>
5:13 pm - Monday April 18, 4844

"ድፍረት ያጣው የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ንጽጽር  ...!!!"  (አቻምየለህ ታምሩ)

“ድፍረት ያጣው የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ንጽጽር  …!!!” 
አቻምየለህ ታምሩ

እስራኤል ሰራሽ ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪ የታጠቀው በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኦሕዴድ/የኦሮሞ ብል[ጽ]ግና ፖሊስ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የለበሰ ታቦት አጃቢ አናሳልፍም ብሎ በግፍ ስለረሸናቸው ንጹሐን ዶ/ር ድሉ ዋቅጅራ ‹ታጥቦ ጭቃ፣ አድሮ ቃሪያ› በሚል ርዕስ የሚሰማውን የገለጸበትን ጽሑፍ አንድ ወዳጄ በውስጥ መስመር ልኮልኝ አነበብኹት።
ዶ/ር በድሉ ጽሑፉን ሲደመድም “ታቦት ያጀበ ምእመን ላይ የሚተኩስ (በምንም ምክንያት ይሁን) የጸጥታ ኃይል፣ መስጊድና ቤተክርስቲያን በመድፍ ከደበደበው ትሕነግ የከፋ ነው” በማለት ይቋጫል።
ይህ የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የመደምደሚያ ሀሳብ ከላዩ ሲታይ ገላጭ ይመስላል። ብዙ የማኅበራዊ ሜዲያ ተጠቃሚም እየተቀባበለ ሲያጋራው ተመልክቻለሁ። ሆኖም ግን “ታቦት ያጀበ ምእመን ላይ የሚተኩስ (በምንም ምክንያት ይሁን) የጸጥታ ኃይል፣ መስጊድና ቤተክርስቲያን በመድፍ ከደበደበው ትሕነግ የከፋ ነው” የሚለው የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ድምዳሜ ሶስት ነገር ይጎድለዋል።
የዶ/ር በድሉ ድምዳሜ የመጀመሪያው ጉድለው የንጽጽር ፍሰት ጉድለት ነው። ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የለበሰ ታቦት አጃቢ አያሳየኝ ያለው የዐቢይ አሕመድ ኦሕዴድ/የኦሮሞ ብ[ል]ጽግና ያሰማራውን ምዕመኑን በጥይት የቆላውን የጸጥታ ኃይል ማን እንደሆነ ሳይገልጽ በስም ያልገለጠው የጸጥታ ኃይል የሚነጻጸርበት ግን ትሕነግ ብሎ በስም ይጠቅሳል። በስም ያልተገለጠን የጸጥታ ኃይል ስሙ ከተገለጠ ኃይል ጋር ማነጻጸር ሥነ አመክንዮ አስተሳሰብ (ሲሎጅዝም) ይጎድለዋል።
የዶ/ር በድሉ ድምዳሜ  ሁለተኛው ጉድለት የሎጂክ ዝንፈት ነው። ዶ/ር በድሉ ታቦት ያጀቡ ምዕመናንን ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪ ታጥቆ የረሸነውንና ስሙን ያልገለጠውን በዐቢይ አሕመድ የሚመራው ኦሕዴድ/የኦሮሞ ብል[ጽ]ግና ያሰማራውን “የጸጥታ ኃይል” ያነጻጸረው ከትሕነግ [እኔ ፋሽስት ወያኔ እያልሁ ነው የምጠራው] ጋር ነው። ይህ የዶ/ር በድሉ ንጽጽር ፈረንጆቹ comparing apples to oranges fallacy የሚሉት የFalse equivalence ሎጂክዊ  ዝንፈት ነው። ዶ/ር በድሉ ትሕነግ እንደ ጭካኔ መለኪያ ካነሳ [መነሳትም አለበት] ትሕነግን ማወዳደር ያለበት ከዐቢይ አሕመድ ኦሕዴድ/የኦሮሞ ብል[ጽ]ግና ጋር እንጂ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የለበሰ ምዕመን እንዳታሳልፍ የሚል ትዕዛዝ ተቀብሎ ከተሰማራው ፖሊስ ጋር መሆን የለበትም።
