>
5:13 pm - Tuesday April 18, 7893

መንግስታዊ አገር የማፍረሻ የክህደት ሰነድ....!!!

መንግስታዊ አገር የማፍረሻ የክህደት ሰነድ….!!!

 
አማራ ላይ ያነጣጠረው የኦሕዴድ ብልፅግና ሰነድ እጃችን ገብቷል እነሆ! 

ሰነዱ በግልፅ እንደሚያስረዳው መጨው ጊዜ ለአማራ እጅግ የከፋ ከአለፈው የበለጠ ሴራና መከራ የተጎነጎነለት እንደሆነ ይነግረናል።
ሰነዱን በ PDF ወይንም በ Word እንድልክላቹህ የምትፈልጉ ሰዎች በውስጥ መስመረ አናግሩኝ። መረጃውን ከአገር ቤት የላኩልኝን በእጅጉ አመስግኑልኝ!
ድህረ ጦርነት በሚል ለብልፅግና ካድሬዎች ውይይት የቀረበው ሰነድ ህዝብም ሊወያይበት ያስፈልጋል::
ሰነዱ በዋናነት ያተኮረው በአማራ ክልል ላይ ይመስላል::
ጦርነቱ ባላለቀበት ሁኔታ አማራ ክልል ውስጥ ያሉትን ፋኖና ሌሎች አደረጃጀቶችን ትጥቅ ለማስፈታት ያለመ ነው::
ይህ ደግሞ ክልሉን ለእርስ በርስ ግጭትና ለህወሃት ጥቃት ተጋላጭ ያደርገዋል::
ከፍተኛ ውድመት የደረሰበትን ክልል እንዴት መልሶ መገንባት እንደሚቻል የሚለው ነገር የለም::
ሰነዱ ስለ ድህረ ጦርነት ቢያወራም ጦርነቱ እንዴት እንደሚጠናቀቅ አይገልፅም::
ሰራዊቱ ትግራይ የማይገባው በትግራይ ላይ በቀል እንዳይፈፀም ነው ይላል::
ብዙ ንፁሃን ዜጎች የሚታረዱበት ኦሮምያ ክልል ደግሞ ህገወጥ ታጣቂ የሌለበት ተደርጎ ቀርቧል::
የድህረ ጦርነት መዛነፎች እና እርማቱ የሚለው የኦሮሞ መንግስት የስልጣን ማደላደያ ሙሉ ይዘቱ ጦርነት የሚያስነሳ እንጂ ሰላም የሚየመጣ አይደለም። የገዥ መደቡን የኦሮሞ መንግስት ወንበር ስጋት ላይ የሚጥሉ ሀይሎችን ለመምታት ህጋዊ ቅቡልነት ለመውሰድ የሚይዘጋጅ አካል እንዳለ በግል ያስረዳል። ሲጀመር አማራ እንደህዝብ በዚህ የህልውና ጦርነት ያበረከተውን አስተዋፆ የዘነጋ የከፈለውን ክቡር መስዋትነት የደበቀ ሁኖ አግኝቸዋለሁ። አጠር ባለ አነጋገር ዶክመቱ የአማራን ህዝባዊ ሀይል ለማጥፋት እንደታቀደ፣ የተገኘውን ሩብ የጦርነት ድል ለመቀማት እንደታሰበ፣ በመላው ኢትዮጵያ አማራን እየገደሉና እየጨፈጨፉ እንደሚቀጥሉ ያስፈራሩበት እንዲሁም የኦሮሚያ ልዩ ሀይል በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ለመጠበቅ ፈቃደኛ አለመሆኑኑ ያስረዳበት ሁኖ አግኝቸዋለሑ። የሚያሳዝነው ግን የአማራ ክልል መንግስት በዚህ የህልውና ጦርነት ላይ ኢ መደበኛ ሀይል ያሳተፈ የአማራ ክልል ሁኖ እያለ እና በዚህ ሰሀትም ፋኖዎች እንዲሰለጥኑ ፈቃድ ሰጥቶ ሲያበቃ አሁን በዚህ ሞጅዩል በእየ አዳራሹ ካድሬ ሰብስቦ ለማወያየት ሲሞክር ምን አስበው ነው ብየ እንድጠይቅ አድርጎኛል?
ታዲያ አሁን ገዥው መደብ (መንግስት) ምን ለማድረግ አስቧል?
አገዛዙ በዚህ ሰነድ መሰረት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ህዝቡን ማወያየትና ይህ አካሄድ የሚያመጣውን ችግር ማጤን አለበት::
=========================
በዘላቂ ድል ወደ ብልጽግና”
የድኅረ ጦርነት መዛነፎችና እርምቶቹ
  ታህሣሥ 2014 ዓ.ም
ማዉጫ
1. መግቢያ 1
2 ሀገራዊ የድኅረ ጦርነት ፈተናዎችና አቅጣጫዎች 3
2.1 የአማራ ክልል ሁኔታ 3
2.2 የአፋር ክልል ሁኔታ 5
2.3 የትግራይ ክልል ሁኔታ………..………………..………………………………………………..6
2.4 የኦሮሚያ ክልል ሁኔታ 7
2.5  የአዲስ አበባ ሁኔታ…..…………………………………………………………………………………..8
2.6 የሶማሌ ክልል ሁኔታ 9
2.7 የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁኔታ 9
2.8 የጋምቤላ ክልል ሁኔታ 10
2.9 ሲዳማ ክልል ሁኔታ 11
2.10 የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሁኔታ 11
2.11 የሐረሪ ክልል ሁኔታ 12
2.12 የድሬዳዋ አስተዳደር ሁኔታ 12
2.13 የደቡብ ብ/ብ/ህዝቦች ክልል ሁኔታ 13
3 ማጠቃለያ 15
“በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና፣ ገደሉን ሳታይ እልም ካለው ገደል ወደቅክብን ወይ?” – ሀገራዊ ብሂል 
1. መግቢያ
የፖለቲካ ቅራኔዎች ወደ ግጭት አድገው ለብዙኃን እልቂትና ለንብረት ውድመት ምክንያት በመሆን በጦርነት ድምዳሜ ሊያገኙ ይችላሉ። ሆኖም ጦርነቱን በድል ያጠናቀቀው ኃይል የድኅረ ጦርነት ሁኔታውን በአግባቡ መምራት ካልቻለ፣ የጦርነቱ ሂደት የሚፈጥረው የፖለቲካና ወታደራዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቡናዊ መናጋት የሚወልዳቸው ችግሮች ድሉን ወደ ኋላ የሚቀለብሱና አሸናፊው ወገን ወደ አዲስ ብጥብጥ እንዲገባ የሚያደርጉ የድኅረ ጦርነት ቀውሶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ጠላትን በጦር ሜዳ በማሸነፍ ብቻ ዘላቂ ድል ማግኘት አይቻልም። የጦርነት ሜዳ ድል በዘላቂነት እንዲረጋገጥና ወደ ፖለቲካ ድል ከፍ እንዲል፣ ከድል ማግሥት የሚከሠተውን የድኅረ ጦርነት ሁኔታ በአግባቡ መምራትና የተገኘውን ድል ወደ ኋላ ሊመልሱት ከሚችሉ ተግዳሮቶች መጠበቅ ያስፈልጋል። በማያባራ ጦርነት አዙሪት ውስጥ የቆዩ ሀገራት ተሞክሮም ለዚህ እውነታ ጥሩ ማሳያ ይሆናል።
ከዘመናት ትግል በኋላ ነጻነቷን ያገኘችው ኢስት ቲሞር ከነጻነት ማግሥት የነበረውን የድኅረ ጦርነት ሁኔታ በአግባቡ መምራት ባለመቻሏ በመከላከያና በፖሊስ ውስጥ የታቀፉት የቀድሞ ታጋዮቿ ጎራ ለይተው ጦርነት እስከመግጠም የደረሱበት አለመረጋጋት ውስጥ እንድትቆይ አድርጓታል። በላይቤሪያም በእርስ በርሱ ጦርነት የተሳተፉ ታጣቂዎች ይፈጽሟቸው የነበረው ሕገ ወጥ ተግባራት ሀገሪቱ ለተራዘመ የድኅረ ጦርነት አለመረጋጋት እንድትጋለጥ ያደረገ ነበር።
