>

እነ እስክንድር ነጋ ከፍተኛ ጦርነት የተደረገበትን የሊማሊሞ ግንባር ጎበኙ (ጌጥዬ ያለው- ከሊማሊሞ)

እነ እስክንድር ነጋ ከፍተኛ ጦርነት የተደረገበትን የሊማሊሞ ግንባር ጎበኙ
ጌጥዬ ያለው (ከሊማሊሞ)

 

“ወያኔን ከአማራ ብቻ ሳይሆን ከትግራይም እናጠፋዋለን” ሻለቃ ሰፈር መለሰ
በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች የፋኖ ወታደራዊ አደረጃጀቶችንና በጦርነቱ ጀብዱ የሠሩ ጀግኖችን እየጎበኘ የሚገኘው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ልዑክ ከወራሪው የትግራይ ሃይል ጋር ከፍተኛ ፍልሚያ የተደረገበትን የሊማሊሞ፣ ዘሪማ፣ ጨው በር  ግንባርን ዛሬ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ጎብኝቷል። ቡድኑን በክብር ተቀብለው ያስጎበኙት የፋኖ ብርጌድ መሪ በመሆን ጦርነቱን እየመሩ የሚገኙት ሻለቃ ሰፈር መለሰ ናቸው።
“ይህ ነብራ ተራራ ይባላል። ብዙ ገድል የተሠራበት ነው። ብዙ መስዋዕትነት የከፈልንበት ነው። ጀግኖች ልጆቼን (ወታደሮቸን ማለታቸው ነው) አጥቸበታለሁ። ወያኔዎች ዙሪያውን ቆፍረው ገደል ውስጥ ገብተው አንገታቸው ብቻ ነበር የሚታየን። ድል አድርገን ግን እዚያው ጉድጓድ ውስጥ ቀብረናቸዋል። ፋኖን በጣም ይፈሩታል። ሰፈር አንድ ብርጌድ ፋኖ መርቶ እየመጣ ነው ሲባል ነው ገና መሸሽ የጀመሩት። ይህንን ራሳቸው ወያኔዎችም ያወራሉ” ብለዋል ጀግናው የጦር መሪ ሻለቃ ሰፈር።
“የትግራይ ወራሪ ሃይል አማራን ሊያጠፋ እንጂ ሊገዛ አልነበረም የመጣው። ወያኔዎች ድጋፍ የላቸውም። ለምን እንደሚወሩም አይገባኝም። ለራሱ ሊገዛ ሳይሆን ለሌላ ቅኝ ገዥ ለመሥጠት ነው የሚዋጋው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ እንኳን አማራ ላይ ትግራይ ላይም ተከታትለን እናጠፋዋለን። አሁን ቁሙ ተብለን ነው የቆምነው” ሲሉም ጨምረዋል። የባልደራስ ልዑክ በረሃ አቆራርጦ መጥቶ በመጎብኘቱም ምስጋና አቅርበዋል። “እስክንድርና ጓደኞቹ እንደ ሻማ እየቀለጣችሁ የታገላችሁ” በማለትም ገልፀዋቸዋል።
የባልደራስ ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ በበኩላቸው “እኛ የከፈልነው መስዋዕትነት ከእናንተጋር ሲነፃፀር ኢመንት ነው። የእኛ የፈሪ ጀግንነት ነው። የእኔ በተለይ የፈሪ ጀግንነት ነው። እውነተኛው ጀግንነት የእናንተ ነው።
የአሜሪካ ወታደር እንኳን ቢመጣ ከዚህ ተራራ ውስጥ መሽጎ የተቀመጠን ሃይል ያስለቅቃል ለማለት ይከብደኛል። ይሄን ምሽግ ሰብሮ ማስለቀቅ ታላቅ ጀግንነት ነው” ብለዋል።
“ሰፈር  መለሰ አሁን በፋኖ አደረጃጀት እንደሚጠራበት ሻለቃ አይደለም። ፍትሕ ቢኖር ኖሮ ጀኔራል ነው። እናም ጀኔራል ብየ እጠራዋለሁ” ሲሉም በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ውስጥ ሆነው ተናግረዋል።
ሰፈር መለሰ ወያኔ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ከመግባቱ አስቀድሞ የጫካ ትግል ያደርግ ከነበረበት ጀምሮ ሲዋጋው የኖሩ አርበኛ ናቸው። በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜም በተደጋጋሚ ለመግደል ሞክረው ወያኔዎች ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በአንድ ወቅት በአየር ላይ ከነሰራዊታቸው በአየር ላይ ሊደበድቧቸው ሔሊኮፍተር አብርረው ቢሄዱም ሔሊኮፍተሯ በዚያው ተማርካ ቀርታለች።
