>

"ፋኖ ለእኛ መደበኛ ተቋማችን ነው ፤ እውቅና መስጠት ግን የመንግስት ጉዳይ ነው....!!!" (ቬሮኒካ መላኩ)

“ፋኖ ለእኛ መደበኛ ተቋማችን ነው ፤ እውቅና መስጠት ግን የመንግስት ጉዳይ ነው….!!!”
ቬሮኒካ መላኩ

ፋኖ በወያኔ ዘመንም የህወሃትን ጨቋኝ አገዛዝ ገርስሶ ለመጣል በዱር በገደሉ በየበረሃው በመዋጋት ተኪ የሌለው መስዋዕትነት ከፍሎ ይመጣል ተብሎ ለነበረው ለውጥ መሰረት ጥሏል፡፡ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ለውጥ በተለያየ ምክንያት መንገድ ላይ ቢቀርም ፋኖ በአንድ በኩል መደበኛ ስራውን በመስራት የግልና የቤተሰቡን ህይወት በመምራት በሌላ በኩል ተጨባጭ ልውጥ እንዲመጣ እንደ ህዝብ ከህዝብ ጋር እየታገለ ቆይቷል ፡፡ ህወሃት በኢትዮጵያና በመከላከያ ላይ በከፈተው ጦርነት በመደበኛ የመከላከያ ሰራዊትና ልዮ ሃይል ብቻ መቀልበስ ከባድ የነበረውን ጦርነት ከመንግስት  በቀረበለት ጥሪ  መሰረት አስፈላጊውን ትግል በማድረግና የህይወት መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል ሃገራችን ተደቅኖባት ከነበረው መፈራረስና የመንግስትን ስልጣን በማረጋጋት በኩል የራሱን ድርሻ ተወጥቷል፤ በመወጣትም ላይ ነው፡፡ ይህን ሲያደርግ በመንግስት ግብዣ (የድረሱልኝ ጥሪ) መሰረት ሆኖ በመንግስት የእዝ ሰንሰለት እየተመራ ጭምር ነበር፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የሚገርመው የትጥቅና ስንቅ አቅርቦት የሚሸፈነው በራሱ በፋኖ በግሉ ፤ በኪሱ ነበር፡፡ ታዲያ ለዚህ በክፉ ቀን ለተገኘና ህይወቱን ሁሉ ለሰጠ ሃይል ምስጋና፤ የህይወትና የአካል ጉዳት ካሳ ሊታሰብለት ሲገባ ከድል አጥቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ስለሆነ መፍረስ አለበት የሚል ውይይት መካሄድ ነበረበት ? እውነት ህወሃትንና ኦነግን እስከመጨረሻው ከማጥፋት ይልቅ የፋኖ ኢ-መደበኛነት ነው አንገብጋቢ ችግር ሆኖ አጀንዳ የተቀረጸለት ?
ስለ ኢ-መደበኛነት ከተነሳ ለከማል ገልቹ ከስልጣን መውረድ ምክንያት ስለሆነውና በመንግስት በጀት እየተደጎመ ስለሚኖረው የኦነግ ስራዊት (ሪዘርቭ ሃይል) ላይ መጨከን ያልተቻለው ለምን ይሆን ? ኦነግ የበጀት ምንጩ የት ነው ? የመንግስት መከላከያ ሰራዊት ያልታጠቀውን የጦር መሳሪያ የታጠቀው ከየት አምጥቶ ነው ? ያን ሁሉ ሰራዊት በገፍ በየ ጊዜው በሞንታርቦና በV-8 ታጅቦ የሚያስመርቀው የት ሆኖ ነው ? ንጹሃን የሌላ ብሄር አባላት በተለይ ደግሞ አማራዎች በኦሮሚያ ምድር (በአሁኑ የክልል ስያሜ ለማለት ነው) እንዳይኖሩ እየገደለና እየያፈናቀለ ያለው ለምን ይሆን ? ጥላቻው ከመንግስት ሳይሆን ከንጹሃን ጋር የሆነው ለምንድን ነው ? እንደ ህወሃት ከመንግስት የጸጥታ ሃይል ጋር የማይገጥመው ለምን ይሆን? ከጸጥታ ሃይል ጋር ገጥሞ የማያውቀው ህጻናትና ሴቶች ላይ ጀግና የሆነውን ኦነግ በመንግስት የጸጥታ ሃይል ለማጥፋት ያልተቻለው ለምን ይሆን?
