>

"... ተቃርኖአችን ከሀሳብ እና ከሀሳብ ጋር ብቻ እንጂ ከስጋና ከደም አይሁን.... !!!" (ጎዳና ያእቆብ)

“… ተቃርኖአችን ከሀሳብ እና ከሀሳብ ጋር ብቻ እንጂ ከስጋና ከደም አይሁን…. !!!”
ጎዳና ያእቆብ

“የሽግግር መንግሥት ጥያቂው ቡድንl በሚል” ርዕስ ትላንት (January 13, 2022) በ Ethio360 ልዩ ፕሮግራም በሀብታሙ አያሌው የቀረበው ፕሮግራም ላይ (2፡01.01) አቶ ያሬድ ጥበቡ ከTMH ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ያቀረበውን ሀሳብ በኢትዮጵያ ህልውና ተቆርቋሪዎች ስብስብ (ኢህተስ) የቀረበው ሀሳብ በማጋባት ማቅረቡ ከጋዜጠኛነት ስነ ምግባርም (ethics) አንጻርም ይሁን እንደ አንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው የግለሰቡን ሀሳብ እንደቡድኑ ሀሳብ አድርጎና የሰነዱ አካል አስመስሎ የሰነዱን ሀሳብና አላማ misrepresent አድርጎ ማቅረቡ አሳዝኖኛል። በሰነዱ ላይ የተሳተፉ በርካታ ግለሰቦችን ክብር የሚነካ መሆኑ ተገማች ሆኖ ሳለ በዚያ ላይ የታየው ግድ የለሽነትን ለጊዜው ተወት አድርጌ ከሰነዱ ጭብጥ አንጻር ብቻ ቅሬታዎቼን አቀርባለሁ።
አቅርቦቱ ስህተት እንዳልሆነ ስላልጠፋኝ ነው ይህንን ጉዳይ በአደባባይ ላቀርበው የወሰንኩት። ስብስባችን የፓለቲካም ይሁን ምንም አይነት ድርጅታዊ ቅርጽ እንደሌለው ተደጋግመን የገለጽነው  ጉዳይ ስለሆና እንደ ሀብታሙ አይነት ብሩህ ጭንቅላት ያለው ጋዜጠኛ እንዲህ አይነቱ silly ስህተት ይሰራል ብል  በእውቀቱ የማደንቀውን ሰው ስላሳዘነኝ ብቻ አሳንሼ ላየው አልችልም።
ሀብታሙ አያሌው የግለሰብ ሀሳብ (እናም ሀሳቡን የመግለጽ መብቱን) ከስብስቡ አላማ ጋር ሁሌም እንደማይስማማ አቶ ልደቱ አያሌው «እንደኔ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ በዚህ ሰነድ ላይ የሰፈሩት ከግማሽ በላይ አይኖርም ነበር።» በቅርብ ከሀብታሙ አያሌው ጋር ባደረገው ውይይት ላይ በግልጽ እና በማያሻማ ቋንቋ ገልጾታል።
የግለሰብ ሀሳብ እና የድርጅት ሀሳብ ልዩነት እንዳለው ለሀብታሙ አያሌው በማስረዳት የማባክነው ጊዜ የለም። ምክንያት ብትሉኝ እንኳን ሀብታሙ አያሌው ማንም የሚያውቀው ወይም ሊያውቀው የሚገባ ያልተወሳሰበ ጽንሰ ሀሳብ ስለሆነ ነው። በኔ እምነት ቅንነት ብቻ ሳይሆነ ሀላፊነት የጎደለው እራስንም ትዝብት ውስጥ የሚከት  በመጀመሪያ ለራስ ክብር ካለመስጠት የሚመነጭ  willful misrepresentation of facts ነው።
ለምሳሌ  ስብስቡ የጋራ የሆነ ብቸኛ መገጫው በሆነው ሰነድ ላይ ስለ ሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ቀጣይት ምን ይላል? ለሚለው
የሽግግር መንግስቱ ዋና ዋና የስራ ሃላፊነቶች (ረ.4.) ላይ «በጦርነቱ ወቅት የተዳከመውን
(1) የአገሪቱን መከላከያ ሰራዊት
(2) ልዩ ልዩ የጸጥታ ተቋማት
(3) የተፋላሚ ወገኖችን ሰራዊትና
(4) የክልል ሃይሎችን
በሚያሳትፍ አግባብ እንደገና ተጠናክሮ እንዲቋቋም ማድረግ ይሆናል።»
