>

ጥቁር አማሮች...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

ጥቁር አማሮች…!!!

አሳፍ ሀይሉ

‹‹በዚያ በአሰቃቂው በክፉ ዘመን፣
የነፃነት ትግል እንዲያገኝ ብይን፣
ለተበደሉና አቅም ላነሳቸው፣
ጠበቃቸው ሆኜ ስለቆምኩላቸው፣
የማያስታውሰኝ የማይጠራኝ የለም፣
ነገም ከነግ ወዲያም ዛሬም ለዘልአለም፣››
        (- አሌግዛንደር ፑሽኪን)
… ስለ ጄነራል ሃይሌ ጥላሁን ከማንሳቴ በፊት ስለ ሌኒን አነሳስና አወዳደቅ በጣም ባጭሩ ላጫውታችሁ፡፡
የብአዴን 3ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ባህርዳር ላይ ከተካሄደ በሁዋላ በየፖለቲካ ድርጅቶቹ ስር ታቅፈው የነበሩ የሰራዊቱ አባላት የህወሃት ሰራዊት ማእከል ሆኖ በአንድ አካል እንዲዋሃዱ ተደረገ፡፡ ሰራዊቱ ሲዋሃድ የህወሃት ሰራዊት ኮር እንዲሆን በመደረጉ አማራ ታጋዮች ቅሬታ ያዙ፡፡ የኦህዴድ ታጋዮች በዝምታ ይመለከቱ ነበር፡፡ ዝምታቸውም ይበልጥ ጎዳቸው፣
 ‹‹የኦህዴድ ሰራዊት የበታችነት እየተሰማው ግዳጁን በትክክል አይወጣም›› ተብለው ተገመገሙና በቅድሚያ እንደ ጨው ተበተኑ፡፡ ከኦህዴድ ይልቅ በውህደቱ ተጠቃሚ የነበሩት የህወሃት የሰራዊት አባላት ቅሬታ ነበራቸው፡፡
 ‹‹ደርግን ለመጣል በዋነኛነት የታገልነው እኛ ሆነን ሳለ፣ እንዴት የሃላፊነት ቦታዎች ለአማራና ለኦሮሞ ይሰጣል›› ሲሉ ቅሬታቸውን ገለፁ፡፡
ብአዴኖች ከኦህዴድ የተሻለ ጉልበት ነበራቸው፣
‹‹ለህወሃት ቁምጣ መልበስ ያስተማረው ኢህአፓ ነው፡፡ ሊመፃደቁብን አይገባም፡፡ እኛም ታግለናል፡፡ ስለዚህ የህወሃት ሰራዊት ኮር ሆኖ እኛ ማሟያ እንድንሆን መወሰኑ ፍትሃዊ አይደለም›› ሲሉ ጅራፋቸውን አጮሁ፡፡
ይህን መሰል ማጉረምረም በመበርከቱ በየብሄር ድርጅቱ ውይይትና ግምገማ እንዲደረግ ተወሰነ፡፡ የህወሃት ካድሬዎች ወደ መቀሌ፣ አማራ የሆኑ የመከላከያ አባላት ወደ ባህርዳር ተጠሩ፡፡ ኦህዴዶች ደብረዘይት አየር ሃይል ግቢ መሰብሰባቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ስብሰባውን የመሩት አባዱላና ኩማ ነበሩ፡፡ በስብሰባው መዝጊያ ላይ መለስ ተገኝቶ፣
 ‹‹ግኡዝ አትሁኑ! ግኡዝ አካላችሁ ብቻ ከኛ ጋር መሆኑ ይሰማናል፡፡ የግኡዝ አካል እጥረት የለብንም፡፡ ታንክና አውሮፕላን አለን፡፡ ተወልዶ፣ በልቶ፣ የሚሞት አሳማ ብቻ ነው፡፡ ታሪክ ስሩ! የሰው ልጅ ታሪክ ሰርቶ ማለፍ አለበት›› ሲል አሽሟጥጦ ተመለሰ፡፡
አማሮቹን የሰበሰቡት በረከትና አዲሱ ነበሩ፡፡ በታዛቢነት ደግሞ ጄኔራሎእ ሁሉም እንዲገኙ ተደረገ፡፡ ሳሞራ፣ አባዱላ፣ ባጫ ተካፍለዋል፡፡ ከጄኔራሎች በስብሰባው የተካፈለ ብቸኛ አማራ ሃይሌ ጥላሁን ነበር፡፡ ካሳ ደሜና አበባው የተባሉት ጄኔራሎች አማራን ወክለው በስብሰባው ላይ ቢገኙም አማራ አልነበሩም፡፡