እኒህ ጀግና በተመሳሳይ ዘንድሮ በተደረገው ጦርነትም የቡድንና የጦር መሳሪያዎችን የማረኩ ሲሆን  በምርኮ የተገኘችውን ‘ፒ ክ አፕ’ መኪናም ተጉዘንባት አይተናታል።
በቦታው በተገኘው የባልደራስ ልዑክ ቡድን ፕሬዚደንቱ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም (ቀለብ)፣ አስካለ ደምሌ እና ሌሎችም  ተገኝተዋል።
“ከሕወሓት ጋር ለ30 ዓመታት በፖለቲካ ታግለናል። አሁን አጀንዳው ተቀይሮ ኢትዮጵያን የማፍረስና የማስቀጠል ሆኗል። እንደ ቀድሞው ለፍትሕ፣ ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲ አይደለም። ይህ ግልፅ መሆን አለበት። ሕዎሓት አዲስ አበባ ቢገባ መንግሥት አይደለም የሚቀይረው፤ ኢትዮጵያን ነው የሚያፈርሰው” ብለዋል አቶ እስክንድር።
የባልደራስ የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል በበኩላቸው “እስር ቤት ውስጥ ሆነን ፋኖዎች ያሉበት የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ገብተን የምናመሰግናቸው መቼ ነው እያልን እንጓጓ ነበር። ማወቅ ያለባችሁ እኛም ጠመንጃ የሌለን ፋኖዎች መሆናችንን ነው። መንፈሳችን አንድ ነው። ጀኔራል ሰፈር የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስታውስህ ኢትዮጵያን በማዳንህ ነው። እኛ ብቻ አይደለንም ገና መጭው ትውልድ ሲያመሰግንህ ይኖራል። የአማራ ታሪክ ኢትዮጵያን ማዳን ነው” ብለዋል።
የፓርቲው አመራር አባል የሆኑት ወ/ሮ አስቴር ስዩም (ቀለብ) “በእናንተ ተጋድሎ ነው ዛሬ በሰላም ቁሜ ይህንን ንግግር የማደርገው።  የኢትዮጵያ ጠባቂዎች ናችሁ። ግፈኞች ሲወጓት እናንተ ኢትዮጵያን አድናችኋልና አመሰግናችኀበለሁ። ወያኔ ኢትዮጵያን እየጠሏት ነው ሲመሯት የነበሩት። የውጭ ወራሪዎችና ወያኔ አማራን ከመውጋት ወደ ኋላ አይሉምና ትግሉ ይቀጥላል። አብረን እንታገላለን” ብለዋል።
“እጅግ በጣም ኮርተንባችኋል። ኢትዮጵያ የምትድነው በእናንተ በፋኖዎች፣ በአማራ ሚሊሻና በአማራ ልዩ ሃይል ነው” በማለት የሴቶች አደረጃጀት ሓላፊዋ ወ/ሪት አስካለ ደምሌ።
የድርጅቱ የገንዘብ አደረጃጀት ሓላፊዋ ወ/ሪት ዘቢባ ኢብሪሒም በበኩላቸው
“በጣም አስገራሚ ድል ነው ያየነው። በጣም ሙቀት ነው። ጧትና ማታም ብርዱ በእዚያው ክል ነው። ይህንን ሁሉ ተቋቁማችሁ ነው መስዋዕትነት የከፈላችሁልን” በማለት አመስግነዋል።
ልዑክ ቡድኑ እስከ ትግራይ የአስተዳድር ወሰን ድረስ የዘለቀ ሲሆን የጠላት ጦር የሰፈረበትን ቦታ ከሩቅ አሻግሮ ተመልክቷል። መሀል ላይ የጦር ስልጠና የሚያጉ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትን ተመልክቷል። የተኩስ ድምፅም እንደ ጅራፍ ድምፅ በአካባቢው ተለምዷል። በየመንገዱ የወደቁ የዲሽቃ፣ የመድፍና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችንም ተመልክተናል። በረሃው ውስጥ ያሉ አስተኛ ከተሞች የወታደር ካምፕ ይመስላሉ።
Filed in: Amharic