>

ጧፍ ያዡ ብአዴን! (ፍቃዱ ሽ.)

ጧፍ ያዡ ብአዴን!

 

(ፍቃዱ ሽ.)


ድሮ ፣ ድሮ አያቴ በህይወት በነበረበት ዘመን፣ በመንግስት ካድሬዎች ድርጊት አንጀቱ እርር ሲል፣ “ምድረ ጧፍ ያዥ ሁላ! ጧፍ ይዛችሁ፣ ፊታችሁን ወደ ግድግዳ አዙራችሁ ጌቶቻችሁን ከማብላት መቼ ነው የምትቆጠቡት!” ይላል፤ በቁጭት የእጁን ጣቶች እያንጣጣ፡፡

እውነት ነው፣ በጥንት ዘመን የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት በሀገራችን ስላልነበር የመሳፍንቱና የመኳንንቱ ቤተሰቦች እራት ለመብላት ማዕድ ላይ ሲቀርቡ፣ የቤቱ ምርጥ አገልጋይ ባሪያዎች ይመረጡና ጧፍ አብርተው በእጃቸው ከፍ አድርገው በመያዝ ፊታቸውን ወደ ግድግዳ በማዞር ቆመው እራት ያበሉ ነበር፡፡ ታዲያ አልፎ ፣ አልፎ መኳንንቱ እነዚያ ጧፍ ያዥ ታማኝ አገልጋዬቻቸውን ስማቸውን በመጥራት ከቀረበው ማዕድ ላይ ያጎርሷቸው ነበር፡፡ 

ጧፍ ይዘው፣ ጌቶቻቸው ሲበሉ እና ሲጠጡ እንዳያዩ  ፊታቸውን ወደ ግድግዳ አዙረው ፤ ወገባቸው እየተንቀጠቀጠ እግራቸው እየራደ፣ ለሰዓታት ቢቆሙም ለድካሙም፣ ለህመሙም ሆነ ለተገዢነቱ ትኩረት አይሰጡም፡፡ የእነሱ ትኩረት የጌቶቻቸው ጉርሻ ላይ ብቻ ላይ ነበር፡፡

ብአዴንም ከፍጥረቱ ጀምሮ ወያኔ በስልጣን በነበረችበት 27 ዓመታት ከጌቶቹ የሚጣልለትን ፍርፋሪ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ጌቶቹን ጧፍ ይዞ ፣ ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ፣ ባላየ እራት ሲያበላ ነበር፡፡

አሁንም ይህንን ታማኝ ባለሟልነቱን ለማስቀጠል፣ ከብቶቹን ሸጦ እና ነብሱን አሲዞ በብትር ከትግራይ ወራሪ ኃይል ጋር በመተናነቅ ማርኮ በታጠቀው መሳሪያ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ የአማራ ህዝብን ከከፋ እልቂት ፣ ሀገሪቱን ደግሞ ከመበታተን ቢታደግም፤

ለብልጽግና ፓርቲ፣ በየቀኑ አማራን እያረደ ካለውና ይዞታውን አስፋፍቶ እዚህ የመንግስት መቀመጫ ከሆነችው መዲና አፍንጫ ስር  በምትገኘው ኩዬ ከተማ ዙሪያ ያሉ ሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ እየተርመሰመሰ ካለው፣ እንዲሁም ከአ.አ. በስተ ደቡብ ምስራቅ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ዝቋላ በመባል በሚታወቀው ከፍተኛ ተራራ አካባቢ እንደ ልቡ የሚንቀሳቀሰውና በአቅራቢያው በምትገኘው የገጠር ከተማ ያለማንም ሃይ ባይነት እየገባ ፖሊሶችን በጠራራ ፀሀይ እየገደለ ካለው ከኦነግ ሸኔ ይልቅ የአማራ ህዝብ አሌንታ የሆነውን ፋኖን ለስልጣናቸው እንደ ስጋት በመቁጠር ትጥቅ ለማስፈታታ እየተሯሯጡ ነው፡፡

ይህንንም እቅዳቸውን ደግሞ ብአዴን ለማስፈጸም እንቅልፍ አጥቶ እየሰራ  ነው፡፡

ብአዴኖች እንደው ቢያንስ፣ ቢያንስ ጧፋችሁን አሽንቀጥራችሁ ጥላችሁ ከኦህዴድ ጋር እኩል ማዕድ ላይ ቅረቡ፡፡ ለምን ቢሉ? እወክለዋለው የሚሉትን ህዝብ ጥሎ ሊጋባነትን አንጠልጥሎ፣ ለመጣው ሁሉ ማጎብደድ የኃላ፣የኃላ  ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላችኃልና፡፡

Filed in: Amharic