>

የኬኛ ፖለቲካ አልተቻለም፤ ዙሩ ከሯል!! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

የኬኛ ፖለቲካ አልተቻለም፤ ዙሩ ከሯል!!

 

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ (ma74085@gmail.com)


ከችግሮቻችን መብዛት የተነሣ ከየት እንደምጀምርም ግራ ገባኝ፡፡ በርካታ ዜጎች ሀገር ሰላም መስላቸው በሚሆነው ሁሉ ሳይሞቃቸው ሳይበርዳቸው የዕለት ከለት ኑሯቸውን ፀጥ ረጭ ብለው ሲገፉ ይታያሉ፡፡ ዕድለኞች ናቸው፡፡ አንድ ሰው መሞቱን እያወቀ ሳይጨነቅ በእርጋታ ሞቱን መቀበል መቻሉ ከመታደልም በላይ ልዩ ፀጋ ነው፡፡ እኔ ግን ይህ ዓይነቱ ዕድለኝነት በፈጣሪ የተነፈገኝ ይመስለኛል አልችልም፡፡ በማየውና በምሰማው፣ በማነበውና በየዕለቱ በሚገጥመኝ አሳዛኝ ሀገራዊና ማኅበራዊ ክስተት ሁሉ መፈጠሬንና ኢትዮያጵዊነቴን ጭምር እስክጠላ ድረስ ክፉኛ ይጨንቀኛል፡፡ ለዚህም ነው ቢያንስ በብዕር ፍዳየን የማየው፡፡ እጅግ ብዙ ሰዎች  ሙሽራው ሳይመጣ መጣ እያሉ በተደጋጋሚ እንዳታለሏትና እርሷም በንዴት “ካልታዘልኩ አላምንም” እንዳለችው ሙሽራ ሆነዋል፡፡ የሙሽራዋስ ቀላል ነው – ግፋ ቢል ሌላ ባል እስክትታጭ መጠበቅ ነው፡፡ የኛው ግን ከባድ ነው፡፡ እያስገመገመ ያለው የመከራ ዶፍ እንዲህ በቀላሉ የምንወጣው አይደለም፡፡ ለማይቀረው አርማጌዴዖን ሁሉም ይዘጋጅ፡፡ ዘመኑ ከፍቷል፡፡ መተዛዘን ጠፍቷል፡፡ ሐጎስና ደቻሣ አምርረዋል፡፡ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ!” ብለው ለትግራይ ትግርኝና ለኦሮሙማ ስኬት ከፍተኛ ዝግጅትና የተናበበ ርብርብ በያቅጣጫው እያደረጉ ነው፡፡ ለዚህም የጦስ ዶሮው አማራ ነው፡፡ አማራው ለመሞትም ራሱን ከሞት ለማዳንም ከምንጊዜውም በበለጠ ተዘጋጅቶ ይጠብቅ፡፡ ከፊት ለፊታችን የሚታይ ብርሃን የለም፡፡ ከጨለማው በኋላ እንጂ አሁን ምንም ደስ የሚል ነገር አይታይም፡፡ “መከራ ሲመጣ አይነግርም ዐዋጅ፤ ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጂ” የሚባለው ሰም ለበስ ቅኔ በተግባር እየታዬ ነው፡፡

ለማንኛውም እጅግ አሳሳቢ ከሆነው ነገር ልጀምር፡፡ ከአንድ የዩቲዩብ ቻናል እንደተገኘው መረጃ ከሆነ የኦሮሙማው መንግሥት ልክ እንደሃጫሉ ሁሉ በቅርብ ከእሥር ቤት ወጣ የተባለን አንድ ታዋቂ ግለሰብ በማስገደል አማራ ገደለው ለማስባልና ኦሮሞው በስሜት ተገፋቶ እንደስካሁኑ ሁሉ አሁንና ወደፊትም የትም ቦታ የሚገኝን አማራ እንዲፈጅ ታላቅ ዕቅድ እንደወጣና ገዳዮቹም ከ”ውጭ ሀገር” እንደመጡ ተጠቁሟል፡፡ ውጭ ሀገር ሲባል ሩቅ እንዳይመስላችሁ – የኛዋ ከነበረችና ሳትወድ በግዷ ጉርብትናን ከመረጠች ሀገር ነው የመጡት፡፡ ይህች ዓመት መቼስ የጉድ ናት፡፡ 