ገለፃው እንደተለመደው ከተካሄደ በሁዋላ የውይይት መድረክ ተከፈተ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ሌኒን ቆፍጠን ብሎ ከመቀመጫው የተነሳው፡፡ ከውይይቱ ርእስ አፈንግጦ እንዲህ ሲል በረከትን አፋጠጠው፣
‹‹በረከት! አንድ ያልገባኝ ነገር አለ!›› ሲል ነበር የጀመረው፣ ‹‹…. ሁላችንም እንደምናውቀው ከብአዴን አመራር አባላት መካከል ጄኔራል ሃይሌ ጥላሁን ብቻ ነው አማራ፡፡ ሌሎቻችሁ አማራ አይደላችሁም፡፡ በረከት ስምኦን! አንተ ራስህ ኤርትራዊ ነህ! አዲሱ ለገሰ ኦሮሞ! ተፈራ ዋልዋ ደቡብ ነው! ታደሰ ጥንቅሹ ትግራይ! አመራሩ አማራ ሳይሆን እንዴት ነው በአማራ ጉዳይ እዚህ የምንነጋገረው? …
‹‹አባዱላና ሳሞራስ እዚህ ስብሰባ ላይ ምን ያደርጋሉ? ይሄ የአማሮች ስብሰባ ነው ከተባለ አማራ ያልሆኑ ከዚህ ስብሰባ ይውጡ! ወይ ደግሞ እንደ ቀድሞአችን ህብረብሄራዊ ሆነን ከቀጠልን ልትመሩን ትችላላችሁ፡፡ ኢህዴን ‹ብአዴን› ተብሎ የአማራ ድርጅት ሆኖአል ከተባለ፣ ይህ ስብሰባና አጀንዳውም የአማሮች ከሆነ ግን ስብሰባው በአማሮች መመራት ያለበት ይመስለኛል! ለዚህ ጥያቄ መልስ እፈልጋለሁ…››
አዳራሹ በጭብጨባ ጦፈ!!
እንደተለመደው ጫጫታ!! ብአዴኖች መሪ ካገኙ አይቻሉም፡፡ ለአመፅ በጣም ቅርብ ናቸው፡፡ እንደ እንግሊዞች አባባል ሻይ ብርጭቆ ውስጥ ማእበል ያስነሳሉ፡፡ ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ደግሞ ፈጥነው ሲበርዱና ሲከፋፈሉ ይስተዋላል፡፡
ሌኒን የለኮሰው አመፅ ወዲያውኑ ታፈነ፡፡
በረከት መድረክ ከያዘ ተሰብሳቢውን ርስበራስ አለያይቶ ሾልኮ የመውጣት ችሎታው የተጨበጨበለት ነው፡፡ የንግግር ስልቱም ‹‹ሲሞቅ በሹካ›› አይነት ነው፡፡ እና ያን ቀን ‹‹ሌኒን›› የተባለውን ታጋይ ላቀረበው አደገኛ ጥያቄ ‹‹የስምኦን ልጅ በረከት›› ስሜት የሚነካ ምላሽ ሰጠ፡፡ አዳራሹን በሞሉት ታጋዮቹ ፊት እንባ ተናነቀው፡፡ ለ20 ደቂቃ ያህልም ተናገረ፡፡
 ‹‹ምነው ይህችን ቀን ባላየሁዋት ኖሮ!›› ሲል እንደ ወጋየሁ ንጋቱ ተወነ፡፡ እያለቃቀሰ እንዲህ አለ፣
‹‹ምነው ይህችን ቀን ባላየሁዋት ኖሮ? ያኔ በረሃ ላይ ስንታገል ምነው የስልጣን ጉዳይ ሳይነሳ ቀረ? ምነው ኤርትራዊነቴን ያኔ ሳታነሱ ቀራችሁ? የወጣነው ተራራ፣ የወረድነው ቁልቁለት ተረሳ? ‹ያልተንበረከክነው› እያልን እየዘመርን ጓዶቻችንን አፈር የምናለብስበት በእነዚያ ዘመናት ምነው የኔ ኤርትራዊነት ሳይነሳ ቀረ?››
እንዲህ ሲል ማስፈራሪያ ቢጤ ደሞ አከለባት፣
‹‹ከእረኛነት እያነሳን አማራ ያደረግናችሁ እኛ አይደለንም እንዴ? አማራነታችሁን የት ታውቁት ነበር?››
መልሶም ንግግሩን በመግቢያው አረፍተ ነገር ቋጨ፣
‹‹ምነው ይህችን ቀን ባላየሁዋት ኖሮ?››
በረከት እንባውን ቸፍ አድርጎ፣ ብሶቱን ሲያንተከትከው አንዳንድ ሆደ ቡቡዎች በመሃረም አይኖቻቸውን ሲያባብሱ ታይተዋል፡፡ ውይይቱ ቀርቶ አዳራሹ የሃዘን ቤት ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ አገጩን መዳፉ ላይ ያስደገፈው ይበዛ ነበር….
