እንደ ኢትዮጵያዊ ካለፈው ምን ተማርን? ለመጭው ትግልስ የምን ያህል እየተዘጋጀን ነው?
ፊልጶስ
ከወያኔ አገዛዝ እስከ አሳለፍነው ሶስት ዓመት በአገራችን የተፈጸመው፤ እኛን ባለቤቶቹን ብቻ ሳይሆን ጉረቤቶቻችንም የሚስተምር ነው። ታዲያ ”ጽድቅናውስ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” እንደሚባለው ሆነና፤ ካለፈው መማርና ተደራጅቶ የትግል ስልት መቀየስና መፍትሄ ማግኘት ቀርቶ፤ ገዥዎቻችን ከመከራ –መከራ እያላጉ፣ ከቀን– ቀን መከራችን እያበዙት ከአዙሪት አልወጥንም።
እንደ አገርና እንደ ህዝብ በአንድነት እንዳንቆምና ርስ–በርስ እንድንተላለቅ ፤ መሰረታዊ የችግራችን ምንጭ ከሆነው ውጭ፤ አጀንዳ እየተሰጠን፤ ከአጅንዳ ወደ አጅንዳ እንደ ፌንጣ እየዘለልን፤ አሁን ካለንበት የወያኔን እና የብልጽግናን ድርድር በአጀንዳነት ለመቀበል ደረስን።
ስንት አጀንዳዎች ተነስተው፣ ስንት አጅንዳዎች እንደተፍጸሙ፣ ስንት አጀንዳዎች በአገርና በህዝብ ላይ ቁስላቸውን ጥለው እንዳለፋና አሁንም እያቆሰሉ እንዳሉ፤ ስንት አጀንዳዎች እንደተተግበሩና ለህዝብ መፍትሄ እንዳስገኙ፤ ስንት አጀንዳዎች ከትውስታ ውጭ እንደሆኑ፤ የሚያውቅ ትላንትም ወያኔ፤ ዛሬም ተረኛው ኦነጋዊ–ብልጽግናና አጋሮቹ ብቻ ናቸው።
በዚህ ሰዓት እንኳን ባለፍት ወራቶች በጦርነት ስንለበለብ የተነሱት አጀንዳዎች የት ደረሱ?
– የጦርነቱስ ዓላማ ህዝብን አስጨርሶ ከወያኔ ጋር ለመደራደር ነወይ?
– ትላንት ምን ስትሉን ነበር? ዛሬስ ምን እያላችሁን ነው? ብሎ የህዝብንና የአገርን ጥያቄ የሚጠይቅና ፊለፊት የሚጋፈጥ ቡድንም ሆነ ዜጋ መጥፋቱ፤ ነፍሱን ይማረውና እንደ ደቡብ አፍሪካዊ ደራሲ፤ አለን ፒተን ”እሪ በይ አገሬ!” ያሰኛል።
ብቻ እንደ ግሪሳ ‘’ሆ! ‘’ እያልን፤ ተረኛው ማጠፊያው ሲያጥረውም ሆነ ህዝብን ማዘናጋት ሲፍለግ የሚሰጠንን እጀንዳ እይተቀበልንና እያራግብን፤ ”እኛ ብቻ እናውቅልሃለን” በሚል ግብዝነት፡ በህዝብና በአገር ላይ ሲቆመር፣ አጥንት አደተጣለለት ውሻ፣ በአጥንቱ ርስ–በርስ እየተባላን፤ አገራችን የጎሰኞችና የሥልጣን ፍርፋሪ ለቃሚዎች መጫዎቻ አደረግናት።
ህዝብ ምንም በማያውቀውና በማያገበው ጉዳይ የመከራው ሁሉ ገፈት ጨላጭ ሆኖ፤ ገዥዎቻችንና መስሎቻቸው፤ ከዚያ መከረኛ ገበሬ ከሚጎርሳት ነጥቀው በሰበስቧት ግብር ይምነሸነሻሉ፣ ጮማ ይቆረጣሉ፤ ውስኪ ይራጫሉ።
