>

ኢትዮጵያ በቴድሮስ አድሐኖም ጥፋቶች ላይ ማብራሪያ እንዳሰጥ መታገዷን አወገዘች

ኢትዮጵያ በቴድሮስ አድሐኖም ጥፋቶች ላይ ማብራሪያ እንዳሰጥ መታገዷን አወገዘች

 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ስብሰባ ላይ ንግግር እንዳታደርግ መታገዷን አወገዘች፡፡
የሽብር ቡድኑን ትሕነግ አመራርና የውጭ ክንፍ አስተባባሪ ቴድሮስ አድሐኖም የድርጅቱ ዳይሬክተር ጄኔራል ሆኖ ለሁለተኛ ዙር እንዲሾም ዕጩ አድርጎ ለማቅረብ ስብሰባ በተቀመጠው ቡርዱ ላይ ኢትዮጵያ በተወካይዋ በኩል ሐሳቧን እንዳታቀርብ መከልከሏ ይታወቃል፡፡
ትናንት በነበረው የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ 150ኛ ስብሰባ ኢትዮጵያ ንግግር እንዳታደርግ ታግዳለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችን ጨምሮ በስዊዘርላንድና በአገሪቱ ለሚገኙ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ዘነበ ከበደ በቴድሮስ ጉዳይ የአገራቸውን አቋም እንዳያቀርቡ ተደርገው የኢትዮጵያ ድምፅ በመንግሥታቱ ሴራ እንዲታፈን መሆኑ የውጭ መገናኛ ብዙኃን የዜና ርዕስ ሆኖ ውሏል፡፡
ይህንኑ በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት ግልፅ ደብዳቤን ያወጣ ሲሆን የመንግሥታቱ አባል ለሆነ አገር ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ማሳየት ተቀባይነት እንደሌለው ገልጾ ድርጊቱ አሳፋሪ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ቴድሮስን የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ለማድረግ በዕጩነት አቅርባና አገራት ድጋፍ እንዲሰጡ አስተባብራ ማስመረጧን ያስታወሰው ደብዳቤው ግለሰቡ ግን የሽብር ቡድኑ ትሕነግ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሲከፍት ትክክለኛ ማንነቱን ገልጧል ብሏል፡፡
ግለሰቡ ከመንግሥታቱም ሆነ ሌሎች የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች በኩል የሚጠበቀውን የገለልተኝነት መርህ በግልፅ በመጣስ የፖለቲካ ውግንናውን እያሳየ ነው፡፡ የሚመራውን ድርጅትም ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ ለማድረግ እየተጠቀመበት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ግለሰቡን እንዲመረምርና ተጠያቂ እንዲያደርግ መጠየቋን አስታውሶ የኢትዮጵያ ጥያቄ ከድርጅቱና ሰራተኞቹ ጋር ሳይሆን በቀጥታ ከግለሰቡ ጋር ብቻ የሚገናኝ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ አስምሮበታል
Filed in: Amharic