ድኅረ ጦርነት ቀውስ ብዙ መነሻዎች ያሉት ክሥተት ነው። ለድኅረ ጦርነት ቀውስ መነሻ ተደርጎ የሚቀርበው አንዱ ጉዳይ ጦርነት በተከሠተበት ማኅበረሰብ ውስጥ ተለምዷዊ እሴቶች ላይ የሚፈጥረው መሸርሸር ነው። በግጭት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው በጦርነት ውስጥ የሚፈጸሙ የኃይል እርምጃዎችና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች፣ በድኅረ ጦርነት ማኅበረሰቡ የኃይል እርምጃና ሕገ ወጥ ተግባራት እንዲለማመድ በማድረግ ከጦርነቱ በኋላ ወንጀል የሚበራከትበትን ማኅበራዊ ዐውድ ይፈጥራሉ። ጦርነት ግድያና ዘረፋን በቀላሉ የሚያይ ማኅበረሰብ ሊፈጥር ይችላል። በዚህ የተነሣ የሕግ የበላይነትን ብቻ በማስፈን የድኅረ ጦርነት መረጋጋትን መፍጠር ፈታኝ ይሆናል።
በጦርነቱ የተሳተፉ ታጣቂዎች ጦርነቱ ተጠናቆ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ቢደረግም ትጥቅ የመፍታት ሂደት በቀላሉ የሚተገበር አይደለም። በመሆኑም፣ ታጥቆ የሚገኘው ኃይል ለሥርዓት አልበኝነት መበራከት ጉልህ ሚና ይጫወታል። ታጣቂው የተሰለፈበት የጦርነት ዓላማ፣ ከጦርነቱ ማለቅ ጋር ቢቋጭም የታጣቂው ፍላጎት ወደ ቁስ መሰብሰብ ሊሸጋገር ይችላል። ከዚህም በላይ ጦርነቱ የሚፈጥረው ውድመት የሚያስከትለው ሥራ አጥነት ሥርዓት አልበኝነቱን ያባብሰዋል።
“በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በጦርነት የሚከሠተው የዕሴት መሸርሸርና ሥርዓት አልበኝነት ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ለማድረግ የሚያስችሉ የመንግሥት የሕግ ማስከበር ተቋማት በጦርነቱ የመፈራረስ ዕጣ ያጋጥማቸዋል። የመንግሥት ተቋማት መዳከም ከሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች ጋር ተደምሮ የድኅረ ጦርነት ሁኔታው ወዳልተረጋጋ ጫፍ እንዲደርስ ይገፋዋል። በተጨማሪም የድኅረ ጦርነት ሁኔታው የሚፈጥረው የጸጥታና የፖለቲካ ክፍተት፣ ጣልቃ በመግባት ጦርነቱን በራሳቸው መንገድ መቅረጽ ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ሁኔታው ከወቅታዊ ሁኔታችን ጋር ተመሳሳይነት አለው። አሸባሪው ጁንታ የከፈተብንን ወረራና ጦርነት በተሳካ ሁኔታ በአጭር ጊዜ እየቀለበስን ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት፣ ከወራሪው አሸባሪ ነጻ በወጡ ቀጣናዎች የአለመረጋጋት ችግር እየተስተዋለ ነው። ይህም እንደ ሀገር ወደ ድኅረ ጦርነት አለመረጋጋት እንዳንገባ ያሠጋል።
በተለይም ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን ለሕልውና ዘመቻው በስፋት እንዲሳተፉ ማድረጋችን ይታወቃል። በእነዚህ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች የሚገኙ አንዳንድ ክፍሎች፣ በጦርነቱ ያስቀመጥናቸውን ፖለቲካዊ ግቦች ወደሚሸረሽሩ ተግባራት የመሠማራት አዝማሚያ እያሳዩ መጥተዋል። ሀገራዊ የክተት ዐዋጁን በመቀላቀል ውሱን የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማጉላት እየተጠቀሙበት ነው። የወገንን የተግባር አንድነት የሚበታትኑ ተግባራት ላይ የመሳተፍ አዝማሚያም እያሳዩ ነው።
“ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ የሥርዓት አልበኝነት ዝንባሌዎቹ ጠላቶቻችን በቅንጅት ከከፈቱብን ጦርነት ጋር ተዳብሎ ከጫፍ የደረሰ ድላችንን ወደ ኋላ እንዳይመልሰው የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። የድኅረ ጦርነት ሁኔታውን በትኩረትና በዲሲፕሊን መምራት ካልቻልን ጦርነት ውስጥ ያስገቡን ጠላቶቻችን በጦር ሜዳ ያጡትን ድል፣ በድኅረ ጦርነት ቀውስን ለማግኘት እንዲሞክሩ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም በወገን በኩል በሚፈጠሩ ግድፈቶችና መዛነፎች አማካይነት ወደ ድኅረ ጦርነት ቀውስ እንዳንገባ የጋራ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
የሰነዱ አንኳር ጉዳይ በጁንታው ላይ የተቀዳጀናቸውንና በቀጣይም የምንቀዳጃቸውን ሁለንተናዊ ድሎችን ጠብቆ በማስፋት ወደ ዘላቂ ሰላም ለመሸጋገር የምናደርገውን ጥረት መዳሰስ ነው። ከዚህ አኳያ ሰነዱ የጦርነት ድሉን ተከትለው የሚመጡ የፖለቲካና የጸጥታ ችግሮችን በመቃኘት፣ ወደ ድኅረ ጦርነት አለመረጋጋት ሊከቱን የሚችሉ መዛነፎችን በመለየት፣ ለችግሮቹ መፍትሔ በማበጀት፤ አርመን ወደ ፊት መቀጠል የሚቻልባቸውን አቅጣጫዎች ይጠቁማል።
2 ሀገራዊ የድኅረ ጦርነት ፈተናዎችና አቅጣጫዎች
2.1 የአማራ ክልል ሁኔታ
        ሀ/ የፖለቲካ ሁኔታ
በፖለቲካው መስክ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ጠቅለል አድርገን ስናያቸው በሦስት ፈርጆች ሊሠፍሩ ይችላሉ፤ የድል ሽሚያ ፖለቲካ፣ የይገባኛል ፖለቲካ እና የተከዳን ፖለቲካ ናቸው።
የድል ሽሚያ ፖለቲካ፡- ድሉን ማን አመጣው በሚል አጀንዳ ሕዝቡን የመከፋፈልና የፖለቲካ ተዋሥዖው ባለድሉ እኔ ብቻ ነኝ በሚል እሰጥ አገባ እንዲሞላ የሚያደርግ ነው። ይህ የድል ሽሚያ ፉክክር፣ በዋናነት በክልሉ የጸጥታ ኃይሎችና በፌዴራል ኃይሎች መካከል፣ እንዲሁም በክልሉ ልዩ ልዩ ኃይሎች መካከል፣ እንዲሁም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መካከል የሚፈጠር ሊሆን ይችላል። በተለይም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚደረግ ፉክክርና እርስ በርስ መካሰስ፣ በጦርነቱ ውስጥ የነበረን ሚና እየጠቀሱ መወቃቀስ፣ ወዘተ. የክልሉን ፖለቲካና አንድነት አደጋ ውስጥ ሊጥለው ይችላል።