ማን ነበር፤ “‘ ለቆረጡት ስጋ፣ ላፈሰሱት ጠጅ
ከፋዩ አንተ ነህ፣ በርትተህ ሥራ እንጅ።”—-ያለው
ካለፈው ግንዛቤ ወስደን አሁን ያለንበትንም ሆነ የወደፊት ትግላቻን አቅጣጫ እንዲኖረው፤ ወደ ኋላ መለስ ብለን ሃቁን ቀለል ባለ መንገድ እንመልከት፤
ወያኔን ወደ መቀሌ እንዲፈረጥጥ ያደረገው ትግል ፤ ወያኔ ”በጋራ ጠላትነት” ይፈረጅ እንጂ፤ ትግሉን ያካሂዱት ወይም ይመሩት የነበሩት የፓለቲካ ቡድኖችና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ዓልማቸው ወይም ግባቸው በርግጥም ”እሳትና ጭድ ” ነበር። ይህን ለመረዳት አሁን ያለውን የወቅቱን የአገራችንን የፓለቲካ ጨዋታ ማየት በቂ ነው።
ከወያኔ ከአዲስ አበባ መሸኘት በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የኋላ – ኋላ ሁለት ጎራዎች በገሃድ ወጡ፤
አንደኛው/ የወያኔን የበላይነትና በነሱ ጎሳዎች ላይ ያለው የፈላጭ ቆራጭነት የታገሉ፤ ነገር ግን ህገ –መንግሥቱንም ሆነ የጎሳ ክልላዊ አስተዳደሩን የሚቀበሉ ፤ ካስፈለገም አንቀጽ 39 ተጠቅመው ለመገንጠል የሚሹ ሲሆኑ በውጭም ሆነ በአገር ወስጥ የተደራጁ ከኦዲድ ጋር አበረው ይሰሩ የነበሩት የኦሮሞ ብሄርተኞች ለጥገናዊ ለውጥ የሚታገሉ ነበሩ።
ሁለተኛው/ የወያኔ ህገ–መንግስትና የጎሳ ክልል አይደለም አመለካከቱም መወገድ እንዳለበት የሚሰብኩና የጎሳ ፓለቲካ በአገሪቱ እንዲጠፋ የሚፈልጉ፡ በኢትዮጵያ አንደነትና ሰንደቅ ዓላማ የማይደራደሩ ስር–ነቀል ለውጥ ለማምጣት ቃለ የገቡ ነበሩ።
የትግሉ ውጤትም ከወያኔ በኋላ ስንመለከትው የኢህአዲግ ክንፍ የሆነው ኦህዲድ፤ ከጎሳ ፓለቲካ አራማጆች ጋር የለውጡ ቁንጮና አሸናፊ ለመሆነ በቃ። በርግጥ ቤተመንግስቱን የተቆጣጠረው ኦህዲድ ከውስጥም ሆነ በውጭ መፈረካከስ ቢደርስበትም ዛሬ የወያኔን መንገድ ተከትሎና ስሙን ወደ ብልጽግና ቀይሮ፣ ብአዲንን የጋሪ ፈረስ አድርጎ፣ ለስር- ነቀል ለውጥ እንታገላልለን ይሉ የነበሩትን በአጃቢነት አስከትሎ፤ በጠ/ ሚ አብይ አህመድ አማካኝነት ኢትዮጵያዊነት እየተሰበከ፤ በተግባር ግን በኦሮማማ የበላይነትና በፍጹም ተረኝነት እየገዛ ይገኛል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ?
– ከልዮነት እንደንት፣ ከጎሰኝነት ኢትዮጵያዊነት አይበልጥም ወይም ለእድገትም ሆነ አብሮ ለመኖር አይመረጥም ወይ?
