>

“ወታደሩ ትግራይ ገብቶ የተዘረፈውን ንብረት እንደሚያስመልስ  ጠብቄ ነበር...!!!” (ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስት)

“ወታደሩ ትግራይ ገብቶ የተዘረፈውን ንብረት እንደሚያስመልስ  ጠብቄ ነበር…!!!”-

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር


ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ በደርግ ዘመነ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኋላም የመንግስት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ፡፡ የቀድሞው ባለስልጣን ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር አዲስ አበባ ወደሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ሌ/ ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ በኤምባሲው ቅጥር ግቢ 30 ዓመታት ከቆዩ በኋላ ተለቀው ወጥተዋል፡፡አል ዐይን አማርኛ ከቀድሞው ከፍተኛ ባለስልጣን ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡

አል ዐይን አማርኛ፡- በደርግ ዘመነ መንግስት ድርድር ይደረግ የሚከል ግፊት ነበር፡፡ ድርድሩ እንዴት ነበር?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- በወቅቱ ህወሃት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ስለዚህ ድርድር ከሻቢያ ጋር ተጀምሮ ነበር፡፡ ፋንታ ይህደጎ የሚባል የትግራይ ተወላጅና ትግራይ ውስጥ ያቆጠቆጠ ውንብድና ነገር አለ፤ እናም ይህ ጦር ወደ ኤርትራ ሲሄድ ደምስሶ ካልሄደ ወደፊት አድጎ አደገኛ ይሆናል ብሎ ሃሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ግን ይሄ ተቀባይነት አላገኘም በዛ ጊዜ ፤ አይ እሱ በቀላሉ ይጠፋል ተባለና ታለፈ፤ እንደተባለውም እያደገ ሄዶ አሁኑ ደረጃ ደርሷል፡፡ ያኔ ድርድር ተባለ ናይሮቢ ይሁን ተብሎ ነበር፤ እነሱ ከልብ ለሰላም የቆሙ ስላልሆኑ አልተሳካም፡፡ ከዛ በኋላ ነው ወያኔ እየጠነከረ የሄደው፡፡ ወያኔን ተሸክሞ አዲስ አበባ ያደረሰው ሻቢያ ነው፡፡

አል ዐይን አማርኛ፡- በደርግ በኩል ተደራዳሪው ማን ነበር ?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ጓድ አሻግሬ ይግለጡ ነበሩ፡፡

አል ዐይን አማርኛ፡- በወቅቱ ድርድር ያደረጉ አካላት ፍላጎት ምን ነበር ?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ሻቢያ ያነሳ የነበረው የመገንጠልጥያቄን ነው፤ እንገነጠልና ጥሩ ጎረቤት ሀገሮች እንሁን የሚል ነው፤ እኛ ደግሞ መገንጠልን አንፈልግም፡፡ እኛ ሀገርን የማስገንጠል ማንደቱም የለንም፤ አንድ ሆና የተቀበልናትን ሀገር እስከ ቀይባህር ድረስ ባለወደብ የነበረች ሀገር እንዲገነጠሉ ፈቅደን የባሕር በር የሌላት ሀገር ማድረግ ስልጣኑም የለንም፡፤ እናም፣ ህሊናችንም አይቀበለውም፡፡ለዚህ ነው ድርድር ያልተሳካው፡፡

አል ዐይን አማርኛ፡- ኢህአዴግ እንዴት አዲስ አበባን ሊቆጣጠር ቻለ?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ተረባረቡበታ፡፡ ሻቢያም ወያም አንድ ላይ ሆነው፡፡ ኦነግ ሕዝቡም ደግሞ ወደኋላ ደርግን እየጠላ ሄዶ ነበር በሚወሰደው እርምጃ፤ በሁሉም ነገር እየተባባሰ ሄደ፡፡ መጀመሪያ የተወደደውን ያህል የሚስጠላው ነገር ይሰራ ነበር ደግሞ ደርግ፡፡ ለምሳሌ የእህል ዋጋ በኩንታል 50 ይሁን ብሎ ወሰነ፡፡ ይሄ የሚደግፈውን ሰው ሁሉ ነው ያስከፋው፡፡ ነጋዴው፣ ገበሬው እንደልቡ ይሸጥ የነበረውን በዛ ብቻ ሽጥ ተባለ፡፡ ግን ደርግም ያንን ያደረገው የከተማው ሕዝብ ስለተቸገረ ነው ፤ስለዚህ ይህንን ሲያደርግ ደግሞ ገበሬው ደግሞ አኮረፈ፡፡ወያኔና ሻቢያ ከላይ እያጠቁ ሲመጡ ሕዝቡ እኮ በደንብ እየጨፈረ ፣ሆ እያለ ሰራዊቱ ምሽግ ይዞ እየተዋጋ አላዩ ላይ ይወጣል፤ ስንቱን ይፈጀዋል፡፡

አል ዐይን አማርኛ፡- አሁን ያለው ጦርነት መፍትሄው ምንድነው ይላሉ ?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- መፍትሄው ህወሃትን መደምሰስ ብቻ ነው፤ እሱ ካልጠፋ ምንም ሰላም አይኖርም ፤ህወሃት መጥፋትና መደምሰስ አለበት፡፡ ደግሞም ተደምስሶ ነበር፤ አሁን መጨረሻ ላይ በተወሰደ እርምጃ መሪዎቹ፣ ምናምኖቹ ተደረገ ፡፡