አይ አበሻ!? እኛ አበሾች መቼም የዋህ ነን፡፡ ሰው ሲያለቅስ አያስችለንም፡፡ ቁጣችን ከምኔው በርዶ፣ ፕሮፌሽናል አስለቃሽ የምንሆንበትን ፍጥነት ለራሳችንም አናውቀው፡፡ አንዳንዱማ አንዴ ለቅሶ ከጀመረ ሟች አያቱን ወይም አማቹን እያስታወሰ ለቅሶውን በዚያው ይቀጥልበታል፡፡
እና ያን ቀን በረከት አስተዛዝኖም አስፈራርቶም አጀንዳውን አስቀየረ፡፡ የበረከት ኤርትራዊነት አጀንዳው በዚህ ከተዘጋ በሁዋላ ወዲ ስምኦን የመድፉን መሪ፣ ‹‹ብቸኛ አማራ!›› ወደተባለው ወደ ጄኔራል ሃይሌ አዞረበት፡፡
‹‹የብአዴን አባላት ጠባቦች አይደሉም፡፡ ከሁዋላ ሆኖ ያሳሳታቸው መኖር አለበት፡፡ ሃይሌ ጥላሁን ‹አማራ እኔ ብቻ ነኝ እያለ ቀስቅሶአል› ተባለ፡፡ ስብሰባው ከእንባ ወደ ቁጣ ዞረ፡፡ ጄኔራል ሃይሌ ጥርስ ውስጥ ገባ፡፡ የጄኔራል ሃይሌ ይቆይልንና የሌኒን ፍፃሜ ምን እንደሆነ ልግለፅላችሁ፡፡ ባጭሩ ሌኒን የባድመ ውጊያ ላይ ተገደለ፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነበር…
ሌኒን 300 የወታደር ሃይል ያላት ጦር መሪ ነበር፡፡ ሌኒን የሚመራት የሻለቃ ጦር ኢላላ የተባለ ቦታ ላይ የማጥቃት ግዳጅ ተሰጣት፡፡ ሌኒን ሶስት ጊዜ ያህል የታዘዘውን ለመፈፀም ሞክሮ ነበር፡፡ የተሰጠው ግዳጅ ግን የማይቻል አይነት ነበርና ሳይሆንለት ቀረ፡፡ የሰው ሃይሉ ተመናምኖበት ሳለም ለአራተኛ ጊዜ እንዲያጠቃ አዘዙት…
በዚሁ ቀውጢ ደቂቃ ይኸው ሁኔታ ደምበ ገዳሙ ከተባለ የማዘዣ ቦታ ላይ ለነበረው ለጄኔራል ሳሞራ ሪፖርት ይደረግለታል፡፡ ሌኒን ይመራው ለነበረው የሻለቃ ጦር የተሰጠው ግዳጅ አለመሳካቱ ለጄኔራል ሳሞራ ሪፖርት ሲደረግለት አራት ከፍተኛ መኮንኖች ከሳሞራ ጋር አብረውት ነበሩ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ይባላል፡፡
ሳሞራ፣ ‹‹ሌኒንን ግደሉት!›› ብሎ ትእዛዝ ሲሰጥ አብረውት የነበሩት አራቱም መኮንኖች ሰምተውታል፡፡
ሳሞራ ሌኒን እንዲገደል ትእዛዙን የሰጠው ከወታደራዊ የቅጣት ደንብ ውጭ ሲሆን፣ በመከላከያ ሚኒስቴር የቅጣት ደንብና ህግ ውስጥ ወታደሮች በዚህ መንገድ እንዲረሸኑ የሚፈቅድ አንቀፅ አልነበረም፡፡
ሌኒን እንዲገደል ትእዛዝ የተላለፈው ለወዲ እምበይተይ (ጄኔራል ሃይለስላሴ ግርማይ) እና ለጄኔራል አበባው ታደሰ ነበር፡፡ ትእዛዙ ሲተላለፍ በወቅቱ የመድፈኛ አስተባባሪ የነበረው ኮሎኔል ገመቹ አያና እዚያው ነበር፡፡ ትእዛዙን መስማቱንም አረጋግጦልኛል፡፡
