“ከመክዳት መከዳት ይሻላል ….!!!”
መስከረም አበራ
*…. መንግስት አማሮች ተከዳን ይላሉ ሲል ሰነድ የፃፈውም እንዲሁ ከዚህ ቀደም በአማራ ሃይሎች ላይ ያደረገውን እና ወደፊትም ሊያደርግ ያሰበው የክህደት መጠን ራሱን ጭምር ስለሚረብሸው ነው፡፡ለአማራ ሃይሎች መካድ አዲስ አይደለም፡፡
ጦርነት የጨረሰ የመሰለው የብልፅግና መንግስት ከሰሞኑ የድህረ-ጦርነት ሰነድ አዘጋጅቶ ሲመክር ሰንብቷል፡፡ ባለፊልድ ማርሻሉ መንግስት ጦርነት አለቀ የሚባለው መቼ እንደሆነ እንኳን የሚያውቅ አይመስልም፡፡ፊልድ ማርሻሉም እስትንፋስ ያለው ሁሉ የሚገነዘበውን የመንግስት እንዝላልነት ለመደበቅ “ስለጦርነት ለማውራት አርባ አመት በጦር ሜዳ መቆየት ያስፈልጋል” ብለው ተገላግለዋል፡፡
መንግስት በእንዝላልነቱ ያመጣው ጉዳት ከዚህ መልስ አይባልም፡፡ የሃገር ውስጡ ቀውስ ቀርቶ ምዕራባዊያኑን የህወሃት ጠበቃ ያደረጋቸው መንግስት ጦርነቱን የያዘበት የምንግዴ አያያዝ ነው- በመሃል አበባ መትከሉ፣ፓርክ ማሰማመሩ ወዘተ፡፡ መንግስት በስተመጨረሻው ጭራሽ የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጌያሁና ወያኔ የፈለገውን ያድርግ ብሎ ምንም ባልተዘጋጀው የአማራ ሃይል እና የሃገር መከላከያን በሚያስንቅ ደረጃ በታጠቀው የትግራይ ሃይል መካከል የሚደረገውን ትንቅንቅ የኬንያ ወይም የዩጋንዳ መንግስት እንደሚያደርጉት ባለ ዝምታ መታዘብ ጀመረ፡፡በዚህ አስተዛዛቢ ሰሰዓት በጦር ሜዳው መሃል እሳት ላይ የነበረው በዚህ የከዳተኞች ሰነድ ስጋት ተደርጎ የተፈረጀው በራሱ ስንቅና ትጥቅ ሲዋጋ የነበረው ፋኖ ነው፡፡
መንግስት ከጦርነቱ በኋላ በአማራ ክልል የድል ሽሚያ ፣ባለቤትነትና የተከዳሁ ስሜት ይንፀባረቃል የሚለው የሰራውንና ሊሰራ ያሰበውን ስለሚያውቅ ነው፡፡ የድል ሽሚያ የሚለው የኋላቀር ሃገር መንግስት መሆኑ በሰጠው የራሱን እውነት የመፍጠር ጉልበት ተመክቶ እንጅ ሶስት አራት ወር ሙሉ ብቻውን ከወያኔ ጋር ሲተናነቅ የነበረው ፋኖ ከማን ጋር ነው ድል የሚሻማው? የሃገር መከላከያ ሰራዊት ራሱ እጃችንን ይዞ ያወጣን የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሽያ ነው ሲል የመሰከረለት አካል ድል ለመሻማት ምን አደከመው? መንግስት የድል ሽሚያ የሚለው ወያኔን አሁን ያለችበት ቦታ ለማድረስ የአማራ ሃይሎች ያደረጉትን የማይተካ አስተዋጽኦና መንግስት ያሸነፈ ሲመስለው የአማራ ሃይሎችን አመድ አፋሽ ለማድረግ የሚያጣድፈውን የራሱን አመል ስለሚያውቅ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ እውነቱ ግርግዳ ላይ በትልቁ ተፅፏል!
መንግስት አማሮች ተከዳን ይላሉ ሲል ሰነድ የፃፈውም እንዲሁ ከዚህ ቀደም በአማራ ሃይሎች ላይ ያደረገውን እና ወደፊትም ሊያደርግ ያሰበው የክህደት መጠን ራሱን ጭምር ስለሚረብሸው ነው፡፡ለአማራ ሃይሎች መካድ አዲስ አይደለም፡፡
ክህደቱ በቀራቀርና ሰሮቃ የአማራ ሃይሎች ያደረጉትን ጠሚው ራሳቸው ያመኑትን ድል በሳምነቱ ሽምጥጥ አድርጎ በመካድና በአካባቢው ያልነበሩትን የሌላ ክልል ልዩ ሃይሎች በማመስገን የተጀመረ ነው፡፡ መንግስት ራሱ የለኮሰው ጦርነት ተጋግሞ የአማራ ክልልን ማንደድ ሲጀምር “ጦር መውደድ ጥሩ አይደለም ፓምና ትራክተር ውደዱ” የተባለበትን ክህደት የሚስተካከል ክህደትስ ከወዴት አለ? ወደፊት በራያ፣ወልቃይት ባለቤትነት ላይ የሚደረገው ክህደት ደግሞ የቀድሞውን ሁሉ እንደሚያስረሳ ግልፅ ነው፡፡
ይህ ሁሉ የተደረገበትና ወደፊትም ምን እንደተሰነቀለት የማይታወቀው የአማራ ህዝብ ተከዳሁ ማለቱ ስለማይቀር አስቀድመን “በቅርቡተከዳሁ ይላል” ብለን እናሳፍረውና መከዳቱን በሆዱ ይዞ ዝም አንዲል እናድርገው ነው የቀድሞ መጮሁ ሚስጥር …..
የሆነው ሆኖ የአማራ ህዝብ የሚከዳው “ጨቋኝ፣ቅኝ ገዥ” ብሎ በፈረጀው የወያኔ ሰልፈኛ ብቻ አይደለም-በራሱም ልጆች ጭምር እንጅ፡፡ የአማራ ህዝብ ቆምኩልህ የሚሉት ከአብራኩ የወጡ ልጆቹ ሳይቀሩ ዶሮ ሳይጮህ ስድስት ጊዜ የሚከዱት፣የጠላቶቹ ረዥም እጅ በሆነ ክልላዊ መንግስት ግዞት ውስጥ ለዘመናት የኖረ ህዝብ ነው፡፡ጦር ሰብቆ በወያኔ ላይ ሲዘምትም ክህደት እንደሚከተል አጥቶት አይደለም-ጠላትን መቀነሱ ደግ እንደሆነ ስለሚያውቅ እንጅ!
የሆነ ሆኖ የክህደቱ ሰንሰለት ርዝመትና የከሃዲው ብዛት ለአማራ ህዝብ እውነተኛይቱን የነፃነት መንገድ ይፈልግ ዘንድ ይረዱታል እንጅ ብርቱ ክንዱን፣ጠንካራስነ-ልቦናውን አያጥፉትም፡፡