ስለሆነም ውድ ኦሮሞዎችና አማሮችዬ የተደገሰላችሁን አውቃችሁ ከወዲሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ታደርጉ ዘንድ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ ሥልጣን ወዳድ የሤራ ፖለቲካ ሰዎች የክፉ ክፉ ናቸውና ለዕብሪታቸውም ገደብ የለውምና እነሽመልስና አቢይ ይህችን ዕቅድ አይነድፉም ማለት አይቻልም፡፡ ያፈቀረና ያበደ አንድ ነው እንዲሉ ሥልጣን ያፈቀረና በዘረኝነት አባዜ አእምሮው የተለከፈም ሰው እንደዚያው በመሆኑ ለተለከፈበት ነገር ስኬት ሲል ከፀሐይ በታች የማይሠራው ወንጀልና ኃጢኣት፣ ክፋትና ነውርም የለም፡፡ ስለሆነም ከዚህን መሰሉ ሩዋንዳዊ ድርጊት ትቆጠቡ ዘንድ ለጭፍጨፋ ያሰፈሰፋችሁ ወገኖቼ አደብ እንድትገዙ በዚህ አጋጣሚ መልእከቴ ይድረሳችሁ፤ ዜጎችን በመፍጀትና በማፋጀት የምትጠቀሙት ነገር የለም፡፡ ኋላ ይጸጽታችኋል፡፡ አማራና ኦሮሞዎችም – ማንም ይሙት ማን፣ የትም አካባቢ ይገደል … ይህ ተግባር ለሤራ መሆኑን ተገንዝባችሁ የጠላቶቻችሁን ሸርና ተንኮል አምክኑ፡፡ በጠላት ሤራና ወጥመድ መጠለፍ የሚያመጣው ጣጣ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ዛሬ የምትገድለው ሰው ልጅ ነገ ያንተን ልጅ ላለመግደሉ ደግሞ ምንም ዋስትና የለህምና ወገኔ ሆይ ለራስህ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድህም አስብ፡፡ ከሊቢያና ከሩዋንዳ፣ ከሦርያና ከኢራቅ፣ ከሶማሊያና ከየመን፣ ከአፍጋኒስታንና ከዩጎዝላቪያ … የማይማር ትውልድ ራሱ እንዳለቀሰና ሌሎችንም እንዳስለቀሰ ይኖራል፡፡ 

የአክራሪ ኦሮሞዎች ብልጠት የሚጎድለው ራስ ወዳድነትና ችኩልነት ከወያኔም ባሰና ወያኔ እንኳን በ27 ዓመታት ዘግናኝ የዘረኝነት አገዛዙ ያልሞከረውን ኦነግ/ኦህዲድ ሥልጣን በያዘ በአራተኛ ዓመቱ ያቀላጥፈው ገባ፡፡ በወያኔ ዘመን የኢትዮጵያን የቀድሞ ባንዲራ በአልባሳትና በጥቃቅን ነገሮች ላይ እያስጠለፉ መልበስ ያን ያህል ከባድ ችግር የሚያስከትል አልነበረም፡፡ አሁን የኦህዲድ መንግሥት በማንአለብኝነት እየሠራው ያለውን ግፍና በደል ስናይ ግን የወያኔዎችን በዕጥፍ ድርብ የሚያስከነዳ ድፍረት ነው፡፡ መቼም ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ ንጹሑ የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት ያለባቸውን ልዩ ልዩ ነገሮች የሚሸጡ ሱቆች መዘረፋቸውንና ለእሳት እራትነት መዳረጋቸውን በዚያን ሰሞን ሰምተናል፤ ለእውነት በቆሙ የሚዲያ አውታሮችም አይተናል፡፡ ይህ የሚያሳየን ገዢዎቻችን ፍጹም ፀረ ኢትዮጵያ መሆናቸውንና ከዚህ የበለጠ ዕድልና የአገዛዝ ዘመን ቢያገኙ አንድም ኢትዮጵያዊ በሕይወት እንደማያተርፉ ነው፡፡ በአሌልቱና ቱሉ ቦሎne በመሳሰሉ የአዲስ አበባ አቅራቢያዎችማ የታዬው ለዬት የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህ ባንዲራ ጥላቻ ለይቶላቸው ማበዳቸውን የሰሞኑ የጥምቀት በዓል በግልጽ አሳይቶናል፡፡ እንዲህ ያለ ዕብደት ደግሞ በየትም ሀገር የለም፡፡ እንኳንስ በነገድና በሃይማኖት ሳይለያዩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ደማቸውን ያፈሰሱላትና አጥንታቸውን የከሰከሱላት የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራና አንድ ዜጋ ሲፈልግ የሰይጣንን ዓርማ ሲያሻው ደግሞ የጭራቅን ምልክት በአናቱ ወይ በክርኑ ጠምጥሞ ቢሄድ መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን “ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” ሆነና ነገሩ እነዚህ ገልቱዎች ማጣፊያ ለሚያሣጥራቸው ቅብጠት ራሳቸውን አጋለጡ፡፡ 

ባንዲራን መቀማቱና ቀለማቱ ያሉባቸውን አልባሳትና ጌጣ ጌጦች እየቀሙ ማቃጠላቸው ሳያንሳቸው ታቦት ያጀቡ ወጣቶችን በጥይት በመረፍረፍ ሙትና ቁስለኛ ማድረጋቸውን የወይብላ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በቋሚ ምሥክርነት አስመዝግባለች፡፡ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ከነቅርሳቸው እንዳወደመ የሚነገርለት ግራኝ አህመድ እንኳን ይህን ያህል ድፍረት ያሳዬ አይመስለኝም፡፡ ሃይማኖት ክብር ነው፡፡ አንተ አመንከው አላመንከው ሌላ ጉዳይ ሆኖ አንድን ሃይማኖት ይህን ያህል መዳፈር ጥጋብና ዕብሪት ነው፡፡ ወያኔዎችና ኦህዲዶች በዚህ ጠባያቸው አንድ ናቸው – ከተወራረሱት የዘረኝነት ደዌ በተጓዳኝ ማለቴ ነው፡፡ ለነገሩ የማይመሳሰሉበትን ነጥብ ማፈላለግ ይቀላል – ሊያውም ካለ፡፡ በተረፈ ኢትዮጵያን ሊያጠፉ ከጥልቁ የጨለማው ንጉሥ ከሊቀ ሣጥናኤል የተላኩት እነዚህ ጉዶች  እንዳያያዛቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከምድረ ገጽ ሳያጠፉ የሚመለሱ አይመስሉም፡፡ ለመጥፋትም ሆነ ላለመጥፋት ምርጫው የኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ተባብሮ እነሱን መመከት ወይም በተያዘው የእንቅልፍ ሰመመንና የጎሣና የነገድ ልዩነት ቀጥሎ እስከወዲያኛው መጥፋትና ኢትዮጵያን ወደታሪክ ማኅደር ማስገባት፡፡ እነሱ እንደሆኑ በኢትዮጵያ ውድመት ወጧ እንዳማረላት ሴት እየቦረቁ ሃሤት ላይ ናቸው፡፡ አራት ኪሎ ቁጭ ብሎ አማራን እያስጨፈጨፈ ያለው የአጋንንት ጭፍራ “ሰንዳፋና ሰበታ ላይ የሚደረገውን አላውቅም፤ የሥራየ አካልም ስላልሆነ በግድ ማወቅም የለብኝም” ሲልህ አምነህ ከተቀበልክ ታማሚው እርሱ ብቻ ሳይሆን አንተም ነህ፡፡ ከወለጋ ጫካ እስከትግራይ መናገሻ ከተማ በግልጽና በሥውር ባመቻቸው ፀረ ኢትዮጵያ ጨፍጫፊ ኃይል በየቀኑ እየረመረመህ ሳለ “ይህ ልጅ አጋዥ አጣ እንጂ ከላይ የተላከ አሻጋሪ መሲሕ ነው” ብትል መሣቂያው ጅላንፎ አንተ እንጂ አቢይና ሽመልስ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ከዚህ ሁሉ ትያትርና አፍዝ አደንግዝ ጎን ለጎን የማዝንበት ዋና ነገር ግና ኢትዮጵያ የምትገዛው በአጥፊዎቿ የመሆኑን መራር እውነታ ሳስብ ነው፡፡ በበኩሌ ሀገራችን በተማሩና በሚቆረቆሩላት የራሷ ዜጎች ስትተዳር አይቼ በማግሥቱ ብሞት ደስታውን አልችለውም፡፡      