ጄኔራል አበባው ወደ ሌኒን የበላይ አለቃ (አርባእተ አይኑ ይባላል) ደውሎ ሌኒን እንዲገደል ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ በዚያች ደቂቃ ደግሞ አርባእተ አይኑ ሌኒንን በወታደራዊው የሬዲዮ መገናኛ መስመር ላይ ሊያገኘው እየሞከረ ነበር፡፡ ሌኒን በበኩሉ ለአራተኛ ጊዜ ጉብታዋን ለመቆጣጠር በቀለጠ ውጊያ መሃል ነበር፡፡
‹‹በመጨረሻ የሌኒንን ሬዲዮ ሌላ ወታደር ተቀብሎ ለአርባእተ አይኑ መልስ ሰጠ፡፡ ሬድዮኑን የተቀበለው ወታደር ሌኒን በውጊያው ላይ መሞቱን በኮድ ለአርባእተ አይኑ ገለፀለት፡፡ አርባእተ አይኑ ይህንኑ የሌኒንን መሞት ለአበባው ሪፖርት አደረገ፡፡ አበባው በተመሳሳይ መንገድ፣ ‹‹ሌኒን ቀደም ብሎ በውጊያው ላይ ሞቶአል›› ሲል ገለፀለት፡፡
በርግጥም ከሳሞራ፣ ከበረከት እና ከአበባው ጋር መግባባት ያልነበረው ሌኒን ከሚመራቸው ወታደሮች ጋር በውጊያው ላይ ሞቶ ነበር፡፡ አንድን ሰው ሁለት ጊዜ መግደል አይቻልምና የሳሞራ ትእዛዝ ሳይፈፀም ቀረ…
በሰላም ወቅት ጥርስ የሚነከስባቸውን ወታደሮች፣ በውጊያ ወቅት ወደ አስቸጋሪ ውጊያ እንዲገቡ በማድረግ የማስወገዱ ዘዴ በሃገራችን በጣም የተለመደ ነው፡፡ በደርግም ሆነ በጃንሆይ ዘመን ሲሰራበት ቆይቶአል፡፡ ሌኒን ግን ሃገሬ ለሚላት ሃገር ከሞተላት በሁዋላ ሞት የተፈረደበት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ጀግና ወታደር ሳይሆን አይቀርም፡፡
ሌኒን ላይ ተላልፎ የነበረው የሞት ፍርድ በቀጥታ ከበረከት ጋር የተያያዘ ነው ለማለት የሚያበቃ ማስረጃ የለኝም፡፡ ሌኒን በደፋር ተናጋሪነቱና የዘር መድልዎን በመቃወም ጠባዩ ግን ጥቁር አማሮችና የህወሃት ወታደራዊ አዛዦች ጥቁር መዝገብ ላይ አስፍረውት መቆየታቸው ግልፅ ነበር፡፡
(የሌኒን አስከሬን በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ከዋለ በሁዋላ መኮንን መሆኑን ሲያውቁ ኪሱን ፈትሸውት ነበር፡፡ ሌኒን ለእጮኛው የፃፈላትን ያልተላከ ደብዳቤ ያገኙ ሲሆን፣ ያንን ደብዳቤም በኤርትራ ሬዲዮ አንብበውታል፡፡)
የሌኒን እጮኛ እዚያው ግንባር ደምበ ገዳሙ ከተባለ ቦታ ላይ የሰራዊት ሃኪም ነበረች፡፡ በጣም ቆንጆ ልጅ መሆኗን ሰምቻለሁ፡፡ ህይወት ትባላለች፡፡ ሌኒን ለህይወት የፃፈላትን ደብዳቤ የኤርትራ ሬዲዮ ማንበብ ሲጀምር ህይወት ቁስለኞችን እየረዳች ነበር፡፡ ሬዲዮ ይከታተሉ የነበሩ ቁስለኞች ጠርተው የሌኒንን ደብዳቤ እንድትሰማ ሲያደርጓት፣ ጩኸቷን ለቃ፣ ራሷን ስታ ወደቀች ብለው ነግረውኛል፡፡
ወጣት ደራስያን ሆይ!