የሚለውን ሳያነበው ቀርቶ አይደለም። «እንደገና ተጠናክሮ» ማለት እኔ በማላውቀው ቋንቋ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ይፍረሰ የሚል ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ባላውቅም ይህ ሰነድ በተጻፈበት በአማርኛ ቋንቋ ግን በፍጹም ለይፍረስ የሚቀርብ ሀሳብ እንኳን በሰነዱ ላይ አለመቅረቡ ግልጽና ግልጽ ነው።በዚህ ጉዳይ ላይ ማለትም አቶ ያሬድ ጥበቡ እንደግለሰብ የተናገረውን ንግግር ማብራሪያም ይሁን ማስተባበያ የመስጠት ሀላፊነቱ የአቶ ያሬድ ጥበቡ ነው። ነገር ግን «መከላከያ ሰራዊት ይፍረስና በህዋሃትና በኦነግ ቡድን ሀገሪቱን ይረከብ።»  የሚሉትንም አስተናግደናል በማለት ስብስቡ የማይወከልበትን እና መሰረተ ቢስ ክስ ነው። ሀገራዊ እብደት ውስጥ ባንሆን ኖሮ ይቅርታ ይጠየቅበት የሚያስብል ትልቅ misrepresentation  ነው።
ከስብስቡ ጋር ይሁን ከሰነዱ አላማ ጋር በምንም መልኩ የሚገናኝ እንዳልሆነም አቶ ሀብታሙ አያሌው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ለሱን ማብራሪያም ይሁን ማስተባበያ በመስጠት ጊዜ አላጠፋም። ከዚህ ቀደምም «የሽግግር ጊዜው የሚተዳደርበት ቻርተር የለውም።» በማለት በአደባባይ ቢናገርም እንደዚህ አይነቱ ስህተት ሰነዱን በአግባቡ ካለማንበት የመነጨ ይሆናል በሚል እርምት ቢሰጥበትም በአደባባይ ይህንን ያልኩት በስህተት ነው የሚል ሀላፊነትን የወሰደ እርምትም አልተደገም።
ሰነዱ በሽግግር ጊዜ የሚተዳደርበት ቻርተር እንዳለው ከአንድም ሁለት ጊዜ ተጽፏል የሚል ማስተካከያ እንስካሁን አልሰማንም። ተጠያቂነት እና ማስተካከያዮች አስፈላጊ የሚሆነው ለሁሉም ነው። አንድ ጋዜጠኛ እንደ አንድ ባለሞያ « መከላከያ ይፍረስና የህዋሃትና የኦነግ ብድን ሀገሪቱን ይረከብ።» ብሏል ሲል ከላይ ከሰነዱ ላይ ቀንጭቤ ያወጣሁንት ማንበብ ከመቦዘን አይደለም።
እራንስ ለተጠያቂነት ለማቅረብና fact check ለመደረግ ከተዘጋጀ ልብና ሞያዊ ዲሲፒሊንና ኩራት የሚመነጭ አይደለም። ሰነዱ እንኳን እንደዚህ አይነቱን የሰውን ስሜት ለመኮርኮር ተብለው ከሚሸጎጡ ትንንሽ ጉዳዮች ይቅርና በማንኛው ዝርዝር ይሁን ጥቅል ጉዳዮች ላይ ምላሽ የሚሰጥበት ነው። ሰነዱ እራሱን ችሎ መቆም የሚችል ነው። በዚህ ሰነድ ዝግጅት ላይ የተሳተፍን ሰዎችም እንደ ግለሰብም ይሁን እንደቡድን እንደዚህ አይነቱ gross  & reckless misrepresentations of fact ነቅሰን አውጥተን ስህተቱን እርቃኑን ማስቀረት የሚያቅተን አይደለንም። አረሙን ከስንዴው ጋር አብረን እንዳንነቅለው ስንል አብሮ ይደግ በሚል የወዳጅነት መንፈስ ዝምታን በመምረጥ እንጂ።
አሁንም ግለሰብን እና ቡድንን የመቀላቀል አዙሪቱ እንዳይቀጥል ይህንን የጻፍኩት ብቸኛ ተጠያቂና ባለቤት እኔ ጎዳና ያዕቆብ ነኝ። ግለሰቡ ነኝ። ይህ disclaimer ያስፈለገው ደግሞ ከላይ ያሰፈርኳቸው አስተያየቶች እና እርምቶች የሰነዱ አካል ተደርገው ነገ ከነገ ወዲያ ሌላ ፕሮግራም ላይ እንዳይጠቀሱ በማለት ነው። ቅንነት አንጣ። ተቃርኖአችን ከሀሳብ እና ከሀሳብ ጋር ብቻ እንጂ ከስጋና ከደም አይሁን። ከሆነ ግን እዚህም ቤት ስጋ አለ ብሎ ማሰብ ባይጠቅም አይጎዳም።
እርስ በርሳችን በአንድ ሰነድ ላይ ሀቀኛ ውይይት ማድረግ ከቸገረን እንዴት መንግስት እንደ መንግስት ሀቀኛ ውይይት ይጀምር ማለት እንችላለን? የሚለውን ሳስብ ሀገራችን ምን ያህል አደጋ ውስጥ እንዳለችና መፍትሄው ደግሞ ምን ያህል የራቀ መሆኑ ያሳስበኛል።
Filed in: Amharic