እንግዲህ “ቂጣም ከሆነ ይጠፋል፤ ሽልም ከሆነ ይገፋል” እንዲሉ ነውና በአቢይ ተስፋቸውን ሰንቀው የኢትዮጵያን ትንሣኤ በጉጉት ይጠብቁና እኛንም ክፉኛ ያወግዙ፣ በወያኔነትም ፈርጀው የጁንታ ተላላኪ ይሉን የነበሩ በአዲሱ አገላለጽ ምድረ ውታፍ ነቃዮች ሁላ አሁን ምን እንደተሰማቸው መረዳት ቢያስቸግርም ከአሁን በኋላ ግና ምን አፍ እንደሚኖራቸው እነሱም የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ “ሀ” ብሎ ሲነሳ “መግደል መሸነፍ ነው” ብሎ በደስታ ያስቦረቀንና ያስቦረቃቸው ወጣቱ ዝንጀሮ ካሊጉላ አረማመዱን ከአባቶቹ ከወያኔዎች ጋር ካስተካከለ ወይም እንዳስተካከለ ከተረዳ በኋላ የሚናገረውን ሁሉ ለመቃረን ደቂቃዎችም ሳይፈጅበትና ይሉኝታና ሀፍረትንም እንደደፈጠጠ አሁን ላይ ደርሷል፡፡ ቀድመን የነቃን ከልጁ ባርነት አመለጥን፡፡ በምንም በምንም ያልተነካካን እስካሁን በአቋማችን እንደፀናን አለን፡፡ የወደፊቱን አንድዬ ይወቀውና አሁን ያለው እውነት ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡ ጽኑዓንን እርሱ ይጠብቀን፡:

በአሁኑ ወቅት በሰውዬው ተለዋዋጭ ተፈጥሮና ባስከተለው ሀገራዊ ውድመትና አለመረጋጋት ቀስ በቀስ እየፈዘዘ የመጣው በርካታው ውታፍ ነቃይ በካፈርኩ አይመልሰኝ ወገቡን እንደተመታ ተሳቢ ፍጡር እዚያው ግቢ እየተጥመለመለ ይገኛል፡፡ የሰውዬው አይነጥላም በቀላሉ የሚገፈፍ አይመስልም፡፡ ምን እንደሚያቀምሳቸው ወይንም ምን እንደሚያስነካቸው እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ እንደምንታዘበው ከሆነ ከርሱ ጋር የተጣበቁበት ሙጫ በቀላሉ የሚለቅ አይመስልም፡፡ ለርሱ ዐይናቸው የሚታወር ብዙ ናቸው – አሁንም ድረስ፡፡ ለማንኛውም የኦህዲድ ግመል ደክሟት መቼና የት ላይ ሸብረክ እንደምትልና እንደምታርፍ ባናውቅም እኛ ውሾች ግን መጮሃችንን እንቀጥላለን፡፡  አዎ፣ እንዲህ ማለቴ የኦህዲድ ጌቶች “ውሾቹም ይጮሃሉ፤ ግመሊቷም ጉዞዋን ትቀጥላለች” እያሉ ያላግጡብን ስለነበርና መጨረሻቸውንም ስለተረዳን ነው፡፡ ታሪክ እንዲህ ነበር፤ በዚሁም ይቀጥላል፡፡ “ቆሞ ያለ የሚመስለው ግን ይጠንቀቅ” – ይላል መጽሐፉ፡፡ 