የሌኒን እጮኛ ዛሬም በህይወት አለች፡፡ ሃገር ውስጥ መግባት ቢፈቀድልኝ ኖሮ ያቺን የጀግና ጓደኛ ፈልጌ አገኛት ነበር፡፡ የኔን ብእር ይዛችሁ፣ ፈልጋችሁ ታገኟት ዘንድ አደራ እላችሁዋለሁ፡፡ አግኟት፡፡ እናም ይህን የዘመናችንን ትራጀዲ ጥሩ አድርጋችሁ ተርኩልን፡፡
በኔ በኩል አልቻልኩም እንጂ የሌኒንን ሙሉ ስምና የህይወት ታሪክ በጨረፍታም ቢሆን እዚህ ማስፈር ነበረብኝ፡፡ መረጃዎች አልተሟሉልኝም በሚል ይህን ታሪክ አፍኜ መያዙ ግን ሃጢአት መስሎ ስለተሰማኝ የማውቀውን ያህል ፅፌላችሁዋለሁ፡፡
ብአዴን ውስጥ የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ሊባሉ የሚችሉ ሶስት አማራ ጄኔራሎች ብቻ ነው የነበሩት፡፡ ተፈራ ማሞ፣ አሳምነው ፅጌና ሃይሌ ጥላሁን፡፡ ሁለቱ ጄኔራሎች ከግንቦት7 ጋር በተያያዘው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተይዘው ወደ ወያኔ ማጎሪያ ተልከዋል፡፡ አበባው ታደሰ አገው ነው ቢባልም ግማሽ ጎኑ ግን ከትግራይ ነው፡፡ ሆኖም እንደ አማራ ወኪል ሲታሰብ ቆይቶአል፡፡
ይህን ምእራፍ በምፅፍበት ወቅት በተረጋገጠ አማራነት ሊጠቀስ የሚችል ጄኔራል ቢኖር ዘውዱ እሸቴ ብቻ ነው፡፡ እሱም ቅፅል ስሙ፣ ‹‹ጄኔራል እሺ!›› ሆኖአል፡፡ ‹‹ለተጠየቀው ጥያቄ ሁሉ እሺ! ይላል፣ ግን አይፈፅመውም›› እያሉ ያሙታል፡፡
ይህን መኮንን ደርግ ሳይወድቅ ጀምሮ አውቀዋለሁ፡፡ በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ ‹‹ሰው መግደል ሃጢያት ነው›› ብሎ የሚያምን ንፁህ የእግዚአብሔር ሰው ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ማንኛውንም አለቃ በጣም ያከብራል፡፡ ‹‹አለቃ ሊሳሳት ይችላል›› ብሎ አያስብም፡፡
ሰላምተኛና ሳቂታ ነው፡፡ እንደ ሴት ጥርስ ችምችም ያሉ፣ አገዳ ማኘክ የማይችሉ መስታወት የመሰሉ ንፁህ ጥርሶች አሉት፡፡ ጥርሶቹን ብዙ ጊዜ ለሳቅ አገልግሎት ይጠቀምባቸዋል፡፡ እንደተኮረኮረ ሰው ሲስቅ የሚውል ጄኔራል እንዴት አድርጎ ወታደሮችን ሊመራ ይችላል?
ዘውዱ ከደግነቱ ብዛት መቆጣት አይሆንለትም፡፡ እና ጄኔራል ዘውዱ እንኳን መፈንቅለ መንግስት ሊሞክር፣ ባዶ ዙፋን ቢያገኝ ቁጭ አይልበትም፡፡ ምንቸግሮት? እግዜር ሲፈጥረው ዘውድ ጭኖለታል – ዘውዱ!
