>

ፋኖ ማለት እኮ... (አሳዬ ደርቤ)

ፋኖ ማለት እኮ…‼️

አሳዬ ደርቤ

➔ፋኖ እኮ ትምህርቱን፣ ሥራውን፣ እርሻውን ጥሎ ከቤቱ የወጣው ‹‹የመጣብን ጠላት በመደበኛ የጸጥታ ሃይል የሚመለስ ስላልሆነ ተደራጅተህ እራስህን እና ሕዝብህን አስከብር›› የሚል ጥሪ ከመንግሥት ቀርቦለት እንጂ መንግሥትን ለመውጋት አይደለም፡፡
➔ፋኖ እኮ በተወሰነ መልኩ ትጥቅ ማግኘት የቻለው የእነ ጌታቸው ረዳን “በከንቱ አትለቅ” የሚል ምክር ችላ ብሎ በክትክታ በትርና በአሮጌ ሚኒሽር ባደረገው ተጋድሎ የአገር አፍራሾችን ክላሽ ማርኮ እንጂ ሰሜን እዝን ወግቶ ወይም ደግሞ ከመከላከያ ሠራዊቱ ቀምቶ አይደለም፡፡
➔ፋኖ እኮ ከክልሉ ባለፈ ለኢትዮጵያ ቀጣይነት እራሱን ለመሰዋት የተዘጋጀ ሃይል እንጂ ዜጎችን የማጥቃትም ሆነ አገር የመውጋት ግብ ይዞ የተነሳ የጥፋት ቡድን አይደለም፡፡
➔ፋኖ እኮ ሕዝቡንና ክልሉን ከወራሪዎች ከመከላከል ውጭ የትኛውንም ክልልም ሆነ ሕዝብ የመውረር ዓላማ ያለው ጸረ ሰላም ሃይል አይደለም፡፡
➔ፋኖ እኮ ከመከላከያ ሠራዊቱና ከልዩ ሃይሉ ጎን ያለምንም ደምወዝ ተሰልፎ ደጀን ሲሆን የሰነበተ የወጣቶች አደረጃጀት እንጂ እንደ ኦ*ግ ወይም እንደ ት*ነግ ታጣቂዎች መደበኛውን የጸጥታ ሃይል ሲያባትል ወይም ደግሞ ሲገድል የከረመ የባንዳዎች ጥርቅም አይደለም፡፡
➔ፋኖ እኮ የመንግሥት ጥበቃ ከወራሪ ሃይል ሊያስጥላቸው ባልቻሉ አካባቢዎች ላይ በእራሱ ስንቅና ትጥቅ ተደራጅቶ በመውጣት ከአስገድዶ ደፋሪዎች፣ ከጨፍጫፊዎችና ከዘራፊዎች ጋር ግብግብ ሲገጥም የከረመ የደህንነት ሃይል እንጂ ሕግና መንግሥት ጠፋ ብሎ ንብረት ሲዘርፍና ሕይወት ሲጨፈጭፍ የከረመ የጥፋት ሃይል አይደለም፡፡
➔ፋኖ እኮ የመንግሥት አመራር ሕዝባቸውን ለወራሪ አስረክበው ሲጠፉ ቤተሰቡንና ሕዝቡን ለመጠበቅ ያለምንም ሥልጠና ከሞት ቀጠና ውስጥ ዘሎ የገባ የጀግኖች ስብስብ እንጂ፤ የክልሉንም ሆነ የፌደራሉን ሥልጣንና ወንበር መንጠቅ የሚያስብ የፖለቲከኞች ስብስብ አይደለም፡፡
➔ፋኖ እኮ ለፈጸመው ተጋድሎ ሽልማት ባይሰጠው እንኳን የምሥጋና መድረክ ተዘጋጅቶለት አድናቆት ሊቸረው የሚገባው የሀገር ባለውለታ እንጂ በስብሰባ መድረኮች ላይ ‹‹ኢ መደበኛ ሃይል›› ተብሎ በስጋት መልክ የሚወሳ አልነበረም፡፡
እናም እንዳጠቃላይ…
 ፋኖ የስጋት ምንጭ ሊሆን የሚችለው ክልሉ ድረስ ሄዶ አማራን የመግደልና የማፈናቀል እቅድ ላለው አካል ብቻ ነው፡፡
ሀገርን ለማዳን ከ150 ሺህ ታጣቂና ፋኖ ያዘመተው አማራ ላይ የተሰነደ የክሕደት ሰነድ…!!! 
አሸባሪው ሃይል የዘመቱበትን ጠላቶች ሲዘረዝር ከኤርትራ መንግሥትና ከፌደራሉ መንግሥቱ በመቀጠል የአማራ ክልልን በሦስተኝነት ያስቀምጠዋል።
መንግሥት ተብዬው አካል ግን በዚህ ሰነድ ላይ በመከላከያ ሠራዊቱ የተወከሉትን ሁሉንም ክልሎች በጦርነቱ አሳትፎ የትግሉ ባለቤት ካደረጋቸውና ካመሰገናቸው በኋላ ከአሸባሪው ቀጠና በባሰ መልኩ የአማራ ክልልን የስጋቱ ምንጭ ያደርገዋል።
ቆይ እኔ እምለው…
➔የአማራ ሕዝብ ልጆቹን ከጉያው አውጥቶ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ አላሳተፈም እንዴ?
➔ሠራዊቱ በገባበት ሁሉ እየገባ ሲቆስልና ሲሰዋ የከረመው የአማራ ልዩ ሃይል አይደለም እንዴ?
➔150 ሺህ ታጣቂና ፋኖ ያዘመተውስ የአማራ ክልል አልነበረም እንዴ?
➔ከሁሉም በላይ ደግሞ “ትግሉ አልተጠናቀቀም” ከማለት ባለፈ “ድሉ የእኛ ብቻ ነው” የሚል የድል ሽሚያ ውስጥ የገባ የአማራ ኤሊትም ሆነ አክቲቪስት ነበረ እንዴ?
እንዲህ ያለ የክሕደት ሰነድ አዘጋጅቶ ለውይይት የሚያቀርብ
አካልስ በአማራ ሕዝብ ዘንድ እንደ ጠላት እንጂ እንደ መንግሥት ሊታይ ይገባዋል ወይ?
Filed in: Amharic