ከህወሃት ጋር ጋብቻ ፈጽሞ በኦሮሚያ ምድር ላይ እንደፈለገ እየናኘ ለሀገር መፍረስ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለውን ኦነግን ስለማጥፋት ነው ሰነድ ተሰንዶ ህዝብ መወያየት ያለበት? ወይስ ሃገርን ከመፍረስ ህዝብን ከእልቂት እየታደገ ያለውን ፋኖን (ለዚያውም በመንግስት ጥሪ መሰረት የሚታገለውን) ማፍረስ ነው አጀንዳ መሆን ያለበት? በኪስ ገንዘቡ ለነጻነት እየተዋደቀ ያለው ፋኖ ነው መጥፋት ያለበት? ወይስ የመንግስትን ሃብት እየተጠቀመ ሀዝብን ለእልቂት እየዳረገ ያለው ኦነግ ነው መጥፋት ያለበት?
ከምንም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የታጠቀ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት የለም የሚል ዝባዝንኬ በሰነዱ ላይ ተካትቶ ለውይይት መቅረቡ ነው ፡፡ ፋኖ የግል ሃብቱን ተጠቅሞ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ የመንግስትን የእዝ ሰንሰለት ተከትሎ ህወሃትንና ኦነግን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና መጫወቱ ኢ-መደበኛ ነው መፍረስ አለበት የሚያስብለው ከሆነ በመንግስት ክተት አዋጅ መሰረት የግልም ሆነ የመንግስት መሳሪያ የታጠቀ ሁሉ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ነበር ህወሃትን ሲዋጋ የነበረው፡፡ ታዲያ ያ ሁሉ የህዝብ መዓበል ኢ-መደበኛ ነው ተብሎ መፍረስ አለበት ይባል ይሆን ?
ይህንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለ ፋኖ እንደዚህ ከተባለ የመንግስትን ሃብት እየመዘበረ ለህዝብ እልቂት፤ ለሃገር መፍረስና ለአብሮነት ስጋት የሆነው ኦነግ ምን ሊባል ይችላል ? መቸም ኦነግማ አንድ ጊዜ አሸባሪ ተብሎ ተፈርጆ የለ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ ፡፡ እሽ አሸባሪ ሆኖ ተፈርጇል እንበል ፡፡ ታዲያ ህወሃትን ለማጥፋት ምንም አስተዋጽኦ ያላደረገውና ከየትኛውም ክልል በላይ በገፍ የተመረቀው የኦሮሚያ ልዩ ሃይልና የክልሉ ሚሊሻ/ታጣቂ ኦነግን ከኦሮሚያ ክልል ለምን ማጥፋት አልቻለም ? እንደ ህወሃት ኦነግም የህዝብ ሽፋን አለው እንዳይባል ደግሞ አሸባሪውን የደገፈ ህዘብ አሸባሪ ሊባል ነው ፡፡ ኦነግ የመንግስት ድጋፍ አለው አንዳይባል መንግስት ራሱም አሸባሪ ሊባል ነው፡፡ ግድ የለም ኦነግ ያልጠፋበት ምክንያቱ ምንም ይሁን ፡፡
ፋኖ ግን አስካሁን መንግስት ምንም ኢንቨስት ያላደረገበት፣ በነጻ ሃገሩንና ህዝቡን በማገልገል ላይ ያለ፣ ለህዝብ ሲል ውድ ህይወቱን የከፈለና አካሉን ያጎደለ፣ እንደ ማንኛውም ህዝብ መደበኛ የግል ስራውን በመስራት ቤተሰብና የግል ህይወቱን የሚመራ፣ ለሃገር ኢኮኖሚ የበኩሉን የሚያበረክት፣ ከምንም በላይ ንጹሃንን ከግዞት ለማውጣት ለነጻነት በግልጽ የሚታገል፣  ለንጹሃን ስጋት ያልሆነ፣ ለህዝብ ዋስ ጠበቃ የሆነ፣ የክፉ ቀን ደራሽ የጸጥታ ሃይል ነው ፡፡ ስለዚህ መንግስት የፋኖ ኢ-መደበኛነት አስቸግሮኛል ካለ መደበኛና እውቅና የተቸረው ተቋም ሆኖ እንዲሰራ የራሱ የፋኖም ፍላጎት ስለሆነ ይህ እንዲሳካ መንግስትም ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚሆን እርምጃ ግን ህወሃትም በ27 ጉዞው ሞክሮት ያልተሳካለት ጉዳይ ነው፡፡
Filed in: Amharic