በመጨረሻም ይህን ሰውዬ የምታገኙት ሰዎች እባካችሁን በየጊዜው “ሥልጣኔን እለቃለሁ” እያለ የሚያስጎመጀንን ነገር እንዲተው ንገሩልን፡፡ የራሱን ሞኝት በየጊዜው ከመግለጽ ይቆጠብ፡፡ አውሮፓና አሜሪካ በአንድ የንግድ ዕቃ ላይ የሚጨመር ዋጋ አንድን መሪ በገዛ ፈቃዱ ከሥልጣን ሊያስወርድ ይችላል፡፡ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ግን ወደውና ፈቅደው ባልተወለዱበት የዘር ሐረግ ምክንያት ሚሊዮኖችን አስገድሎ እንኳን፣ “ተጨማሪ ይጠይቁ” እንደሚለው የፔፕሲ ለስላሳ መጠጥ ማስታወቂያ ሌሎች ሚሊዮኖችን ለማስጨፍጨፍ ይዘጋጃል እንጂ ሥልጣን መልቀቅ የሚታሰብ አይደለም፤ እንደኛ ያለ ዕድለ ቢስ ሕዝብ እኮ የትም የለም፡፡ እንጂማ ለአብይ ሥልጣን መልቀቅ ሌላ ሌላው ዕልቂትና ውድመት ይቅርና በወያኔ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የነበረው የኑሮ ውድነት በአሁኑ ወቅት በአነስተኛ ግምት ከ10 እና 15 ዕጥፍ በልጦ መገኘቱ ብቻውን በሕዝብ ተቃውሞ ወይንም በራሱ ፈቃድ ከአራት ኪሎ ፈንቅሎ ቢቻል ቃሊቲ፣ ያ ባይሆን ወደግል ቤቱ ወስዶ በሸጎጠውና ሕዝብም ከዚህ የእፉኝት ልጅ በተገላገለ ነበር፡፡ ግና ዕዳችን ገና ተከፍሎ አላለቀማ!

በመሠረቱ እርሱ ሥልጣን ለቀቀ አልለቀቀ ያን ያህል የሚጋነን ለውጥ አያመጣም፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት ቂን ቂን ስላለ ብቻ ራሱን ሰማየ ሰማያት ላይ ሰቅሎ ልክ እንደሌሎች አምባገነኖች ሁሉ እሱም “እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያም የለችም” የሚል ምናብ-ወለድ አስተሳሰብ ቢኖረውም እርሱ ማለት ልክ እንደዛፍ ጥላ ነው፡፡ ጧት አለ – ማታ የለም፡፡ ብዙዎቹ መሪዎች ማወቅ የሚሳናቸው ይህን እውነት ነው፡፡ በዚህች ምድር ማንም ቢሆን ምትክ-የለሽ (ኢንዲስፔንሲብል) ሊሆን አይችልም፡፡ ይህን ዓይነት ማዕረግ ማግኘት የሚችል የማይሞት ብቻ ነው፡፡ ሟች ደግሞ ያው ሟች ነው፡፡ ዛሬ ይሙት ነገ የማያውቅ አንድ ዳፍንታም ሰብኣዊ ፍጡር ራሱን ከሀገርና ከሕዝብ አስበልጦ ካዬ በርግጥም የሥነ ልቦና ደዌ የተጠናወተው እንደኢዳሚን ዳዳና ኮሎኔል ጋዳፊ ያለ ወፈፌ ነው፡፡ አቢይም የዚህ በሽታ ተጠቂ ነው፡፡ ያሳዝነኛል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሤን በአካልም ባይሆን በፎቶና በርቀት ከወጣትነታቸው እስከጅጅትናቸው አውቃለሁ፤  መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ከወጣትነቱ እስከአሁን የሽምግልና ዘመኑ አውቃለሁ፤ መለስ ዜናዊን ከጎፈሬነቱ እስክምልጥናውና እስክኅልፈቱ አውቃለሁ፤ … ከነዚህ አምባገነኖች አንዳቸውም እንኳን የተፈጥሮን ህግ ጥሰው ወይም ለተወሰነ ጊዜ አስተጓጉለው በወጣትነት ዕድሜያቸውና በአፍላ የሥልጣን ዘመናቸው ልክ እነሱ የፈለጉትን ያህል ዘመን አልኖሩም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፤ የከንቱ ከንቱ፡፡ መጽሐፈ መክብብ ጨርሶታል፡፡ (በነገራችን ላይ ያ አበባው ታደሰ የሚሉት አሽቃባጭ ምን ነክቶት እንደዚያ ነጭ ውሸት ሊዋሽ እንደቻለ የሚያውቅ ሰው ካለ ሹክ ይበለን፡፡ ቀላል ረገጠን እንዴ! “በመከላከያ የዘር መድሎ የሚባል የለም፤ ሊታሰብም አይችልም” አላለ መሰላችሁ! ወይ የሆድ ነገር፡፡)  

ስሙኝማ …. በዘር ፖለቲካ የጨቀዬው ፖለቲካ ካልጸዳ፣ በሙስናና በዘረኝነት የተበከለው አስተዳደር ካልጸዳ፣ በፍቅረ ንዋይ የበከተው የሃይማኖትና የሞራል ስብዕናችን ካልታደሰ፣ ለ40 እና 50 ዓመታት እንዳይሆን ሆኖ በማይምነት ዱላ የተመታው የትምህርት ሥርዓታችን ወደ ቦታው ተመልሶ ጥሩ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት ካልተቻለ፣ በጎችን ለቀበሮና ለተኩላ የሚያስረክብ ውሉደ አጋንንት የሃይማኖት አባት በእውነተኛ እረኛ ካልተተካ፣ የባዘነው ማኅበረሰብ እንዲረጋጋና ሽቅብ የተወነጨፈው የኑሮ ውድነት እንዲረግብ የሚያደርግ ሁኔታ ካልተፈጠረ አንድ ጥዶ ዘለል ብኩን ጠ/ሚኒስትር ከሥልጣን ወረደ አልወረደ ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ እንደማለት ነውና ችግራችን በአንድ ሰው ከሥልጣን መውረድ አለመውረድ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም – መውረዱ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑ ባይካድም፡፡ እርግጥ ነው – “የዓሣ ግማት ከአናት” የሚለውን አባባል መዘንጋት የለብንም፡፡ ከላይ የተበላሸ ከታችም ያው ነውና፡፡  

ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ደግሞ ጅማሮው ከሁሉም አቅጣጫ ቢሆን ለውጡ ይበልጥ ስኬታማ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ለውጥ መጀመር ያለበት ከኔና ካንተም ነውና እኔና አንተ ቀድመን ሰው ለመሆን እንሞክር ይልቁናስ፡፡ በነገር እንግባባ፤ በሃሳብ ፍጭት እንመን፡፡ ለመግባባት ደግሞ እንደማመጥ፡፡ በእርጋታ “እህ” ብለን ከውስጣችን እንናበብ፡፡ ለመናገር የመቸኮላችንን ያህል ለማዳመጥና የሰውን ስሜት ለመረዳትም የፈጠንን እንሁን፡፡ በስፖርታዊ አገላለጽ ወደ “ኳስ በመሬት” ሁኔታ እንግባ፡፡ ሰውነት ይቅደም፡፡ ቋንቋና ዘር፣ ሃይማኖትና ሀብት፣ ትምህርትና ጎጥ አይለያዩን፡፡ ትግስት ይኑረን፡፡ ወደኋላ እየሄድንም ነገር አንጎርጉር፡፡ ባለው ላይ እንመሥረት፡፡ ያጣነው መደማመጥንና መግባባትን እንጂ ከሁሉም ሀገሮች የበለጥን ሀብታሞች ነን፡፡ የአራቱም ወቅቶች ባለቤቶች ነን፡፡ ሰማይና ምድር ቢታረቁልን አንድም የሚጎድለን ነገር የለም፡፡ መሬት ውስጥ ቀብረን በላዩ ላይ እየተገዳደልንበት እንጂ ሁሉም ዓይነት የተፈጥሮና ሰው-ሠራሽ ሀብት አለን፡፡ “እባብ ልቡን አይቶ እገሩን ነሳው” እንደሚባለው ሆኖብን ግን የሁሉም ጌቶች ሆነን ሳለ ምንም ሆንና ሁሉንም ያጣን ነጫጭባዎች ልንሆን ተገደድን፡፡ እንዲህ እንደሆን ባንቀርም የወቅቱ ሁኔታችን ግና በእጅጉ ያናድዳል፡፡ ሰው መሆን እያማረን ዓለም ከማለፏ በፊት በቶሎ እንንቃና ሌሎች ሕዝቦች ወደደረሱበት የሥልጣኔና ራስን የመቻል ማማ እንውጣ፡፡ መፍትሔው ይሄው ብቻ ነው፡፡

Filed in: Amharic