>

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንና አማኞቿ ላይ የሚደረግን ወከባና እንግልት አጥብቀን እናወግዛለን..  !!! (መኢአድ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንና አማኞቿ ላይ የሚደረግን ወከባና እንግልት አጥብቀን እናወግዛለን..  !!!
ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ባሳለፋቸው ረጅም የትግል ዓመታት የሕዝብ ሰላም መከበር ዋነኛውና ተቀዳሚው ፍላጎታችንና ተግባራችንም አድርገን ለዚሁ መረጋገጥም ስንታገልና ዋጋ ስንከፍል ቆይተናል ።
ይሁንና ለዘመናት የታገልንለት እና ብዙም ዋጋ የተከፈለበት ነገር ሁሉ የኋልዮሽ ፈርጥጦ ከ2008 ዓ.ም ከነበረው ወደባሰ መራር የትግል ጊዜ እየመለሰን እንደሆነም እየተረዳን መጥተናል፡፡
ለዚህም ማሳያዎቹ መንግስት ስፖንሰር የሚያደርገው በሚመስለው መልኩ በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከናወን መንፈሳዊ ዓመታዊ የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ በሁሉም ከተሞች እና ገጠር አብያተ ክርስቲያናት የተከበሩ የጥምቀት በዓል አከባበር በየአካባቢው አስተዳደር በተዳረገ መልካም ፍቃድ ሁሉም በሚባል ደረጃ በጣም ሰላማዊ ሆነው ውለዋል፡፡
ይሄ ማሳያው መንግስት ከሕዝባዊ በዓላት ላይ እጁን ሲያወጣ ህዝባችን በምን ያክል መከባበርና ሥርዓት እንደሚያሳልፍ፣ በጅጅጋ፣ በሐረር፣ በድሬደዋ፣ በጅማ አጋሮ፣ በአርሲ፣ በአሰላ፣ በሆሳዕና ወዘተ ከዚህ ቀደም በሰላም የመከበር እድላቸው አናሳ በሆነባቸው አካባቢዎች የአካባቢው አስተዳደርና ፀጥታ ኃይሎች የሚያደርጉትን ትንኮሳና ሽብር
አቁመው በተቃራኒው ህብረተሰቡን ከስጋት ይጠብቁ ስለነበር የጥምቀት በዓሉን የሌላ እምነት ተከታዮችም እንኳን ሳይቀሩ ደስ በሚል ኢትዮጵያዊ አንድነትና ትብብር ሲያከብሩት አስተውለናል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ በቡራዩ ወይብላ ማሪያም የተፈፀመው አሰቃቂ የሽብር ተግባር በመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ያስገነዝበናል፡፡ ይሄ ድርጊት ደግሞ ህዝብን ከመንግስት እየለየ ወደ መረረ ትግል ውስጥ ያስገባዋል እንጂ ከዚህ ድርጊት መንግስት ምንም ጠብ የሚል ትርፍ አያስገኝለትም፡፡
ስለሆነም እንደ መኢአድ መረዳት የሕዝባችን ሰላም የሚናጋው መንግስት በሚያሰማራቸው የመንግስት ፀጥታና ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ስለሆነ በአስቸኳይ መንግስት እጁን ከእንዲህ አይነት ድርጊቱ እንዲሰበስብና በመሪው አንደበት ለይምሰል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ሀገር ናት ኦርቶዶክስን መንካትና ማፍረስ ሀገርን መንካትና ማፍረስ ነው ብሎ ተረድቶ ሀገርን ከማፍረስ እንዲታቀብ እያሳሰብን፤ ከዚህ ቀደም በእንደዚህ አይነት ሀገር አፍራሽ ትንኮሳና የሽብር ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ የፀጥታ አካላትን በአስቸኳይ አጣርቶ ለህዝብ ይፋ የሆነ አስተማሪ እርምጃ መውሰድና በትዕዛዝና በአስፈፃሚነት የተሳተፉ የመንግስት ከፍተኛና የበታች አመራሮች ላይም ግልፅና አስተማሪ እርምጃ ወስዶ የአማኙን ምዕመን እንዲያረጋጋ እናሳስባለን፡፡
በተለይም ደግሞ በዘንድሮው የቃና ዘገሊላ በዓል አከባበር ወቅት በቡራዩ ከተማ ወይበላ ቅድስት ማሪያም እና ቅዱስ ሚካኤል ታቦተ ሕጉን ወደ መንበር ለመመለስ በሥርዓት ላይ በነበረበት ወቅት አርማ የሌለው ሰንደቅን በሚል ሰበብ የማይነካውን በመንካትና የእምነቱን ሥርዓት በመድፈር በምዕመናን ላይና በዘማሪያን አገልጋዮች ላይ የተወሰደው ወታደራዊ የግድያ እርምጃ እጅግ ዘግናኝና አደገኛ ስለሆነ፤ ይህም እንዲፈፀም የሆነው ሆን ተብሎ በበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ የታቀደ እንደነበር የሚያመለክተው ፖሊስ በኦፊሻል የፌስቡክ ገፁ ላይ አውጥቶ ከጥቂት ቆይታ በኋላ እርማት የሰጠው የበዓል አከባበር ወቅት ሊደረጉ የተከለከሉ መመሪያዎች ውስጥ አርማ የሌለው ባንዲራ የሚል አረፍተ ነገር መሰንቀሩ አንዱ ለተፈፀመው ችግር በር ከፋች ድርጊት ሆኖም አግኝተነዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ድርጊቱ መንግስትን ቀጥተኛ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡
ወደ ከፋ ትግል እየገባን እንደሆነ የሚያሳየን ደግሞ ከዚህ ቀደም በባንዲራ ምክንያት የሞትነውና የተገደልነው በውጭ ወራሪ እንጂ ሀገራችንን በሚመራ አካል ተገድለን አናውቅም፡፡
ዛሬ ግን ይህቺን የብዙ ጥቁሮች የነፃነት አርማ የሆነች አባት፣ አያቶቻችን የወደቁላትን ሰንደቅ ዓላማ ጣሊያን በሚጠላት ልክ መንግስትም እንደሚጠላት ማሳያው እሷን ያዛችሁ ብሎ በጥይት ደብድቦ መግደል ደረጃ ደርሷል፡፡ በዚህም ምክንያት የሕዝብን ትዕግስት የሚፈታተን ድርጊት እየፈፀመ ነው፡፡
ሌላው ከዚህ ጋር የተያያዘውና መቆም ያለበት አስተሳሰብ ለአጀንዳ ማስቀሪያ መንግስት የሚከተላቸው ጭር ሲል አልወድም በሚል እሳቤ የተሳሳተው መንገድ ሰሞኑን በመስቀል አደባባይ ተፈጥሮ የነበረው የመንግስት ድብቅ እጅ የገባበት ኃይማኖትን ከኃይማኖት አጋጭቶ የቀውስ አትራፊ የመሆን መጥፎ አባዜ መስቀል አደባባይ ላይ የሚነሳ በጣም ሥሱ የሆነ ኃይማኖታዊ ጥያቄ እንዳለና የከዚህ ቀደሙም የአፍጥር ፕሮግራም ምን ያክል መንጫጫት እንደፈጠረ መንግስት ጠንቅቆ እያወቀ ነገሮች ተባብሰው በሀገራችን ላይ በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመርጨት ስለሆነ ችግሮች ወደከፋ ደረጃ እንዳይደርስና ህዝባችን ሰላም እንዳያጣ ከማድረግ ይልቅ ይባስ ብሎ በከንቲባ ደረጃ በሥፍራው በመገኘት የሕዝብን ስሜት የሚያባብስ ድርጊት ላይ ተጠምዶ መገኘት ሀገርን ወደ ብጥብጥ የሚወስድ ሕገ-ወጥ ተግባር መሆኑን እየገለፅን፣ በፀጥታ ኃይሎች ጥቃት ለተፈፀመባቸው ቤተሰቦችና የእምነቱ ተከታዮች በእጅጉ ያዘንን መሆናችንንና መፅናናትንም እየተመኘን፤
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሚከተሉትን ጥሪዎች ያቀርባል፡-
1ኛ.  መንግስት በአስቸኳይ እጁን ከኃይማኖት ተቋማት ላይ እንዲያንሳ፣
2ኛ.  መንግስት ለሁሉም ኃይማኖቶች እኩል ጥበቃ እንዲያድርግ፣
3ኛ. መንግስት የተለመደውን መንግስታዊ አሸባሪነት አቁሞ የሕዝቡን በሰላም የመኖር ዋስትና እንዲያረጋግጥ፣
4ኛ. መንግስት የመንግስትን የፀጥታ ተቋም ተጠቅመው የንፁሀን የኦርቶዶክስ ዘማሪያንና አገልጋዮች ላይ ግድያ የፈፀሙ ወንጀለኞችን በአስቸኳይ አጣርቶ ለሕዝብ ግልፅ የሆነና አስተማሪ እርምጃ ወስዶ እንዲያሳይ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች እና የእምነቱ ተከታዮች አፅናኝ የሆነ ካሳ እንዲክስ ስንል እናሳስባለን፡፡
5ኛ.   መንግስት በኃይማኖቶች ምክንያት የሚነሱ የአምልኮ ማከናወኛ የይገባኛል ሥፍራ ጥያቄዎችን በአስቸኳይ ምላሽ ሰጥቶ በእምነቶች መካከል የሚያንዣብበውን የግጭት ምልክቶች ከወዲሁ እልባት እንዲሰጥ፣
6ኛ.   ለመላው ሕዝባችን በእምነትና በባንድራ ሰበብ በአብሮነትና በአንድነት ላይ ያለውን እሳት ባዳባርከው ትዕግስትህና በሀገር ወዳድ እሴትህ ታግዘህ ሀገርህን ከከፋ መተራመስ ትታደግ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርብልሀለን፡፡
7ኛ.   የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተፈጠረ ያለው ችግር ከዚህ ቀደሙ የከፋ እየሆነ የመሄድ አቅጣጫ ላይ ያለ መሆኑን ተረድተን ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ተጠቅመን የሕዝባችንን አንድነት የመጠበቅና እኛም ለሀገር መቀጠል ሲባል ተባብረን የምንሰራበት ወቅት መሆኑን እንገነዘብ ስንል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!”
ጥር 14 ቀን 2014 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic