>

አባይ ወልዱ አራተኛውንም ነፍሱን ህወሀትን ለማዳን ይሰጣል.... !!! (መስፍን ማሞ ተሰማ )

አባይ ወልዱ አራተኛውንም ነፍሱን ህወሀትን ለማዳን ይሰጣል…. !!!
መስፍን ማሞ ተሰማ 

በዚያን አስጨናቂ ዘርፈ ብዙ ፀረ ህወሃት/ ኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት  የትግል ዘመን ስለ አባይ ወልዱ እንዲህ ተፅፎ ነበር፤ አባይ ወልዱ ሶስት ነፍሶች ቢኖሩት ሶስቱንም ህወሃትን ለማዳን ይጠቀምበታል እንጂ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚያጠፋው ትርፍ ህይወት አይኖረውም። እኔም እላለሁ፥ አባይ ወልዱ በቀዳማይ ህይወቱ ወንበዴ ነበር፣ በሁለተኛው ህይወቱ መንግሥታዊ ማፊያ ሆነ፣ በሶስተኛው ህይወቱ ደግሞ ጁንታ።
እነሆ በጁንታነቱ ህወሃትን ለማዳን ሰሜን እዝን ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ለማንበርከክ መቀሌ መሽገው ከናዚስት ህወሃታውያን ቀንደኛ ጓዶቹ ጋር ትግራይን ቀርቅበው በር ዘግተው ሲዶልቱ ከረሙ። ጊዜና ሁኔታን ጠብቀው የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊታችንን በሌሊት ፈጁ። እነሆ አምርረው በሚጠሏት ኢትዮጵያ ላይ የሲዖል ጦርነት ከፈቱ። ኢትዮጵያን ለማፍረስ በዘመነ ፋሽዝም ሆነ ናዚዝም ያልተፈፀም አረመኔያዊ ግፍ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ፈፀሙ። በወሎ በጎንደር በአፋር እግዚዖ ያስባለ ዘግናኝ ጭፍጨፋና ውድመት አደረጉ። ይህ ሁሉ የሆነው ከአዲስ አበባ ወጥተው መቀሌ በመሸጉባቸው ሶስት ዓመታት እነ አባይ ወልዱ (ከደብረ ፂዮን በፊት የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበረ ) ባቀዱትና በተደራጁበት ደግሞም ለተግባራዊነቱ የጋራ ትዕዛዝ በሰጡበት የበቀል ዘመቻ ማኒፌስቶ ነው !!! [ይህ ማኒፌስቶ በቅርቡ ይፋ ሆኖ እኔም ሰፋ ያለ ትንታኔ አዘል ዘገባ አቅርቤ አስነብቤያለሁ]
እነሆ በዚህ የህወሀት ክህደት በተፈጠረው እጅግ ፈታኝና መራር መስዋዕትነት በተከፈለበት ጦርነት በቁርጥ ቀን ልጆቿ የኢትዮጵያ አምላክ እጇ ላይ ከጣላቸው ቀንደኛ ናዚስቶች ስብሃትን ጨምሮ አንዱ አባይ ወልዱ ነው። እኒህ የክፍለ ዘመኑ እርጉማን በእነሱ የበቀል ማኒፌስቶ ያለቁት ኢትዮጵያውያንን አፈር አልብሰን ሳንጨርስ፣ የህሊናና የሰብዐዊነት ስብራት ያደረሱባቸው አያሌ የአማራውና የአፋር ወገኖቻችን ሰቆቃ ሳይጠግግ፣  አርባ ዓመት ወደ ሁዋላ የመለሱት የአማራውና የአፋር ከተሞችና መሠረተ ልማቶች ፍርስራሽ ገና ሳይፀዳ እነሆ የህወሀት የሲዖል ሠራዊት አለቆች ተጨማሪ ነፍስ በብልፅግና መንግሥት ተሰጥቷቸው ወደ ዘረፉት ንብረትና ቤታቸው ገብተዋል።
አሰደናቂው ብቻ ሳይሆን እጅግ መራርና ዘግናኙ ጉዳይ ደግሞ ተጨማሪ ነፍስ የታደጉበት ምክንያት ተብሎ በአደባባይ ከመሪ እስከ ሚኒስትሮች የተነገሩት ህሊናን አቁሳይ ልብን በጭካኔ ሸቅሻቂ ምክንያቶች ናቸው። “መንግሥት አረጋውያንን አስሮ እስር ቤት እንዲሞቱ አይፈልግም፣ ገዳም ገብተው ይኑሩ፣ ሰብዓዊነት፣ ምህረት፣ ይቅርታ ወዘተርፈ” ተብለው ናዚስቶቹ ከእስር ስለተለቀቁበት ምክንያት የተደረደሩት ሰበቦች ምን ያህል በዚህ የህልውና ጦርነት ውስጥ እንደ አንድ ሰው ሆኖ ከመንግሥት ጎንና ፊት የቆመውን ህዝብ በመንግሥታዊ መብረቃዊ የድማሚት ጥቃት መጠነ ሰፊ ጉዳትና ስብራት እንዳደረሱበት መንግሥትና የመንግሥት ሚኒስትሮች ለመገንዘብ እንኳንና ከዘግናኝ ዲስኩራቸው ለመታቀብ ዳተኞች መሆናቸው ከማሳዘን አልፎ ተስፋን ይፈታተናል።
አዎ እነ አባይ ወልዱ እንደሆን ንሰሀ ገብተው ገዳም አይገቡም። አዎ አባይ ወልዱ የተቸረውን አራተኛ ነፍስ ለህወሀት ህልውና ዳግም ለመሰዋት ያውላታል እንጂ ኢትዮጽያን ከናዚስት ህወሀት የሲዖል ሠራዊት አይታደጋትም። በነአባይ ወልዱ፣ በእነ ስብሃት ነጋና መሰል የህወሀት ናዚስቶች መፈታት ሰብዐዊነትም ሆነ ፍትህ፣ ዘላቂ ሠላምም ሆነ ዕርቅ ከኢትዮጵያ ተፃርሮ እንደ ድርጅትና እንደ ሀይል ዛሬም በሁለት እግሩ ከቆመው ከግፈኛውና ናዚስት ህወሀት ጋር ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ አፋርና አማራ እንደ ክልል ሠላም ሊኖራቸው አይችልም። ናዚስት የወያኔ መሪዎች ሲፈቱ የነበረኝ የፀና ተቃውሞ ውሎ ሲያድርም ጉዳዩን ባብላላሁትና የሚያሳምን ፍንጭም ሆነ ምክንያት በፈለግሁለት መጠን ምሬቴ ከመጨመር በቀር አልረገበም !!! ዛሬም የናዚስቶቹን መፈታት አወግዛለሁ !!! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ !!!
[ ፎቶ፥ ናዚስት የህወሀት መሪና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት በ2006 ዓ/ም ከሱዳኑ መሪ አለበሽርና ከኢትዮጵያ ጠ/ሚር ሀይለማርያ ደሳለኝ ጋር በመቀሌ በወያኔ ክብረ በዓል ላይ፤ የባንዲራዎቹን አቀማመጥ ልብ ይሏል – መማተ ]
Filed in: Amharic