በተቀረ ከጄኔራል መአረግ በታች የሚገኙ አስቸጋሪ አማራ መኮንኖችና በድርጅት ስራ ላይ ያሉ ካድሬዎች ሁሉ እየታፈኑ አድራሻቸው ወደማይገኝበት አለም በተለያየ ዘዴ ተልከዋል፡፡ ፀጋ ሞልቶ የተረፈውን የሁመራ፣ የወልቃይት፣ የዳንሻና የራያ የእርሻ መሬቶች ለህወሃት ያስረከቡት እነዚሁ ጥቁር አማሮች ናቸው፡፡
የአማራ ክልል መሬት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እየተቆረጠ በመወሰዱ ጥያቄ ያነሱ ታፍነው ጠፍተዋል፡፡ እነ አሻግሬ በለው፣ ስማቸው ጎበዜ፣ መንግስቱ ተበጀ ዛሬ የት ናቸው? ይህን የሚመልስ ጀግና የወያኔ አመራር ከቶ ማነው?
ከላይ የጠቀስኳቸው ሰዎች፣ ‹‹አማራውን እያፈናቀላችሁ ለም መሬታችንን ለትግራይ መስጠታችሁ አግባብ አይደለም›› ብለው በመናገራቸው በረከት ስምኦን አፍኖ አጠፋቸው፡፡
በአማራው ክልል መሬት ጉዳይ በረከት እንዴት ብቸኛ አዛዥ ናዛዥ ሊሆን ቻለ? በረከት ስምኦንና መለስ ዜናዊ ቁጭ ብለው በአማራው መሬት ጉዳይ ለመፈራረም ችለዋል፡፡ ከተፈራረሙ በሁዋላ ደግሞ በረከት አማራ ካድሬዎችን እየሰበሰበ የውሳኔውን ትክክል መሆን ይሰብካል፡፡
‹ኢትዮጵያ› እና ‹ኢትዮጵያዊነት› የሚለው ቃል አይነሳብን ይላሉ፡፡ ‹እንግዲያው አማራ አይደላችሁምና የአማራውን ክልል ለአማሮቹ ልቀቁ› ሲባሉ፣ ‹ትምክህተኞች ነፍጠኞች› እያሉ ይሳደባሉ፡፡
‹ህወሃት ትግራይ ስጥ ፋብሪካዎች እየገነባ ነው፡፡ እናንተ ግን በአማራው ክልል ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ብቻ ነው የገነባችሁት› ብሎ የሚጠይቀውን፣ ‹ደመኛ ጠላት! ዘረኛ!› ይሉታል፡፡ ‹ምቀኛ› የሚልም ይመርቁለታል፡፡ ይህን መጠየቅ እንዴት ምቀኝነት ሊሆን እንደሚችል የማብራራት ችሎታ ግን የላቸውም፡፡
ወደ ጄኔራል ሃይሌ ጥላሁን ልመልሳችሁ፡፡
በርግጥ ሃይሌ ከመነሻው ህዝባዊ አመለካከት የነበረው አርበኛ አልነበረም፡፡ እንደ አብዛኞቹ የወያኔ አመራር አባላት እጁ በደም የታጠበ ነው፡፡ በቀዳሚው መፅሃፌ (የጋዜጠኛው ማስታወሻ) ጠቁሜው እንዳለፍኩት የአምቦው አዛውንት፣ የድምፃዊት አበበች አባት፣ ኦቦ ደራራ ከፈኔ እንዲገደሉ ውሳኔ ካስተላለፉት ጄኔራሎች አንዱ ሃይሌ ጥላሁን ነው፡፡
ይህ ጥቁር ታሪኩ እንዳለ ሆኖ ሃይሌ በተለይ በሸዋ አማራነቱ ብቻ ከስርአቱ ተፅእኖ እየደረሰበት ፊት ለፊት ሲናጭ ኖሮአል፡፡ በመጨረሻም በጡረታ አግልለውት ድምፁ ጠፍቶአል፡፡ ስሙ ደብዝዞአል፡፡
ሌኒን ባህርዳር ላይ ካስነሳው ማእበል በሁዋላ ሃይሌ ከነበረበት ስልጣን ተነስቶ ወደ ደብረዘይት አየር ሃይል ተላከ፡፡ በወቅቱ የአየር ሃይል አዛዥ ለነበረው ለጄኔራል ጀቤ፣ ‹‹ጠብቀው! ተጠንቀቀው!›› የሚል ምክር አብሮ ሳይላክለት እንዳልቀረ እንጠረጥራለን፡፡
ሃይሌ ጥላሁን የህወሃትን መከፋፈል ሊጠቀምበት ሞክሮ ነበር፡፡ ሳይሳካለት ቀረ፡፡ በርግጥ ሃይሌ ከልቡ ለመለስ ታማኝ ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ አየር ሃይልን ከተረከበ በሁዋላ የጀቤን ደጋፊዎች እንደ ጫት ቃማቸው፡፡ ደብረዘይት ላይ አብዮት ተነሳ፡፡ አማራና ኦሮሞዎችን፣ ‹‹ብሶታችሁን ተናገሩ!›› አላቸው ስብሰባ ጠርቶ፡፡
