ሸንቁጥ አየለ
አንድ መንግስት ለሚመራዉ ህዝብ በጣም የሚጠነቀቅ:የሚጨነቅ እና የህዝቡን ስነልቦና ላለመጉዳት የሚችለዉን ሁሉ ማድረግ የሚችል ከሆነ ብቻ ረዥም ጊዜ በህዝብ ልብ ዉስጥ የመቆዬት እድል ይኖረዋል::
የብልጽግና መንግስት ግን ለሚመራዉ ህዝብ የማይጨነቅ: ለራሱ መንግስት የማይጠነቀቅ:ግዴለሽ እና በራሱ ላይ ሽብር ያወጀ መንግስት ነዉ::በዚህም እራሱን ከዉስጡ ቦርቡሮ የበላ መንግስት ነዉ::ሆኖም የብልጽግና መንግስት እንዳይወድቅ አንድ ቁልፍ ነገር ደግፎ ይዞታል::ይሄዉም ሀገራዊ ተቃዋሚ ሀይል የለዉም::
————-
የአማራ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉት
——————
የብልጽግና ተቃዋሚዎች በአጠቃላይ ሲታዩ ቀልደኛ ተቃዋሚዎች ናቸዉ::የአማራ ተቃዋሚ ነን የሚሉት በአንድ ገበታ ከብአዴን ጋር ቁጭ ብለዉ እየበሉ በሌላ እጃቸዉ ደግሞ ብልጽግናን/ኦህዴድን እንቃወማለን ባዮች ናቸዉ::አንዳንዶቹ አክራሪ ተቃዋሚ ነን ቢሉ እንኳን ከብአዴን ጋር ያላቸዉ ግንኙነት ከመረቁ አዉጡልኝ ከስጋዉ ጾመኛ ነኝ የሚል አይነት ነዉ::ሁለተኛዉ የአማራ ተቃዋሚዎች ትልቁ ድክመት ደግሞ እራሳቸዉን ባህርዳር ላይ የወሰኑ መሆናቸዉ ነዉ::
ትግላቸዉ ከምኒሊክ ቤተመንግስት የተቆረጠ ራዕይን ያነገበ ነዉ::የሚሰባሰቡት እና የሚፎክሩት አማራ ክልልን እያሰቡ መሆኑ ነዉ::ስለዚህ የአማራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ ወገን ብአዴን በጎን አንቆ በርቀትም በቅርበትም ስለያዛቸዉ ከዚያም በላይ ከመረቁ አዉጡልኝ ከስጋዉ ጾመኛ ነኝ አይነት ከብአዴን/ብልጽግና ጋር የደም ትሥስር ይሁን የአስተሳሰብ ትሥስር ዉስጥ ስለገቡ የስነመንግስት ጥያቄያቸዉ ጎሃ ጺዮንን የሚያሻገር አልሆነም::ግፋ ቢል በደሴ አቅጣጫ ተጎዞ ፍላጎታቸዉ የሚያርፈዉ ደብረብርሃን ከተማ ላይ እየሆነ ተቸግረዋል::

አምስት ሆነዉ ቢሰበሰቡ ሶስቱ ግዴለም ዛሬ ብአዴን እናግዘዉ እና ወደፊት ብአዴን ሲጠነክር እኛም ጠንከር ያለ ተቃዋሚ እንሆንበታለ የሚሉ ግራ ግብት ያላቸዉ ብዙሃን ናቸዉ::እናም ብልጽግና ከአማራ ተቃዋሚዎች በኩል የሚመጣ የስነመንግስት ግፊያ ከቶም አያሰጋዉም::የስነ መንግስት ይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳበት እስካሁን ከአማራ ተቃዋሚዎች በኩል ከቶም አልደረሰዉም::የብልጽግና መንግስትም ይሄን በደንብ የተረዳዉ ይመስላል::
——————
ሀገራዊ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉት
————————-
ሌላዉ ብልጽግና እድለኛ የሆነበት ነገር ሀገራዊ ተቃዋሚ ፓርቲ ፈጽሞ መጥፋቱና መዳከሙ ነዉ::ቀድሞ ኦነግ መር የሆነዉን ግንቦት ሰባት እየደበላለቀ የሀገራዊ አንድነት ፓርቲ ነኝ ሲል የነበረዉ ግንቦት ሰባት/አሁን ኢዜማ በአስተማማኝ የብልጽግና ዋና ክንፍና አካል ሆኗል::
አሁን በራሱ እግር የቆመ: አጠቃላይ ኢትዮጵያዉያንን ሊያንቀሳቅስ የሚችል(የብልጽግና ደጋፊዎች:የህዉሃት ደጋፊዎች:የኦህዴድ ደጋፊዎች: እና የብአዴን ንክኪዎችን ሳይጨምር ማለት ነዉ) ኢትዮጵያዊ ሀገራዊ ፓርቲ አለመኖሩ ለብልጽግና ቁልፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል:: ቢጠቀምበት ይሄ ለብልጽግና ትልቅ ከሰማይ የወረደ ጸጋ እና አጋጣሚ ነበር::በዚህ ረገድ ብልጽግና ላይ ምንም የሚያሰጋዉ አንዳች ስጋት አልነበረም::እዚህ እና እዚያ ተበታትነዉ የሚገኙት እኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኞች በራሳቸዉ ክፋት እና ምቀኝነት እንዲሁም ለሰላሳ አመታት እርስ በርሳቸዉ ስለተቆሳሰሉ እንኳን ተሰባስበዉ ህዝብ ሊሰበስቡ ይቅርና እራሳቸዉ ተሰባስበዉም ለመነጋገር ተቸግረዋል::
ይሄን ሁሉ ጸጋ የተላበሰዉ የብልጽግና መንግስት ግን በራሱ ጊዜ ትግሉን ከራሱ መንግስት ጋር በማድረግ ኢትዮጵያዉያንን ማስከፋት:ማሸበር:ማዋከብ እና ማስጨነቅን እንደ ቁልፍ የስነ መንግስቱ ማስቀጠያ መሳሪያነት እየተጠቀመበት ይገኛል::በአጭሩ በራሱ መንግስት ላይ እራሱ ሽብር እያደረገ ማንኛዉም ተቃዋሚ ሊያደርስበት ከሚችለዉ የመናጋት ጫና የከፋ ጫናን እያደረገ የሚገኘዉ የብልጽግና መንግስት የስነ መንግስት ሚስጢር ገና ምንም አልተገለጠለትም::
ጠቅለል ሲደረገ የራሱን መንግስት በራሱ እጅ የሚያሸብረዉ እና በራሱ ላይ ጫና በማድረግ እራሱን ለማፍረስ እየተወራጨ ያለዉ የብልጽግና መንግስት ያልተረዳዉ የስነ መንግስት ሚስጢር ብዙ ነዉ::የስነ መንግስትን ሚስጢር ለመረዳት እና ለመማር ባለመፈለጉም የራሱን መንግስት በራሱ እጂ ቦርቡሮ የሚጥለዉ እራሱ ብልጽግና ይሆናል::ይሄም የሚሆነዉ ህዝቡን ፈጽሞ በማስከፋት እና ህዝባዊ የመተፋት ቁጣን በራሱ ላይ በማዝነብ ይሆናል::በተቃዋሚ በኩል ግን ብልጽግና እድለኛ ነዉ::