>

በምስራቁ የሀገራችን ክልል  2.4 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ ርግብ ተጋልጧል፤ እንስሳትም እያለቁ ነው (ታደለ ዘውዱ)

በምስራቁ የሀገራችን ክልል  2.4 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ ርግብ ተጋልጧል፤ እንስሳትም እያለቁ ነው!!
ታደለ ዘውዱ

በምስራቁ የሀገራችን ክልል ከዚህ በፊት ከታዩት የድርቅ አደጋዎች ሁሉ በከፋ ሁኔታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እንስሳት እየሞቱ ነዋሪዎችም እየተፈናቀሉ  ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የህዝብን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል…።
በተከሰተው የከፋ ድርቅ የሚሊዮን አርብቶ አደሮች የኑሮ መሰረት የነበሩት እና ሀገራችን ኢትዮጵያን በቀንድ ከብት በአፍሪካ አንደኛ ያስባሉት እንስሳት እንደ ቅጠል መርገፍ ጀምረዋል…፡፡
የድርቁ አደጋ ቀን ከቀን የከፋ፣ ብርቱውን አርብቶ አደር የፈተነ፣ የእናቶችን ጓዳ ያራቆተ፣ በህፃናት ላይ የሞት ጥላውን አጥልቷል…።
የሶማሌ ፈጣን መረጃ ምንጭ እንደጠቆመን 2 እና 3 ቀናት እህል ያልቀመሱ እናትና ህፃናትን መመልከት፣ ነፍስ ለይተው የማያውቁ ህፃናት ለቅሶ፣ “ቤታችን እሳት ከነደደበት”… ቀናት ተቆጠረ የሚሉ የእናቶች በረሃብ የሰለለ የተማፅኖ ጥሪ፣ ከብቶች እና እንስሳት የሚላስ የሚቀመስ አጥተው አጥንትና ስጋቸው ተጣብቆ ለመነሳት አቅም አጥሯቸው በየቦታው ወድቆ ማየት፣ውሃ ሳያገኙ ረጅም ቀናት መቆየት የሚችሉት ግመሎች በየሜዳው ወድቀው ማየት ያለፉት 3ወራት የለት ተእለት ክስተት ነው…።
የድርቁ ከባድነት ከቤት እንስሳዎች አልፎ የዱር እንስሳትም በየሜዳው እና ጢሻው ወድቀው ለሚያይ ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ልብን ሰርስሮ የሚዘልቅ የህመም ስሜትን ያሳድራል….፡፡
የክረምት ዝናብ ባለመጣሉ ተስፋ የተደረገበት የበልግ ዝናብ በቀረበት በዚህ ወቅት ይህ አይነት አስከፊ እና ከዚህ ቀደም ገጥሞ የማያውቅ እልቂት እየደረሰበት የሚገኘው ህዝብ በቀጣዮቹ ወራት ምን ሊገጥመው እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ሆኖበት በተስፋ መቁረጥ ከአከባቢው መፈናቀል አማራጭ የሌለው ከድጡ ወደማጡ የሆነ ነገር ሆኖበታል…. ፡፡
ድርቁ ከፍተኛ በመሆኑ 2.4 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥረት መጋለጡና እንስሳትም በድርቁ ሳቢያ እያለቁ በመሆኑ በጦርነት የተጎዱትን አካባቢዎች ና በድርቅ አደጋ ላይ የወደቀውን ህዝባችንን ልዩ ትኩረትና ህይዎት አድን ርብርብ እናድርግ መንግስት፣ዜጎች፣ እርዳታ ለጋሾችና በመላው አለም የምንገኝ ዲያስፖራዎች እና ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ  እንረባረብ….።
ርሃብ ጊዜ አይሰጥም፤ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ለወገኖቻችን ፈጥንን እጃችንን እንዘርጋ….።
Filed in: Amharic