የአየር ሃይል አባላት ቁጭታቸውን ተናግረው ሳያበቁ ጄኔራል ሃይሌ እንዲህ የሚል የትግርኛ መልእክት ደረሰው፡፡ ‹‹እስካሁን ያልከውን ብለሃል፡፡ አሁን በቃህ!›› ይህ አባባል ሲተነተን፣ ‹‹ህወሃትን መቃወም ታክቲክ እንጂ ስትራቴጂ አይደለም፡፡ እና ጊዜ ተገኘ ብለህ አትጃጃል›› ማለት ነበር፡፡
መለስ ራሱን ካረጋጋ በሁዋላ ሃይሌን ከአየር ሃይል አነሳው፡፡ ሳይቀደም ቀደመው፡፡ በዚህ ዘመን አማራ ለሆነ ሰው የአየር ሃይል አዛዥነት ስልጣን ከቶውንም ሊሰጥ አይችልም፡፡
ሃይሌ ጥላሁን በጡረታ እስከተገለለበት እለት ድረስም ድምፁን ከፍ አድርጎ የህወሃት እኩዮቹን ዝርፊያ ተቃውሞአል፡፡ ተቃውሞው በርግጥ ለሃገር ከመቆርቆር ነው ወይስ የዝርፊያ ድርሻውን በማጣቱ በርግጠኝነት ማወቅ ይቸግራል፡፡
ስርአቱን የማስወገድ ሃሳብ ልቡ ውስጥ ቢኖር ኖሮ ከነበረው የማእረግና የስልጣን ደረጃ አንፃር የማድረግ ብቃቱን ባላጣ ነበር፡፡ ‹‹ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው፣ ሰው የጠፋ እለት›› ይባል የለ?
ወያኔዎችም ይህንኑ ይላሉ፡፡ ‹አማራው በታሪክ የሚኖር የወረቀት ነበር ነው› የሚለውን ብዙ ጊዜ በአደባባይ ይናገሩታል፡፡ በርግጥም በረከት ስምኦን ክልሉን እንደፈለገ እየተጫወተበት፣ ሁለት አሰርት አመታት መድፈናችን ነው፡፡ በጥቁር አማሮች የስልጣን ቀንበር ስር የጭቆና፣ የዘረኝነትና የውርደት ጎርፍ በአማራ ምድር እንደ አባይ ወንዝ ሲፈስ በአይናችን የምናይ የአይን ምስክሮች ነን፡፡
ይህን አባባሌን በመምዘዝ፣ ‹‹ህዝብና ህዝብን ለማጋጨት›› የሚል እሪታ የሚያሰሙ መጣጥፎች መነበባቸው አይቀርም፡፡ እኔ እስከማውቀው ግን ጥቁር አማሮች ህዝብ አይደሉም፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ማጅራት መቺ አደገኛ ቦዘኔዎች ብቻ ናቸው፡፡
በጥንት ዘመን የቡርቃ ወንዝ ውርደትን መሸከም ባለመቻሉ አካሉን ሰብስቦ ከመሬት ስር የመደበቁን ታሪክ ሰምተን ነበር፡፡ በዚህ በኛ ዘመን አባይ እና ቡርቃ ውስጥ ውስጡን እየተገናኙ ወግ ሳይጀምሩ አልቀሩም፡፡ ወሬው እውነት ከሆነ ከሁለት አንዱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ አባይ እንደ ቡርቃ አንገቱን ይደፋል፡፡ አሊያ ደግሞ አባይና ቡርቃ በአንድነት ተያይዘው መዘመር ይጀምራሉ…፡፡ (ገጽ 138)
 
(ተስፋዬ ገብረአብ፣ የደራሲው ማስታወሻ፣ ከገፅ 130-138፣ ነፃነት አሳታሚ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ 2002 ዓ.ም.፡፡)
የደራሲው ማስታወሻ ትረካችን እዚህ ላይ አበቃ፡
ፈጣሪ እናት ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic