>
5:21 pm - Monday July 20, 2212

‹ታጥቦ ጭቃ፣ አድሮ ቃሪያ...!!!›  (ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ)

‹ታጥቦ ጭቃ፣ አድሮ ቃሪያ…!!!› 

ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ

 

*….. ኢትዮጵያ ውስጥ የማያጋጭን፣ የማያዋጋን፣ የተቀበልነው ልዩነት ግለሰባዊ መጠሪያ ስማችን ብቻ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት፣ የማንነት ልዩነት፣ የሀይማኖት ልዩነት፣ ሰንደቅ አላማና ህገመንግስት ላይ ያለን ልዩነት፣ ወዘተ. በሙሉ ህይወት የሚጠፋበት ግጭት ውስጥ ይከተናል፡፡ 
ልዩነታችን ሲሻል መበሻሸቂያ፣ ሲከፋ መጋጫ ነው፡፡ ከወያኔ አገዛዝ ጀምሮ እስካሁን እንደሚታየው ደግሞ፣ አብዛኞቹ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት/ተቋማት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ በተመሳሳይ ፖለቲካዊ አመለካከት ስር የተደራጁ ቡድኖች፣ . . የመበሻሸቁና የግጭቱ መሪ ተዋንያን ናቸው፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከበቂው በላይ ፈተና ላይ ነን፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የሞተው፣ የወደመው የትየለሌ ነው፡፡ ኢኮኖሚው እየተንገታገተ የኑሮ ውድነቱ ፈተና ሆኗል፡፡ የመንግስት አካላትና የሀይማኖት ተቋማት በዚህ ወቅት የሚጠበቅባቸው የዜጎችን ፈተና ማቅለል እንጂ ማክበድ አይደለም፡፡ ባለፈው ሳምንት በመስቀል አደባባይ በሀይማኖት ጉባኤ ስም የተፈጠረው ሁከት፣ በጥምቀት በአል የሰንደቅ አላማ አጠቃቀም ላይ የተነሳው ውዝግብና በጸጥታ ሀይሎች ‹‹አረንጓዴ÷ቢጫና  ቀይ የለበሰ ታቦት አጃቢ አናሳልፍም›› ሰው መሞቱና መቁሰሉ፣ ካለንበት ሁኔታ አንጻር የማይጠበቅ፣ ለዜጎችና ለሀገር አለማሰብና አፍራሽ ተግባር ነው፡፡  በመንግስት የሚታዘዝ የጸጥታ ሀይል፣ እንኳን የሀገራቸውን የጠላትንም ባንዲራ ቢለብሱ፣ ታቦት አጅበው በሚሄዱ ምእመናን ላይ አስለቃሽ ጭስና ጥይት እንደምን ሊተኩስ እንደሚችል ሊገባኝ አይችልም፡፡ የጸጥታ ሀይል የማንን ጸጥታ ነው የሚጠብቀው? ታቦት ያጀበ ምእመን ላይ የሚተኩስ (በምንም ምክንያት ይሁን) የጸጥታ ሀይል፣ መስጊድና ቤተክርስቲያን በመድፍ ከደበደበው ትህነግ የከፋ ነው፤ ትህነግ ሽብርን አውጆ የተነሳ ሲሆን፣ የጸጥታ ሀይሉ ሰላምህን እጠብቃለሁ ባለው ህዝብ ላይ ነው ይህን የሚፈጽመው፡፡ ‹ታጥቦ ጭቃ፣ አድሮ ቃሪያ› እንዳይሆን ይህ ጊዜ ሳይሰጠው መታረም አለበት፡፡
Filed in: Amharic