– ብዙሃኑ የኢትዮጵያዊያን ፍላጎትስ ይህ እየደለም ወይ? ልንል እንችላለን።
መልሱ በጎሳ የሚያምኑና ለኢትዮጵያዊነት ጥላቻ ያላቸው፤ ኢትዮጵያዊነትን ከሚያቀነቅኑና ኢትዮጵያን እንወዳለን ከሚሉት የበለጥ የተደራጁ፣ያደራጁ፣ የዓላማ ጽናትና ቁርጠኝነት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ቤተ–መንግሥቱን ተቆጣጥረው የአገሪቱና የህዝቡ አደራጊና ፈጣሪ ለመሆን የበቁ ናቸው።
የኢትዮጵያዊንተና የአንድነት ኃይሎች፡ በተለይም ከወያኔ በኋላ በበኦነጋዊ ብልጽግና ዘመን የሰሯቸው የኢትዮጵያን ህዝብ አንገት ያስደፋ ስህተቶች ወይም የፈጽሟቸው ክህደቶች አሁን ላለንበት ኢትዮጵያንም ያለባለቤት፤ ህዝብንም ያለ መሪ እንዲቀር አደርጎታል።
በለውጡ ማግሥት ውጭ ያሉ መሣሪ ያነሱም ሆነ ያላነሱ ወደ አገር ቤት ገብተው የለውጡ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከተጋበዙት ውስጥ ግንቦት ሰባት የአርበኞች ግንባርና ኦነግ ይገኙበታል። ኦነግ ከነሙሉ ትጥቁና ወታደሮቹ ወደ አገር ቤት ሲገባ፤ ግንቦት ሰባት የአርበኞች ግንባር ግን ሙሉ ትጥቁን አስረክበ። ይህም ”ልጅና የጀራ ልጅ ” መኖሩን ለኢትዮጵያም ህዝብ ሆነ ለግንቦት ሰባት የአርበኞች ግንባር የሚያስረዳ ነበር። ኦነግ ይባስ ብሎ የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም ባንክ መዝረፍና የአማራን ህዝብ ማረድ ሲጀምር፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቁሚያለሁ የሚለውና ተስፋ የተደረገለት የአሁኑ ኢዜማ ፤ የያኔው ግንቦት ሰባት የአርበኞች ግንባር ”አብይና ህገወጡ ከንቲባ ታከለ ኡማ እሻጋሪዋቻችን ናቸው” በማለት የትግሉን አቅጣጫ ቀየሩት፤ የእንድነት ኃይሉንም ያለ ድርጅትና መሪ መቅረቱ ተጋለጠ። የኦነጋዊ ብልጽግናማ ማንም የሚገዳደረው ኃይል እንደሌለ በመገንዘብ ፤ የኦሮማማን የበላይነት የሚያረጋግጡ ርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ።
– የእዲስ አበባን ህዝብ ከንቲባ የሚመርጥበት ግዜ ሲደርስም ፤ ጠ/ሚ አዲስ ህግ አጸድቀው ታከለ ኡማን በምክትልነት ሾሙለት። የአዲስ አበባንም ዲሞግራፊ መቀይረ በይፋ ተጀመረ። ኢዜማ አዲስ አባባ ውስጥ ያለው ድጋፍ ተጠቅሞ ከኦሮማማ ያተርፈናል ሲባል፤ ይባስ ብሎ ፤ ለመታገል በባልደራስ ስም የተደራጁትን እነ አቶ እስክንድር ”ህገ–ወጥ” ናቸው በማለት በኦሮሞ ሚዲያ ቀርበው ማውገዝ ጀመሩ። ከዚያን ግዜ ጀምሮ ኢዜማ ከብልጽግና ካድሪዋች ባለተናነስ ማገልገሉን ተያያዘው። ከዚያ በኋላማ የስር-ነቀል ለውጥ አራማጆች የኦሮማማን ቂጥ በመከተል፤ ምንም ዓይነት የዲሞክራሲ ተቋማት በሌለበትና የሰው ልጅ እንደከብት በሚታረድበትና የአገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ በወደቀበት ሰዓት ሁሉ ፤ ለኦነጋዊ ገዥ ኃይል እውቅና ለመስጠት በምርጫ በመሳተፍ አሁን ላለንበት ደረጃ አደርሱን።
ከዚህ ላይ ኢዜማም ሆነ ለስር–ነቀል ለውጥ እንትገላለን ይሉ የነበሩ ለግዜያዊ የሥልጣን ጥቅም ብለው የኢትዮጵያን ህዝብ ከዱ ወይስ ተሳሳቱ? ይህን ለህዝብ ልተወው።
አሁን ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ፤
የጠ/ሚ አብይ አገዛዝ የሚከተለው መንገድ ግልጽ ነው፤ ይኽውም በወያኔና በኦነጋዊ –ብልጽግና ድሮም ሆነ አሁን በኢትዮጵያና በተለይም እነሱ አማራ በሚሉት ህዝብ ላይ ያላቸው ዓላማና ግብ አንድ መሆኑን አስመስክረዋል። ለትዝብት ጠ/ሚ ከጦር ሜዳ አንደተመለሱ ፍጹም ተጠያቂነትና ኃላፊነት የጎደለው ግራም ሆነ ቀኝ ፤ ኋላም ሆነ ፊት የሚያዩት ሥልጣናቸውንና የኦሮማማ የበለያነትን መሆኑን ያረጋገጡበትንና ህዝብን ለማዘናጋት በየግዜው የሚሰጡትን አጀንዳና የሚፈጽሙትን ክህደት እንመልከት፤
– ጦሩ ባለበት እንዲጸና ታዟል። ጦርነቱ በድል ተጠናቋል ፤ ጦርነቱ ግን አሁንም ቀጥሏል። ቁምነገሩ ግን አሁንም መሰዋት የሚከፍለው የጎንደር፣ የወሎና የአፋር ህዝብ ነው። ይህ ደግሞ የሚፈለግ ነው።
– እነ የእቶ ስብሃትን መፈታት ስንሰማ እኛም ደንግጠናል፤ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ” ሁሉም ኃይል ተጠሪነቱ ለጠ/ ሚ ነው” የሚለው አዋጅ ማነው ያስነገረው? ይህ የህዝብ ንቀታቸውና ተራ ቅጥፈታቸው ግን ያማል።
– ”መስቀል አደባባይን እንውረስ”= ይህች ደግሞ ዜጋው በነ እቶ ስበሃት መፈታት ልቡ እንደቆሰለ አቅጫ ለማስቀየርና በሌላ በኩል ደግሞ የኦርቶዶድክስ ሃይማኖትን አቅም ለመፈተን የተዘጋጀች አጀንዳ ነች። ‘’በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ።”
– ”ድህረ ጦርነት” ሚሥጥራዊ የብልጽግና ሰነድ፤ ይህ ደግሞ አስቂኝ ነው። ጦርነቱ በድል መጠናቀቁን እያበሰረ፤ በጦርነት ወቅት የተሳተፍትን እና አሁንም በጦር ሜዳ ከወያኔ ጋር የሚተናነቁትን ትጥቅ ስለማስፈታት እየዘበዘብ፤ ከኦነግ ሸኔ ጋር ሆኖ አማራን ስለሚያርደው የኦሮሚያ ልዩ ሃይል አስፈላጊነት ይተርካል። በነገራችን ላይ የአማራ ብልጽግና የሚባለው በርግጥ ለስብሰባ እንኳን ይጠሩታል?
”አረሱት አሉ የሁመራን መሬት፡ ያውም የእኛን እጣ
እነሱ ምን ያርጉ ከኛ ሰው ሲታጣ።” አይደል ያለው ዘፋኝ።
– የወያኔና የመንግስት ድርድር፤ አዲሱ አጀንዳ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ለህዝብ እንዲደርስ የተደረገው የወያኔና የኦነጋዊ ብልጽግና ድርድር አስፈላጊነት ነው። ከዚህ አጀንዳ ላይ ደግሞ የአሜሪካ ተጽኖ በጨውነት ተጨምሯል። ”’ስለ ኢትዮጵያ ከሆነ አንገቴን እሰጣለሁ” ተረስቷል፤፤
ታዲያ ህዝቡ ስለ ጦርነቱ ሳያልቅ መጠናቀቁ፣ ስለነ ስበሃትም መፈታት፣ ስለ መስቀል አደባባይ፣ ስለ ፋኖና የእማራ ልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታታ፤ ከወያኔ ጋር ስለመደራደርና ከሽብርተኝነት መዝገብ ስለ ማንሳት፤ በአጠቃላይ ሁሉም አጅንዳዎች ባለቤቱ ኦሮማማው ኦነጋዊ ብልጽግና ነው። ነገ ከነገ ወዲያ ኦነጋዊ ብልጽግና የሚፈልገውን ያደርጋል፤ የማይፈልገውን ይክዳል ወይም ይሽራል፤ እንደተለመደው ”ለኢትዮጵያና ለህዝብ አንደንት ተብሎ ነው” የሚል አሰልች ሃተታና ሰበካ እንሰማለን።
ግን ለምን ? በጎሳ የተደራጁ ቡድኖች እንዴት በዚች ታላቅ አገር ላይ እንዲህ እንዲፈነጩና የህዝቡንም መከራ እንዲያበዙበት ፈቀድን??
ለዚህ ተጠያቂዎች እኛ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! የምንል በመሆናችን ከምንግዜውም የበለጠ ኃላፊነት መውሰድ አለብን። ከስሜታዊ ነት እንውጣና አገራችንና ህዝባችን የተደቀነበትን የህልውና አደጋ በቅጡ እንገንዘብ። እነሱ እገርና ህዝብ ለማፍራስ ተድራጅተው ሲሳካላቸው፤ እኛስ ‘’በደምና በአጥንት ለተገነባችው አገርና ወገናችን እንዴት መደራጅትና በእንደንት መቆም ያቅተናል?’’ ብለን ራሳችን እንጠይቅ።
አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ ምክክር ወይም ድርድር ቢባል እንኳን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚወክልና ጎሰኞችን የሚገዳደር አንድም ጠንካራ ድርጅት የለም። ዛሬ ማስተላለፍ የተፈለገው ከለፈው ተምረን ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታ አገናዝበን በየ’ለንበት ቦታ ሁሉ ፤ ሁለትም ሶስትም በመሆን፤ መነሻችንም ሆነ መድራሻችን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አድርገን እንደራጅ! ከተድራጀንና ከታገልን ለድል የማንበቃበት ምክንያት የለም።
ወያኔዎች የሚፈነጩብን ስለተደራጁና ስለታገሉ ነው። ኦነጋዊያን ቤተ–መንግሥቱን ተቆጣጥረው የሚፈነጩብን ስለ ተደራጁ ስለ ታገሉ ነው። ይህን ሃቅ መቀበል አለብን። በተለይ በዚህ ሰዓት ተደራጅቶ በአንደንት ለህልውና ከመታገል ውጭስ ምን አማራጭ አለን?
አዶልፍ ኤችማን የናዚ ጀኒራል ነበር፤ ከጦርነቶ በኋላ ራሱን ደብቆ በአርጀንቲና ሲኖር፤ የአይሁድ ጋዜጠኛ ለፍርድ ለማቀርብ ይፈለገው ነበርና ከዓመታት በኋላ አገኘው። አይሁዳዊ ጋዜጠኛ ለኢንችሚን ያቀረበለት ጥያቄ ”ምን ዓይነት አመለካከት ቢኖራችሁ ነው ጀርመን ዓለምን መግዛት ይችላል ብላችሁ የተነሳችሁት?” የሚል ነበር።
ኢችሚን ተረጋግቶ” መጀመሪያ ላይ ዓለምን ለመግዛት የሚስችሉን ነገሮች ነበሩን፤ በኋላ ግን እነዚያ ዓለምን ለመግዛት የሚያስችሉን ነገሮች መፈረካከስ ጀመሩ፤ ስለዚህም ተሸነፍን።” አለው።
”እነዚያ የተፈረካከሱ ለመሸነፋችሁ ምክንያት የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?” ሲል አይሁዳዊ ጋዜጠኛ ጠየውቀ።
”መደራጀት፡ የዓላማ ጽናትና ዲስፕሊን ናቸው” አለው።
አዎ! እኛም ከተደራጀን፣ የዓላማ ጽናት እና ዲሲፕሊን ካለን ፤ አሁን ከተደቀነበን የህልውና አደጋ በድል አድራጊነት በመወጣት ፤ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን የማንታደግበት ምንም ምክንያት የለም። እናም እንደራጅ! የዓላማ ጽናትና ዲሲፕሊን ይኑረን!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!
Email: philiposmw@gmail.com