የይገባኛል ፖለቲካ፡- ከግለሰብ እስከ ቡድን በትግሉ ውስጥ የተሳተፉ ወይም የደገፉ አካላት ስለታገልኩ ልዩ ችሮታ ያስፈልገኛል/ይገባኛል የሚል አጀንዳ ይዘው የሚመጡበት ነው። ይህን ሁኔታ በሁለት መንገድ መመልከት እንችላለን፤ አንደኛ – በመንግሥት ውስጥ፣ ሁለተኛ ከመንግሥት ውጭ። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የዘመተውና ያልዘመተው አመራር፣ በጉልህ የተሳተፈውና ያልተሳተፈው አመራር፣ ወዘተ. መካከል ውጥረት መከሠቱ አይቀርም። በዘመቻው ጉልህ ተሳትፎ ስላለኝ የተሻለ ቦታ ይገባኛል የሚሉ ድምፆች ቅሬታና የመጠላለፍ አዝማሚያ መፍጠራቸው አይቀርም። በሌላ በኩል ደግሞ ከመንግሥት ውጭ ያሉ አካላት ከዘመቻ መልስ ጥቅም ወይም ሥልጣን ፍለጋ በመንግሥት ላይ ጫና ማሳደራቸው አይቀርም። ጫናው በግለሰብ ወይም በተደራጀ አኳኋን በቡድን ደረጃ ሊከሠት ይችላል። በግለሰብ ደረጃ ከመንግሥት ልዩ ችሮታ የመፈለግና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ቅድሚያ ለማግኘት መሞከር ሊኖር ይችላል። በቡድን ደረጃ ደግሞ የድል አጥቢያ አርበኝነት አዝማሚያ፣ እኔ ነኝ ባለድሉ ማን ይናገረኛል የሚል ዐመፀኝነት፣ እና የመንግሥትን ሥልጣን የመገዳደር ፍላጎት ሊስተዋል ይችላል።
ይህኛው አዝማሚያ በቀጣይ ለክልሉ ፖለቲካ ዋነኛ ሥጋት ሊሆን የሚችል ነው። በተለይም ይህ የድል አጥቢያ አርበኝነት አዝማሚያ ከአካባቢያዊነት ጋር ከተሰናኘና የአመራሩም በዚያ ተሳታፊ ከሆነ የክልሉን ፖለቲካ ከፍተኛ አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል መገመት ይቻላል።
የተከዳን ፖለቲካ፡- የትግራይን ክልል ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠር ድል ይገኛል ብሎ የሚያምን ልሂቅና አክቲቪስቱ፣ ጦርነቱ እነሱ በሚያስቡት መንገድ ባለመጠናቀቁ የፌዴራል መንግሥት ‘ከድቶናል’ የሚል ቅሬታ ሊቀርብ ይችላል። የፌዴራል መንግሥቱ ክህደት ፈጽሞብናል፣ መንግሥት ሌላ ዓላማ አለው፣ ዘመቻ ህብረብሔራዊ አንድነትን ቀደም ብሎ ማድረግ ይቻል ነበር፣ ወዘተ. የሚሉና ጦርነቱ የሚቋጭበትን መንገድ ያለመቀበል አዝማሚያዎች ይኖራሉ።
ለ/ የጸጥታ ሁኔታ
በድኅረ ጦርነት ክልሉን ሊፈትኑት ከሚችሉት ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የሕግ የበላይነት መሸርሸር ነው። ጦርነቱን ተከትሎ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችንና የጸጥታ ችግሮችን በሦስት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡- የተለምዷዊ ወንጀሎች መበራከት፣ አጋጣሚውን ለግል ጥቅም የማዋል ፍላጎት፣ እና በትግራይ ክልል ውስጥ በቀል የመፈጸም ፍላጎት ናቸው።
ሐ/ ሰብአዊ ሁኔታ
አሸባሪው ሕወሐት ከአማራ ሕዝብ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ የመጣ በመሆኑ በአማራ ክልል አሰቃቂ ሰብአዊ ቀውስ እንዲከሠት አድርጓል። ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል፤ ሴቶች ተደፍረዋል፤ ሕጻናት ተገድለዋል፤ ሕጻናት እናቶቻቸው ሲደፈሩና አባቶቻቸው ሲገደሉ አይተዋል፤ ሕዝብ ተፈናቅሏል፣ ሰቆቃዎች ተፈጽመዋል። አሁን የሚስተዋለው ሰብአዊ ቀውስም በጊዜ ሂደት የመንግሥትን ዐቅም እየተፈታተነና የችግር ተጋላጮች ቁጥርም እየጨመረ እንደሚመጣ መገመት ይቻላል።
2.2 የአፋር ክልል ሁኔታ 
የኢትዮጵያን ጉሮሮ አንቃለሁ በሚል ቀቢፀ ተስፋ የጁንታው የሽብር ወረራ ካረፈባቸው ክልሎች የአፋር ክልል አንዱ ነው። በአፋር በኩል በወራሪው ቡድን የተከፈተው ጦርነት የኢትዮጵያን የንግድ መሥመር ከመዝጋት ባሻገር ጦርነቱን ቀጣናዊ ለማድረግም ነበር። ዋናውን ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በማድረግ ንዑሳን ጦርነቶችን ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰኑ ሀገራት ውስጥ ካሉ ጎሳዎች ጋር የማቀናጀት ሰፊ ግብ ነበረው። ይሁን እንጂ በትግራይ ወራሪ ኃይል ጦርነት የተከፈተበት የአፋር ክልል በተለመደ አስደናቂ የጀግንነት ገድል አሳፍሮ መልሶታል።
የአፋር ህዝብ ለሀገሩ ክብር፣ ለወገኑ መከታነት፣ ለሃይማኖቱ ክብርና ንጽሕና፣ እንዲሁ ለፍትሐዊነት ሲል ከመከላከያ ሠራዊትና ከልዩ ኃይሉ ጋር በመሰለፍ በጽናት ተፋልሟል። አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከኢትዮጵያዊነት ሥነ ምግባርና ከሰብአዊ ሞራል በተፃረረ መልኩ በአፋር ሕዝብ ላይ ሰብአዊ፣ ተቋማዊ፣ ቁሳዊና ማኅበራዊ ውድመት አድርሷል። በጅምላ ጨፍጭፏል፤ ሴቶችን ደፍሯል። መስጊዶችንና የመደረሳ ትምህርት ቤቶችን አፈራርሷል፤ አርክሷል፤ ቁርዐኖችን ቀዳዷል፤ አቃጥሏል። የትምህርትና የጤና ተቋማትን ዘርፏል፤ መሠረተ ልማቶችን አውድሟል።
በዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መከላከያ ሠራዊታችን፣ የአፋር ልዩ ኃይል እና የአፋር ሚሊሻ የትግራይ ወራሪ ቡድንን ሙሉ በመሉ ከአፋር ምድር ጠርጎ አስወጥቶታል። አሁን በአፋር ምድር የሚደረግ ጦርነት የለም። ይሁን እንጂ በጠላት ፊት ለፊት ገጥሞ የመዋጋት ዐቅም ባይኖረውም የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረጉ ግን የማይቀር ነው። አሁን ባለው አሰላለፍ ጠላት ወደ አፋር ድንበር አንድ ርምጃ እንዳይራመድ በማድረግ ባለበት ከስሞ እንዲቀር ተደርጓል።
የአፋር ሕዝብ እና አመራር ከድሉ ማግሥት ድሉን የሚያይበት መነጽር የጠላትን ቀጣይ እኩይ ሤራ ለማክሸፍ የሚኖር ድርሻ እጅግ የላቀ ይሆናል። ጠላት ሽንፈት ሲደርስበት ሊከተላቸው የሚችላቸው እኩይ ሥራዎች ይኖራሉ። የወገን ኃይል ባገኘው ድል ተኩራርቶና ተመክቶ ስሕተቶችን ከመሥራት ከመቆጠብ ባሻገር ነባራዊ ሁኔታን ገምግሞ ተራማጅ ዕቅድ በማውጣት ተግባራዊ ማድረግና መተባበር ይኖርበታል።
2.3 የትግራይ ክልል ሁኔታ 
የትግራይን ወጣት በማስፈጀት መነሻ ግቡን ሳያሳካ የሚጠናቀቀው የጁንታው ጦርነት በክልሉ የሚያስከትለው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ፣ ጁንታው መከላከያችን መቀሌን ለቅቆ በወጣ ማግሥት አግኝቶት የነበረውን ተቀባይነት የሚሸረሽረው ይሆናል። እንደሚታወሰው ለትግራይ ክልል ሕዝብ የማሰላሰያ ጊዜ ለመስጠት ሠራዊቱ መቀሌን ለቀቀ። ጁንታና ደጋፊዎቹ የሠራዊቱን ከመቀሌ መልቀቅ እንደሽንፈት አቀረቡት። አሁን ላይ ይህ የጁንታውና የደጋፊዎቹ ትርክት ሐሰተኝነቱ በገሃድ ታይቷል። “በተለየ ሁኔታ ጽናት ያለን ሕዝቦች ስለሆንን ማንም አያሸንፈንም” የሚለው ፋሽስታዊ የጥላቻ ቅስቀሳውም ከጁንታው መሰበር ጋር አብሮ ተሰብሯል።
ወታደራዊ ሽንፈቱና የሥነ ልቡናዊ ቀውሱ፣ ቀስ በቀስ ለጁንታው የሰቆቃና የሽብር ስልት ቀንደኛ ደጋፊ ሆኖ ወደ ከረመው ከክልሉ ውጭ ወደሚገኘው የትግራይ ተወላጅ መድረሱ አይቀርም። ይህ ኃይል በክልሉ የሚገኘውና የጁንታው የሰቆቃ ስልት ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽና ማገዶ ከሚሆነው ሕዝብ ይልቅ ለጁንታው ጽንፈኛ አካሄዶች ከፍተኛ ድጋፍን የሚያቀርብ ነው። የጁንታው አንጎል ጀብዶች የሚያስነሷቸው የእሳት ማዕበሎች የማይነኩት ከክልሉ ርቆ የሚገኘው የትግራይ ተወላላጆች የተወሰኑት ጽንፈኛ አቋምን የሚያራምዱ፣ ከሌሎች ብሔሮች ልሂቃን ጋር እልህ የመጋባትና የፉክክር አዝማሚያ ያላቸውና ለጁንታው የሚሰጠው የዲፕሎማሲና የሚዲያ ድጋፍ ጦርነቱ እልባት ወደ ማያገኝበት መራዘም እንዲያመራ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ናቸው።
ኢትዮጵያን አዳክሞ የማጥፋት አጀንዳ ያላቸው የውጭ ጠላት ሀገራት ጁንታውን እንደፈረስ እየጋለቡ አዲስ አበባን የመቆጣጠር ምኞታቸው ተጨናግፏል። ጁንታው አንዳንድ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ወራት ፈጅቶበት ነበር። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የኢትዮጵያ ጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠራርጎታል። ሁኔታው በጁንታው ላይ ከፍተኛ ተስፋ ያደረጉት የውጭ ጠላቶቻችንን ጭምር ያስደነገጠ ሆኗል። የጁንታው በአጭር ጊዜ መሸነፍ የውጭ ኃይሎች ቆም ብለው በማሰብ፣ የአካሄድ ለውጥ እንዲያደርጉ ማስገደዱ አይቀርም። በሠራዊታችን ድል የውጭ ጠላቶቻችን እንደ ሀገር በቀላሉ የማንሰበር መሆናችንን እየተረዱ መጥተዋል። በሂደት ዘላቂ ጥቅማቸውን ከጁንታው ጋር ከሚሠራ አሻጥር ሳይሆን ጥቅማቸውን በሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ የሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ብቻ ሊያረጋግጥላችው እንደሚችል እየተገነዘቡ መምጣታቸው አይቀርም። በዚህም ጁንታው ከውጭ ኃይሎች የሚያገኘው ድጋፍ እየቀነሰ የሚሄድ ይሆናል።
ድኅረ ጦርነት ትግራይ የጁንታው ተሸናፊነት የጁንታው የፖለቲካና የወታደራዊ አመራር እርስ በእርስ እንዲወነጃጀል ያደርገዋል። በንጹሐን የግፍ ፍጅት ያጣሁትን ማዕከላዊ ሥልጣን አገኛለሁ ብሎ ቋምጦ ጦርነት የቀሰቀሰው ጁንታ፣ የቋመጠለትን ሥልጣን እንኳን ሊያገኝ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ አስጨርሶ ጣዕረ ሞት ላይ ይገኛል። ሽንፈቱን ተከትሎ የውድቀቱ ምክንያት እገሌ ነው ወይም እገሌ እየተባባለ መከፋፈሉ አይቀሬ ነው።
በመካከላቸው የነበረውን የቆየ ቁርሾ በጊዜያዊ ድል ሸፍኖ የጋራ ጠላትን ለማጥፋት አንድ መስሎ የቆየው ጁንታ፣ የጦር ሜዳ ሽንፈቱ ወደ አዲስ የመሰነጣጠቅ አረንቋ ይወስደዋል። ሁኔታውን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለና የጁንታውን መፈረካከስ የሚያባብሱ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልቶችን በተቀናጀ አግባብ ማከናወን ከተቻለ የሚፍረከረከውን ጁንታ በታትኖ ለመቅበር መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ይሆናል።
በድኅረ ጦርነት ከጁንታው ጋር የምናደርገው ትግል በአጭር እንዳይቋጭ በማድረግ ጉልህ ሚና የሚጫወተው የውጭ ጠላቶች ጣልቃ ገብነት ነው።
2.4 የኦሮሚያ ክልል ሁኔታ  
ጁንታው ሰሜን እዝ ላይ የጥቅምት 24ቱን ጥቃት ፈጽሞ ጦር ሜዳውን በትግራይ ክልል ከማድረጉ በፊት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተልዕኮ ውጊያዎችን ሲፈጽም ነበር። በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የምስራቅ ዕዝንና የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይልን ተጠቅሞ ያካሄደው ጦርነት አንዱ ሲሆን በምዕራብ በኩል በቤንሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ክልል የተልዕኮ ውጊያዎች አድርጓዋል። በተለይም በወለጋ አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን የሸኔ የሽብር ቡድን ተጠቅሞ ሀገርና ሕዝብን ሲወጋ ነበር። ሕዝብ ተረጋግቶ ሰላማዊ ሕይወት እንዳይመራ፣ የመንግሥት አስተዳደር ሥራዎች እንዲቋረጡ በማድረግ፣ ባንኮችና የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን በመዝረፍ የሕወሃት ስውር እጅ ሰፊ ዘመቻዎችን ሲያደርግ ነበር።
የኋላ ኋላ የሽብር ቡድኖቹ የጥፋት ጋብቻቸውን በይፋ ከገለጹም በኋላ መንግሥትና ሕዝብ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋ የሽብርና የጥፋት እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ነበር። እነዚህን የጥፋት ተልዕኮዎች እንዲመክኑ ከማድረግ ባለፈ በጁንታ ላይ የተከፈተው ጦርነት በድል እንዲደመደም ክልሉ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ኦሮሚያ ከመደበኛ የጸጥታ አደረጃጀት ውጭ በኢ-መደበኛነት ታጥቆ የተሠማራ ከፍ ያለ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት የለበትም። ይህም በመሆኑ በድኅረ ጦርነት የታጠቀ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት የሚፈጥረው የጸጥታ መደፍረስና ሥርዓት አልበኝነት በኦሮሚያ ይከሠታል ተብሎ አይጠበቅም።
  ኦሮሚያ ክልል ጁንታው ወደ ሥልጣን የመመለሻ ፈረስ ይሆነኛል ብሎ መጠነ ሰፊ ድጋፍ የሚያደርግለት ሸኔ ሰፊ የሽብር ተግባር የሚፈጽምበት ክልል ነው። የክልሉን የድኅረ ጦርነት ሁኔታ ሲታይ ቀጣይ ተግዳሮት ሆኖ የሚቆየው የሸኔ ሽብር እንደሚሆን ይጠበቃል።  በመሆኑም የሸኔ የሽምቅና የሽብር ጥቃቶች በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች፣ በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂና ቦረና ዞኖች፣ እንዲሁም በአማራ የኦሮሚያ ዞንና ሌሎች የኦሮሚያ ዞኖች ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃትና ዘረፋዎችን ለማስፋት ይሞክራል።
መንግሥት ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እርምጃ በመውሰድ ሸኔ መደበኛ የመንግሥት ሥራዎችን ማደናቀፍ፣ የዜጎችን ሰላምና እንቅስቃሴ መግታት፣ አርሶ አደሮችን ከእርሻ ተግባራቸው ማራቅና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ማድረግ እንዳይችል መሥራት ያስፈልጋል።
2.5 የአዲስ አበባ ሁኔታ
አዲስ አበባ በጦርነቱ ወቅት ለህልውና ዘመቻው መሳካት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። የሕዝቡን የሞራል ድጋፍ በማስተባበር፣ ሀብት በማሰባሰብ፣ በሎጅስቲክ፣ የደኅንነት ሥጋቶችን በመቅረፍ በተለይም ሰፊ-ሕዝባዊ ሠራዊት ተደራጅቶና ሠልጥኖ ስምሪት በመውሰድ ለፀጥታ ኃይላችን የቀኝ እጅ በመሆን በመንቀሳቀስ፣ ወዘተ ግንባር ቀደም ሥራ ሠርቷል። ድኅረ ጦርነት በከተማው ሊኖሩ የሚችሉ ሁኔታዎች ከወዲሁ አውቆ መዘጋጀት ተገቢ ነው።
የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ  ያጋጥማል። ይህ ችግር ታሳቢ  ያደረገ ስራ በኢኮኖሚው መስክ መስራት ይገባል። መንግሥት በህልውናው ዘመቻ ላይ መሆኑን ከግምት በማስገባት የተባባሰውን የሕገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ ዝርፊያና ሕገ ወጥ ግንባታ በጥናት ላይ በተመሠረተ ሁኔታ በአስቸኳይ መግታትና አጥፊዎችን እንዲቀጡ ማድረግ፣ የተዛቡ አሠራሮችንም ማስተካከል፣ ክፍተቶችንም መድፈን ያስፈልጋል።
የሕዝብ ሰላም መናጋት ሊያጋጥም ይችላል።
2.6 የሶማሌ ክልል ሁኔታ
ከለውጥ አስቀድሞም ሆነ ለውጡ ከመጣ በኋላ ሕወሃት እጅግ ዘግናኝ የሆነ እልቂት ከፈጸመባቸው አካባቢዎች መካከል የሱማሌ ክልል ይጠቀሳል። በወቅቱ የነበረው የክልሉ ፕሬዝዳንት እና በምስራቅ ዕዝ አዛዥ በነበረው ሰው መካከል ተፈጥሮ የነበረው የጥቅም ትስስርና ከፍተኛ ሙስና ተበጣጥሶ፣ ክልሉ የሕወሃት የጥፋት እንቅስቃሴ መከወኛ መሆኑ እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ከመከላከያ ጎን በመሆን በምስራቁ ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የሕልውና ሥጋት በዋናነት ሲመክት የነበረው የክልሉ ሕዝብ ነው።
ምንም እንኳን ክልሉ በድንበር ከትግራይ ክልል ጋር የማይዋሰን ቢሆንም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ለተከፈተው የሕልውና ዘመቻ ከመከላከያ ጎን በመሆን በቁሳቁስ፣ በሰው ኃይልና በሞራል አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል። እንዲሁም ክልሉ ከድንበር ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያዋስናት ረጅም ድንበር በዚያ የሚገኝ እንደመሆኑ የጸጥታና ደህንነት አካላት በሰሜኑ ኢትዮጵያ በተጠመዱበት ወቅት ድንበር የመጠበቅ ኃላፊነት በክልሉ ሕዝብና ልዩ ኃይል ላይ ወድቋል። ከሕወሃትና መሰሎቹ ጋር የገባንበት ጦርነት ካበቃ በኋላ በክልሉ የሚኖረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ከሶስት ነገሮች ይመነጫል።
ይኸውም የአንዳንድ አማጽያን ረብሻ፣ ከሶማሊያ ጋር የሚኖረው ድንበር ሁኔታና ከአፋር ክልል ጋር የሚኖር ግጭት  ሊሆን ይችላል፡፡
 
2.7 የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁኔታ
ክልሉ እንደ ሌሎች ክልሎች በህልውና ዘመቻው ከፍተኛ አበርክቶ የነበረው ክልል ነው። በሕወሓት የእጅ አዙር ጥቃትም ገፈት ቀማሽ ነው። የሕዳሴ ግድብ የሚገኝበት ክልል እንደመሆኑ ሀገራችንን ለማጥቃት የተሰለፉ የውጭ ኃይላትን ትኩረት የሚስብ እንዲሁም በውጭ ኃይላት የሚታገዙ ሸማቂዎችም ጥቃት የሚፈጽሙበት ክልል ነው። የጉምዝ አማጺ ከሽብር ቡድኑ ሕወሃት እና ከጎረቤት ሀገር በሚያገኘው የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የጦር መሳሪያና የስልጠና ድጋፎች ተበረታትቶ በክልሉ በሚኖሩ በህፃናት፣ ሴቶች ንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጽምና ሲያፈናቅል ነበር።
ይኼንን ለመከላከልና ለመመከት የክልሉ አስተዳደርና ሕዝቡ ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍሏል። እንዲሁም ሀገራችን ከሱዳን ጋር ረዥም ድንበር የምትጋራው አንድም በዚህ ክልል በኩል እንደመሆኑ ኢትዮጵያን ሰላም ለመንሣት የሚያስቡ አካላት ክልሉን መሸጋገሪያ ስለሚያደርጉት ቀዳሚ የገፈቱ ቀማሽ በዚያ ክልል የሚኖረው ሕዝባችን ነው። ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷና የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ እንድትቆይ፣ ከጎረቤት ሀገራት የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት በኩል ዛሬ ብቻ ሳይሆን ለረጅም ዘመናት የክልሉ ሕዝብ አይተኬ መስዕዋትነት ሲከፍል የኖረ ሕዝብ ነው።
የሰሜኑ ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በድኅረ ጦርነት ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ ሁኔታዎች መካከል ክልሉ የሕወሐት ችግር መፍጠሪያ  አካባቢ ሊሆን ይችላል ይሆናል፡-
1. የውጭ ኃይላት ኢትዮጵያን ለማጥቃት ዋነኛ አማራጫቸው እየተደካመ መሆኑን ሲረዱ ኢትዮጵያን ለማጥቃት በቤኒሻንጉል ክልል በኩል የተለያዩ አማራጮችን መጠቀማቸው አይቀርም። የሕዳሴውን ግድብ ሥራ ለማስተጓጎልና የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለማወክ ይሞክሩ ይሆናል።:
2. ከሱዳን የሚነሡ ታጣቂዎች ወደ ክልሉ ሠርገው በመግባትና በክልሉ ካሉ አንዳንድ ፖለቲከኞች ጋር በመቀናጀት ከዚህም ጋር ተያይዞ ክልሉን እንዳይረጋጋ ለማድረግ መሞከራቸው አይቀርም።
2.8 የጋምቤላ ክልል ሁኔታ
የጋምቤላ ክልል በህልውና ዘመቻው ወቅት ቀጥተኛ የጦርነቱ ተጋፋጭ ባይሆንም ለዘመቻው መሳካት ግን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለውን ድንበር በመጠበቅና ድንበር ዘለል እንቅስቃሴዎችን በመከታተል ውጤታማ ሥራ ሠርቷል። ከዚህ በፊት በክልሉ ተንሠራፍቶ የነበረው የሕወሐት መረብ እንዲበጣጠስ በማድረግ አሸባሪው ሕወሐት በክልሉ ውስጥ መደበቂያ እንዳይኖረው አስችሏል። በድኅረ ጦርነት የጋምቤላ ክልል ሁኔታ የሚከተሉትን ሊመስል ይችል ይሆናል፡-
1. በጋምቤላ ክልል ያለው ዋነኛ ስጋት የስደተኞች ጉዳይ ነው። በድኅረ ጦርነት ወቅትም ኢትዮጵያን ማጥቃት የሚፈልጉ ኃይላት ይህን ጉዳይ እንደ አማራጭ በመጠቀም የክልሉን ፖለቲካዊ ሁኔታ ለማደፍረስ እንቅስቃሴን ሊያደርጉ ይችላሉ።
2. ሕወሓትና አጋሮቻቸው የውጭና የውስጥ ኃይሎች የደረሰባቸውን ሽንፈት አካክሰው አለን ለማለት ክልሉን የእጅ አዙር ጥቃት የሚያካሂዱበት አማራጭ ሊያደርጉት ይችላሉ።
3. ከደቡብ ሱዳን በኩል የሚገቡ ሸማቂዎች ክልሉን በመበጥበጥ ኢትዮጵያን ሰላም ለመንሣት ሊሞክሩ ይችላሉ።
2.9 ሲዳማ ክልል ሁኔታ
የሲዳማ ክልል በነበረው የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና የተጫወተ ነው። በሲዳማ ክልል ከድል በኋላ የሚኖረው ነባራዊ ሁኔታ እምብዛም የተለየና ሥጋት የሚፈጥር ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። ነገር ግን የሚከተሉት ሁኔታዎች መከሠታቸው አይቀርም፡-
1. ከሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ መስፋፋት ጋር የተያያዙ ፈተናዎች፣ በተለይ ደግሞ ወደ ኬንያ የሚገባው አውራ ጎዳና ማለፊያ ከመሆኑ አንጻር፤
2. ከዘመቻ ተመላሽ አካላትን ከማስተናገድ አንጻር፣
3. ሕወሓት ሊፈጥራቸው ከሚያስቡት የሽብር ጥቃቶች አንጻር ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሉ ሥጋቶች ሙሉ ለሙሉ የተቀረፉ ናቸው ማለት አይችልም። ስለዚህም ከድል በኋላ ደኅንነትን ለማስጠበቅ እና ፖለቲካውን ለማርጋት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
2.10  የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሁኔታ
ክልሉ አዲስ ቢሆንም በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ በህልውና ዘመቻው በሰው ኃይል በሎጀስቲክ ድጋፍና በመሳሰሉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ክልል ነው። ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ መጠን የተጠናከረ የፖሊስና ሌሎች ኃይሎች የሉትም። ነገር ግን ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበሩትን ችግሮች ክልሉ መውረሱ አይቀሬ ነው። ቀድመው የነበሩ የደኅንነት ችግሮች በድኅረ ጦርነት አለመረጋጋትን ለመፍጠር መጠቀሚያ ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይም ከዚህ በፊት በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ብሔሮች መካከል የነበሩ ግጭቶችና ከሌላ አካባቢ መጥተዋል ተብለው የሚታሰቡ ብሔሮችን የማጥቃት አዝማሚያ፣ ለሕወሐት የድኅረ ሽንፈት እንቅስቃሴ ምቹ ዕድል ሊፈጥሩ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ በአጠቃላይ በሀገራችን የተፈጠሩ ሥጋቶች በዚህ ክልልም ሥጋት ሊፈጥሩበት የሚችሉበት ሁኔታ አለ። በመሆኑም በየአካባቢው እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ለመፍታት ክትትል ማድረግ እና በአንክሮ መመልከት አስፈላጊነቱ የጎላ ይሆናል።
2.11  የሐረሪ ክልል ሁኔታ
የሐረሪ ክልል በሕልውና ዘመቻው ከመከላከያ ጎን በመሆን በሰው ኃይል፣ በሎጀስቲክስ አቅርቦት፣ በሞራል ፍጋፍና በመሳሰሉት ቀጣይነት ያለው አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል። በክልሉ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ሥጋት ሊያጭሩ የሚችሉ ጉዳዮች ከድል በኋላ ይከሠታሉ ተብሎ እምብዛም ባይጠበቅም፤ በሌሎች ቦታዎች ሊኖሩ የሚችሉ ጉዳዮች ሙሉ ለሙሉ ዝግ ናቸው ማለት አያስደፍርም። በተለይም ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ሊከሠቱ ይችላሉ። በክልሉ የሚገኙትን የሐረሪና የኦሮሞ ብሔሮች ከሥልጣንና ከጥቅም ጋር በተያያዘ ለማጋጨት ይሞከር ይሆናል። ከሃይማኖት በዓላት ጋር ተያይዘው የሚነሡ ረብሻዎች ለጠላቶቻችን መጠቀሚያ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም ሥጋቶችን ለመቅረፍ በጥንቃቄ ክትትሎችን ማድረግ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም የሕዝቡን አንድነት አስጠብቆ ለመጓዝ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል።
2.12 የድሬዳዋ አስተዳደር ሁኔታ
የድሬዳዋ አስተዳደር በሕልውና ዘመቻው ከመከላከያ ጎን በመሆን በቁሳቁስ፣ በሰው ኃይልና በሞራል አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል። በተለይም በድሬዳዋ የመከላከያ ሆስፒታል የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ቁስለኞች አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙ በጤና ባለሙያ፣ በአምቡላንስና በሌሎች የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች አስተዳደሩ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ እንደ ሐረሪ ከልል ሁሉ በድሬዳዋ አስተዳደር ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ሥጋት ሊያጭሩ የሚችሉ ጉዳዮች ከድል በኋላ ይከሠታሉ ተብሎ እምብዛም ባይጠበቅም፤ በሌሎች ቦታዎች ሊኖሩ የሚችሉ ጉዳዮች ሙሉ ለሙሉ ዝግ ናቸው ማለት አያስደፍርም።  አስተዳደሩ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው የገጠር ቀበሌዎች የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ ሊኖር ይችላል፡፡ በተጨማሪም በድሬዳዋ ካለው ብዝሃነት አኳያ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ሊከሠቱ ይችላሉ። በአስተዳደሩ የሚገኙትን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ከሥልጣንና ከጥቅም ጋር በተያያዘ ለማጋጨት ይሞከር ይሆናል። ከሃይማኖት በዓላት ጋር ተያይዘው የሚነሡ ረብሻዎች ለጠላቶቻችን መጠቀሚያ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም ሥጋቶችን ለመቅረፍ በጥንቃቄ ክትትሎችን ማድረግ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ከአጎራባች ክልሎች ጋር በቅንጅት መስራትና የሕዝቡን አንድነት አስጠብቆ ለመጓዝ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል።
2.13 የደቡብ ብ/ብ/ህዝቦች ክልል ሁኔታ
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለህልውና ዘመቻው መሳካት በሰው ኃይል፣ በሀብት ማሰባሰብና መደገፍ፣ በሎጅስቲክ አቅርቦት፣ የሕዝቡን የሞራል ድጋፍ በማስተባበር፣ የአከባቢውን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅና በመሳሰሉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በጦርነቱ የተጎዱ ህዝቦችን በመደገፍ ረገድም በተጨባጭ አጋርነቱን ያረጋገጠ ክልል ነዉ። በድኅረ ጦርነት ፖለቲካዊ ሁኔታም በክልሉ በጦርነቱ ወቅት ከነበረው እምብዛም የተለየ ነገር ላይ ይከሠታል ተብሎ አይታሰብም። ነገር ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያልተሳካላቸው ኃይላት በክልሉ ያሉ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን በማራገብ ክልሉን ወደ አለመረጋጋት ለመክተት እና የአመራሩን አንድነት ለማሳጣት ጥረቶችን ሊያደርጉ ይችላሉ። ስለዚህም የሚከተሉ ጉዳዮች ድህረ ጦርነት ወቅት በክልሉ ላለመረጋጋትና ለቀዉስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።