በሌላ አነጋገር ዶ/ር በድሉ ነገሩን አህያውን ትቶ ዳውላውን አድርጎ እስራኤል ሰራሽ ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪ አስታጥቆ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የሰለሰ ሰው ድርሽ እንዳይል የሚል ስምሪት የሰጠውን በዐቢይ አሕመድ የሚመራውን ኦሕዴድን/የኦሮሞ ብል[ጽ]ግናን ትቶ ትዕዛዝ የተቀበለውን የጸጥታ ኃይል ጭካኔ ሊነግረን ከፈለገ “የጸጥታ ኃይል” ሲል የገለጸውን  ኃይል ማወዳደር ያለበት ትሕነግ ከሚያሰማራው የጸጥታ ኃይል ጋር እንጂ ከዋናው አሸባሪው ትሕነግ ጋር መሆን የለበትም።
ባጭሩ የአሸባሪው ትሕነግ ጭካኔ መወዳደርና መነጻጸር ያለበት ከዋናው  ከኦሕዴድ/ኦሮሞ ብል[ጽ]ግና ጭካኔ ጋር እንጂ አቻ ካልሆነውና ስምሪት ወስዶ ከተሰማራ የጸጥታ ኃይል ጋር መሆን የለበትም።
የዶ/ር በድሉ የድምዳሜ ሀሳብ ሶስተኛው ጉድለት ድፍረት ማጣት ነው። በኔ እምነት የቋንቋው ሊቅ፣ የተዛነፉና ሥነ መዋቅር የጎደላቸውን የአደባባይ ሙግቶችና ክርክሮች ባለፉት ዓመታት ሲያሄስ የምናውቀው ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ከፍ ሲል የጠቀስኳቸውን ሁለት ጉድለቶች ይፈጽማል ብዬ አላምንም። ስሙን ያልጠራውን የጸጥታ ኃይል ስሙን ከጠራው አካል ጋር ማነጻጸር ሥነ አመክንዮ የተከተለ አስተሳሰብ አለመሆኑን፤ አሸባሪው ትሕነግ መወዳደር ያለበት ከአቻው በዐቢይ አሕመድ ከሚመራው ኦሕዴድ/የኦሮሞ ብል[ጽ]ግና ጋር እንጂ አሸባሪውን ትሕነግን ትዕዛዝ ተቀብሎ ከተሰማራው ፖሊስ ጋር ማወዳደርና ማነጻጸር የሎጂክ ዝንፈት እንደሆነ ዶ/ር በድሉ ይስተዋል ብዬ አላስብም።
በኔ እምነት ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በጽሑፉ የንጽጽር ፍሰት ጉድለት ያሳየውና የሎጂክ ዝንፈት የፈጸመው በዐቢይ አሕመድ የሚመራውን ኦሕዴድ/የኦሮሞ ብል[ጽ]ግና አረመኔነት ከአቻው፣ ከጭካኔና ከርዕዮተ አለም ታላቅ ወንድሙ ከፋሽስት ወያኔ ጋር ለማወዳደር ድፍረቱን በማጣቱ ነው። በዓሉ ግርማ እንዲህ ይላል፤ ‹ድፍረት የሌላት ብዕር – ወረቀት ባታበላሽ ይመረጣል። ከአድርባይ ብዕር ባዶ ወረቀት ብዙ ይናገራል››። ታላቁ ገብረ ሕይዎት ባይከዳኝም “ያገራችን ጸሐፊዎች በነገሮች ላይ ኀጢአት ይሠራሉ፤ በትልቁ ፈንታ ትንሹን ይመለከታሉ፤ ለእውነት መፍረድን ትተው በአድልዎ ልባቸውን ያጥባሉ” ሲል ተችቷል። ድፍረት ያጣውና ሚዛን የሳተው የዶ/ር በድሉ ጽሑፍም እንደዚያ ነገር ይመስለኛል።
Filed in: Amharic