>

"ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ.....!!!" (ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)

“ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ…..!!!”

ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)

ከሳምንታት በፊት የብልጽግና ፓርቲ አዘጋጅቶት የነበረው ሰነድ ርዕስ በሰላም ጎዳና ወደ ብልጽግና የሚል ነበር። ላይ ላዩን ሲያዩት ያማልላል፤ ሆኖም የሰላም ጎዳና የተባለው በአማራ ሕዝብ ህልውና ላይ የሚረማመድና ገና ነጻ ያልወጡ የአማራ አካባቢዎች እያሉ ጦርነቱ እንዲቆም ያደረገ ነበር።
የአሁኑ ደግሞ በተወሰነ መልኩ ለየት ያለ አቀራረብን የተከተለና ለሰላም ቅድሚያ የሰጠ መስሎ የአማራን አንገት የማስደፋት ዓላማ ያነገበ ሰነድ ለውይይት እንዲቀርብ ተደርጓል። በዚህም የአሸባሪውን ሀይል ወረራ በመመከትና ወደ መጣበት በመመለስ ረገድ የአማራ ሕዝብና መንግስት የተጫወተው ሚና ከማንም በላይ ሆኖ ሳለ ተድበስብሶ እንዲቀርብ መደረጉ ባለቤቱን ካልናቁ … ያሰኛል።
ይህም ብቻ አይደለም ገና ባልተጠናቀቀ ጦርነት ድህረ ጦርነት የሚል አሳሳች ሀሳብ ይዞ አኩሪ መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ለዚህ ያበቃውን የአማራን ፋኖና ታጣቂ ሀይል የስጋት ምንጭ አድርጎ ያቀርባል። የሚያሳዝነው ነገር ይኸም ሆነ የፊተኛው ሰነድ ሲዘጋጅ በፌዴራል መንግስትና በብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ውስጥ ስልጣን ላይ የተቀመጡት የአማራ ብልጽግና አመራሮች የማነን ጎፈሬ ያበጥሩ ነበር?
ነው ወይስ ያው የተለመደው የተላላኪነት በሽታ አገርሽቶባቸው ወደ ቀደመ እውነተኛ ባህሪያቸው ተመልሰው አዲሱን ጌታቸውን እያገለገሉ ይሆን? በእርግጥ የክልሉ አመራሮችና በየደረጃው የሚገኙት የስራ ሀላፊዎች ለምን የሚል ጥያቄ አንስተው በድፍረት በመሟገታቸው ምክንያት ሳምንት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት ጊዜ ወደ ባህር ዳር በመሄድ ብዙም ባይሳካላቸውም ካድሬዎችን ለማወያየት ተገደዋል።
ያም ሆነ ይህ የመከላከያና የሌሎች ክልሎች የተጫወቱት ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ የወረራው ሰለባ በመሆንም ሆነ ወረራውን በመከላከል ረገድ የአመራ ክልልና ሕዝብ የነበረው ድርሻና የከፈለው አኩሪ መስዋዕትነት በማንም ሊተካ ያልቻለ ሀቅ ነው። እውነታውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰለሚገነዘብም የማንንም ምስጋናም ሆነ የተለየ ዕውቅና የሚፈልግ ነው ብየ አላምንም።
በተለይ የአማራን ልዩ ሀይል ሚና የዛሬን አያርገውና ጠቅላይ ሚኒስሩ ራሳቸው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፊት ቀርበው በኩራት ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር። የፋኖዎችን አብሪ ኮከብነት ደግሞ በየግንባሩ የነበሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች አድናቆታቸውን ከመቸር አልፈው የሆነ ግንባር ለይተው እንዲሸፍኑላቸው ያደርጉ ነበር። በዚህም አበረታች ውጤት ተገኝቷል። ታዲያ አሁን ምን አዲስ ነገር ተገኘና ፋኖና ሌሎች ታጣቂዎች በስጋትነት ሊፈረጁ ቻሉ?
Filed in: Amharic