1. በክልልነት እንደራጅና ሌሎች የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ማነሣሣት፡- በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች በክልልነት ለመደራጀት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች አሉ። ከክልል መልስ ያሉት የሌሎች የአደረጃጀት ጥያቄዎች መቅረባቸዉም ይታወቃል። እነዚህን ጥያቄዎች ለሕዝብና ለሀገር በሚጠቅም መልኩ ለመመለስ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አሉ። የህልውና ዘመቻው ጦርነት በአሸባሪ ሕወሐት ተሸናፊነት መጠናቀቁ ያበሳጫቸው አካላት የክልልነት ጥያቄዎችን ለሀገር መበጥበጫነት ሊጠቀሙባቸው ይሞክሩ ይሆናል።
በመሆኑም እነዚህን ጥያቄዎች ከዚህ በፊት ከሕዝብ ጋር  የተጀመሩ ምክክሮችን በማጠናከር፣ በሰከነ ሁኔታ ለመፍታት የተጀመሩ ተግባራትና እንዲሁም በመነሻነት በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሠረት በብስለትና ኃላፊነት በተሞላበት አግባብ ለመመለስ መጀመር አለበት።በዚህ ሂደት የመንግስት ሰራተኛውና መላው ህብረተሰብ  የበኩላቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡
2. የብሔር ግጭቶች፡-ክልሉ በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ያሉበት ክልል ነው። እነዚህ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ለዘመናት ተግባብተውና ተዛምደው የኖሩ ቢሆኑም በፖለቲካ ልሂቃኑ የጥቅም ሽኩቻ የተነሣ ለግጭት ሲዳረጉም ታይተዋል። አሁንም ተዋሳኝ ብሔሮችን ማጋጨትና ከሌላ ቦታ መጥተው በክልሉ የሚኖሩ ብሔሮችን በማጥቃት ግጭት መቀስቀስ አንዱ የጠላቶቻችን ሤራ መፈጸሚያ ሊሆን ይችላል።
3. የከተማ ሽብር፡- ከአሸባሪው ሕወሐት ጋር አብሮ ሥልጣን ሊቆጣጠር ቋምጦ የነበረው ሸኔ እና ሌሎች የዉስጥ ተላላኪዎች ሕልማቸዉ መክኗል። በድኅረ ጦርነት በየአካባቢው የተበተነው ሸኔ፣ እንዲሁም የተለያዩ የህወሃት ተላላኪዎች ወደ ከተማ አሸባሪነት ይለወጥ ይሆናል።ይህ አሸባሪ ቡድን  በተለያዩ የክልላችን አካባቢዎች  የተለያዩ የውንብድና ሥራዎችን ሊፈጽም ይችላል፡፡ በተለይም ሰፋ ባለደረጃ የሽብር ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው የክልላችን አካባቢዎች ሁኔታውን ነቅቶ መከታተል ተገቢ ነው።
4. የተመላሽ ሠራዊትና ዘማች ቤተሰብ ጥያቄዎች መበራከት
ለህልዉና ዘመቻ በጣም በርካታ ወጣቶች ዘምተዋል።  በዚህም እንደሃገር የክልላችን አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነዉ። ጦርነት ነዉና ሰፋ ያሉ ለሀገራቸዉ የጀግንነት መስዋዕትነት ከፍለዋል።  ለሀገራቸው ለከፈሉት መስዋዕትናት ታላቅ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል። ኢትዮጸያ ሁሌም  ትዘክራቸዋለች። ከዘመቻ ተመላሹ ኃይልና የዘማች ቤተሰቦችም በተቻለ መጠን ደጋፍና እንክብካቤ ይሻሉ። ስለሆነም ይህንን በአግባቡ ለመፍታት  ከወዲሁ ካልተዘጋጀን የቀዉስ ምንጭ  ሊሆን ይችላል።
5. ከኬንያና ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚኖረው ድንበር ሁኔታ፡
በሰሜን ኬንያና ደቡብ ሱዳን የሚገኙ ማህበረሰብ አባላት ማህበራዊ መሰረታቸዉ አርብቶ አደሮች ናቸዉ።  ከደቡብ ኦሞ ዞን ካሉ ወረዳዎች በግጦሽ፣በዉሃ፣ በንግድ ትስስር እና በሌሎች ማህበራዊ ትስስሮች አብረዉ ለዘመናት የኖሩ ናቸዉ። አሁን አሁን ከተፈጥሮ ሃብት መመናመንና የአየር ንብረት መዛባት ጋር ተዳምሮ ለበርካታ ጊዜያት ወደግጭት እያመሩ እንስሳትን በመዘራረፍ፣ በመገዳደል ጉዳቶች ነበሩበት። በመቀጠልም አሸባሪዉ ጁንታና ተላላኪዉ ሸኔ አባላት ይህንን ድንበር የሽሽት መንገድ አድርገዉ በኬንያ ወደ ዉጪ አገር ለመዉጣት ይጠቀማሉ። በተጨማር የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴም ስጋት ነዉ።
3  ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ ድል አድርጋለች! በጦርነት የሚገኝ ድል ከጦርነቱ በኋላ ለሚመጣ መረጋጋትና ሰላም እንዲሁም የረዥም ጊዜ የሀገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና ይጫወታል።  በአጠቃላይ ከተሰለፍንበት ተግባር አንጻር በድህረ ጦርነቱ  ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል ምን እናድርግ የሚለው ጥያቄ መሰረታዊ ነው። የአንድነት፣ የምክክርና የመደማመጥ መንፈስን ማጠናከር፣ የአካባቢን ሰላምና ደህንነት ማጠናከር፣ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጣችን ከገባባት መፋዘዝ ማውጣት፣ ምርትና ማርታማነትን በማሳደግ፣ ቁጠባን፣ የስራ እድል ፈጠራንና ሌሎች ተዛማጅ አማራጮችን በማሳደግ ድህረ ጦርነት ኢኮኖሚው እንዲጠናከር መስራት እንዲሁም በጦርነቱ ለተፈናቀሉ አካባቢዎች ድጋፋችንን መቀጠልና የተጣራና ተዓማኒነት ያለዉን መረጃ ምንጭ መጠቀም ይጠበቅብናል።
Filed in: Amharic