አል ዐይን አማርኛ፡- የህወሃት መሪዎች መፈታትን እንዴት አዩት ?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ይሄ እኔን በጣም ነው ያናደደኝም፣ ያስደነገጠኝም፡፡ እነዚህ ስንት ዘር ያጠፉ እነስብሃት ነጋ ይለቀቁ ሲባል መቸም በጣም በጣም ነው የተሰማኝ፡፡ እነሱ ካልተደመሰሱ በምንም አይነት ነገር ሰላም አይመጣም፡፡ ይሄው አሁን እኮ እየታዬ እኮ ነው ሲፈቱና ተለቀቁ ሲባል እነሱ እያጠቁ ነው እየተባለ አይደል፡፡ ስለዚህ እነሱ በጦርነት ተወልደው በጦርነት ያደጉ፤ በውንብድና ተወልደው በውንብድና ያደጉ ስለሆኑ ሰላም አያውቁም፡፡ የሚያውቁት መግደል፣ መዝረፍ ባለፈው ምንድነው የሰሩት የሚዘርፉትን እየዘረፉ ሌላውን እኮ እያወደሙ ነው የሄዱት፤ ሆስፒታሎችን፣ ክሊኒኮችን ማውደም ምንድው ትርጉሙ፣ በቀላሉ ጥላቻና የሴጣን ባህሪ ነው ያላቸው፡፡ የሚዘርፉትን ይዝረፉ የቀረውን ለምንድነው የሚያወድሙት ይህንን የሚደርጉት እንግዲህ በዘር ነው፤ በዘር ጥላቻ ሌላውን አንገት ለማስደፋትና ስነልቦናውን ለመግደል ነው፤ ግን ስነልቦናው አይሞትም ፡፡

አል ዐይን አማርኛ፡- ድርድር ይደረግ የሚል ነገር እየተወራ ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን ሃሳብ አለዎት?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- አይ ከማን ጋር ነው ድርድር ፤ከነሱ ጋር ምን ድርድር ያስፈልጋል፤ እነሱን መጨረስና ማስወገድ ነው እንጅ ድርድር አይሆንም፡፡ የምን ድርድር ምን ለማድረግ እነሱን መልሶ ስልጣን ላይ ለማምጣትና ለማካፈል ነው፤ ይሄ የሚሆን አይደለም፡፡

አል ዐይን አማርኛ፡- የኢትዮጵያ ሰራዊት ትግራይ እንዳይገባ መወሰኑን በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት ?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- እሱ እኔ ደስ አላለኝም፡፡ እንዳይገባ እዛ ይቆይ ሲባል በፍጹም ደስ አላለኝም፡፡ እኔ የምጠብቀው መቀሌ ድረስ ገብቶ በባለሙያዎች እየተነቀሉ የተወሰዱ የቴሌኮሙኒኬሽን፤ የኤሌክትሪክ ምሶሶዎች፣ የሆስፒታል ንብረቶች እናም ሌላም ሌላም ትልልቅ ሀብቶችን እንደሚያስመልስ ነበር፡፡ እነሱ እኮ አዋቂዎችን ልከው ነው በደንብ እየነቃቀሉ የወሰዱት፡፡ እነደብረጺዮንን እና ሌሎች የህወሃት መሪዎችን እጃቸውን ይዞ ለፍርድ እንደሚያቀርብ ነበር የጠበኩት፡፡ ነገር ግን ይሄ ቀረና እዛው ይቁም ሲባል እንዳውም ሌላ ማጥቃት ጀመሩ፡

አል ዐይን አማርኛ፡- የራያና የወልቃይት ጉዳይ ብዙ ጊዜ ሲያጨቃጭቅ ነበር፡፡ ቦታዎቹ ላይ ያለው ጭቅጭቅ ለምን ተፈጠረ ?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- ወልቃይት ያለምንም ጥርጥር ከጥንት ጀምሮ የጎንደር ግዛት የነበረ ነው፡፡ ወያኔ ወሮ ነው የትግራይ ክፍል ያደረገው፡፡ በግድ አማርኛ እንዳይናገር ፤ትግርኛ እንዲማር ሁሉ ሞክረው ነበር፤ ሕዝቡም አልተቀበለውም፤ አልተሳካም፤ አሁን ከእንግዲህ በምንም አይነት ወታደርም አያስፈልገውም፤ ሕዝቡ ብቻውን እነሱን ይቀጣቸዋል፤ ይሞክሩት፡፡ እና እሱ አሁንም ወደነበረበት ነው መመለስ ያከለበት፡፡ ራያም እንደዚሁ ነው፡፡ ራያንም ጠቅለው ነው፡፡

አል ዐይን አማርኛ፡- አሁን ስላለው ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ምን ይላሉ?

ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ፡- የኢህአዴግ ፌዴራሊዝም ጎጅ እንጅ ጥቅም የሌለው ነው፡፡ በዘር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ እኔ እንዳውም ወደፊት እንደ ድሮው ቢሆን ይሻላል እላለሁ፡፡

አል ዐይን፡- በጣም አመሰግናለሁ፡፡

Filed in: Amharic