5፤ 2014 በፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ዋነኛ ትኩረት የነበረው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ነው።

ፓርቲው “መንግስት ‘ምዕራፍ አንድ’ ያለውን ዘመቻ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሳያረጋግጥ ማቆሙ፤ ትልቅ አደጋ ያዘለ ነው” ሲል ስጋቱን ገልጿል። ህወሓት አሁንም የሀገሪቱን አንድነት ሊፈታተን በሚችል ወታደራዊ ቁመና ላይ ይገኛል” ያለው ባልደራስ፤ መንግስት “ዘመቻውን ያቆመበትን ምክንያት በተመለከተ በቂ ምላሽ አልሰጠም” ሲል ተችቷል። የፌደራል መንግስቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ “ንቀት እያሳየ ነው” ሲልም ነቅፏል፡፡

ባለፈው ሳምንት አርብ ከእስር የተፈቱት አቶ እስክንድር ነጋ፤ መንግስት “እከሌ ወሰን ጋር ሄጄ አቆማለሁ ማለት አይችልም” ሲሉ በፕሬዝዳንትነት የሚመሩትን የፓርቲያቸውን አቋም አሳውቀዋል። “ብልጽግና ይህን ሊወስን ይችላል። መንግስት ግን እንደመንግስት አማራጭ የለውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የገቡትን ቃለ መሃላ ማስጠበቅ አለባቸው” ሲሉ አቶ እስክንድር አሳስበዋል።

የመከላከያ ሰራዊት፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ከህወሓት ኃይሎች ባስለቀቃቸው አካባቢዎች ጸንቶ እንዲቆይ የኢትዮጵያ መንግስት ትዕዛዝ ያስተላለፈው ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ ነበር። መንግስት ውሳኔውን እንዲወስድ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል፤ የኢትዮጵያ መንግስትን እና መከላከያ ሰራዊቱን ከ“እኩይ ሴራ እና ወጥመድ ለመከላከል” እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

በዛሬው የባልደራስ መግለጫ የተነሳው ሌላው ጉዳይ እነ እስክንድር ነጋ በተፈቱበት ዕለት እንደ እነርሱ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ስድስት ህወሓት አመራሮች ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የእነዚህን የህወሓት አመራሮች ክስ አቋርጦ እንዲፈቱ መወሰኑን፤ ባልደራስ “የህግ የበላይነትን የጣሰ ውሳኔ” ሲል ገልጾታል።

ፓርቲው ክስ የተቋረጠላቸው ግለሰቦችን “የህወሓት የፖለቲካ እነ የጦርነቱ ዋነኛ ቀያሾች የሆኑ” ሲልም ጠርቷቸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት “የጤና እና የዕድሜ ሁኔታቸውን ከግምት በማስገባት” ክሳቸው እንዲነሳላቸው ያደረገላቸው የህወሓት ሰዎች፤ አቶ ስብሐት ነጋ፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አቶ ዓባይ ወልዱ፣ አቶ አባዲ ዘሙ፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር እና ወ/ሮ ኪሮስ ሐጎስ ናቸው።

የስድስቱ ግለሰቦች ክስ መቋረጡ “የፖለቲካም ሆነ የሞራል ተቀባይነት የለውም” ሲል በዛሬው መግለጫው ተቃውሞውን ያሰማው ባልደራስ፤ “ይህ ህጋዊነት ያልተላበሰ ውሳኔ ሀገሪቱን ግልጽ ለሆነ አደጋ አጋልጧል” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል። “የሰሞኑ የብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ፣ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የተነጸባረቀበትን የጸረ- ህወሓት ህዝባዊ አንድነት አቋምን ቀጣይነት የሚያሳጣ እና የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚያወሳስብ ነው” ሲል አክሏል።

በዛሬው የባልደራስ ጋዜጣዊ መግለጫ የፓርቲው አመራሮች ፍቺ ጉዳይም ተነስቷል። ለአንድ አመት ከስድስት ወር በእስር ላይ የነበሩትየፓርቲው አመራር አስካለ ደምሌ “ክሱ ተቋርጧል መባሉ አግባብነት የለውም። እኛ ነጻ ነን” ብለዋል። የፓርቲው የሴቶች አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አስካለ “ክሱ ተቋርጧል ሳይሆን፤ ‘ነጻ ናችሁ’ መባል ነው የምንፈልገው” ሲሉ የራሳቸውን እና የፓርቲውን አመራሮች አቋም አንጸባርቀዋል።

ሊካሄድ በዝግጅት ላይ የሚገኘው አገራዊ ምክክር በባልደራስ መግለጫ የተነሳ ሌላኛው አጀንዳ ነው። ፓርቲው በመግለጫው በምክከሩ የሚሳተፉ አካላት ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለባቸው ብሏል። “የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት ማስቀጠል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል” እና “በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ” በፓርቲው ያስቀመጣቸው ቅደመ ሁኔታዎች ናቸው።

ባልደራስ “ለአገራዊ ምክክሩ ይረዳሉ” ያላቸውን ምክረ ሃሳቦችም በዛሬ መግለጫው ላይ አቅርቧል። ፓርቲው ያቀረበው የመጀመሪያው ምክረ ሃሳብ፤ ምክክሩን ሁሉም ባለድርሻዎች በባለቤትነት የሚመሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚጠይቅ ነው። የምክከር ሂደቱ “ግልጽ፣ ተአማኒ እና ከገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ” እንዲሆን የሚለው ሌላኛው ነው። ሶስተኛው የፓርቲው ምክረ ሃሳብ የምክክር ሂደቱን ግልጽነት ለመፍጠር “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በታዛቢነት እንዲጋበዙ” የሚል ነው።

Filed in: Amharic