>

"በኋላ ማጣፊያው እንዳያጥራችሁ...!!! "  (መስከረም አበራ)

“በኋላ ማጣፊያው እንዳያጥራችሁ…!!! ” 

መስከረም አበራ

እንደ እኛ በመንግስቱም ሆነ በኑሮው የማይደሰት ማህበረሰብ መፅናኛው አምላኩ ነው::አምላኩን የሚገናኘው ደግሞ በእምነት ቦታው ነው፡፡ የመጨረሻ መፅናኛውን አምላኩን እንዳይገናኝ የተከለከለ ደስታ አልቦ ህዝብ ምንም ሊያደርግ ይችላል፡፡ የባህርዳሩ አባት ለነገስታቱ ባስተላለፉት ደርዝ ያለው ንግግር “በኋላ ማጣፊያው እንዳያጥራችሁ” ያሉት ይህን ማለታቸው ነው፡፡ የአባታችንን ምክር እዚህ ላይም ልድገመውና በዘረኛ አምባገነን  መንግስት ስር ያለ  ደሃ ህዝብ መፅናኛው አምላኩ ነው፤የበደላችሁትን በደል ሁሉ ችሎ የሚኖረው በአምላኩ የመፅናኛ ድምፅ ነው፡፡ ይህን የአምላኩን የመፅናኛ ድምፅ እንዳይሰማ ርካሽ ጠመንጃችሁን እየተኮሳችሁ  ከረበሻችሁት እሳት ሆኖ ይበላችኋል! በኋላ ማጣፊያው እንዳያጥራችሁ !
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ላይ የሚደረገው ግፍ ምንጩ ምን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኗ  ይዋከብ ዘንድ፣ይሳደድ ዘንድ ፣ይገደል ዘንድ ፣ ከተቻለም ይጠፋ ዘንድ የታወጀበት መከረኛው የአማራ ዘውግ ንብረት ነች ብሎ የሚያስበው የአስተሳስብ ዝግመት ያለበት አስተምሮ ውጤት ነው ይሄ ሁሉ ግፍ፡፡
እውነቱ ግን ቤተክርስቲያኗም ተልዕኮዋ ሰማያዊ እንጅ ዘውጋዊ አይደለምና የአስተሳሰብ እድገት ውስንነት ባለው አስተዳደር ጠመንጃ የሚጠፋ አለመሆኑ ነው፡፡ ስልጣን በድንቁርና ላይ ሲደረብ የማይነካውን በአስር ጣት ገብቶ የማቡካት እብሪት ላይ እንደሚደርስ ቢገባኝም ይሄኛው ግን በዛ ! ቤተክርስቲያኗም የበዛ ትዕግስቷን የተረዳላት የለምና ክብሯን ለማስጠበቅ መነሳት አለባት፡፡ሲበዛ ያቅራል!
Filed in: Amharic