>

የህዉሃት ዳግም ጦርነት መክፈት እና የፌደራል መንግስቱ ጦርነት ጨርሻለሁ እንቆቅልሽ ምን ሊሆን ይችላል? ( ሸንቁጥ አየለ)

የህዉሃት ዳግም ጦርነት መክፈት እና የፌደራል መንግስቱ ጦርነት ጨርሻለሁ እንቆቅልሽ ምን ሊሆን ይችላል?
ሸንቁጥ አየለ

 ሰሞኑን ጠሚው ከዲያስፖራዎች ጋር ሲወያይ አንድ ጥያቄ ቀርቦለት የመለሰዉ መልስ ቀልብ ይስባል::”አማራን ከድተሃል ይባላል” በዉይይቱ ዉስጥ ለጠሚዉ የቀረበለት ትችት ነበር::
“አማራን አልከዳንም:: አማራ በወያኔ በሀይል የተያዙበትን ቦታዎች ለጊዜዉ ይዞ እያስተዳደረ ነዉ::ሆኖም በሀይል ተወስዶ የነበረ በሀይል መመልስ ዘላቂ ዉጤት አያመጣም::ስለዚህ ሁኔታዉ በህግ ፍጻሜ እንዲያገኝ ይደረጋል::” ሲል ይመልሳል::
እናም ዋናዉ ጥያቄ እዚህ ጋ “በህግ” ፍጻሜ ያገኛል ማለት ምን ማለት ነዉ?ህገ መንግስቱን በመቀዬር እንዳይባል የብልጽግና ቁልፍ ሀይል የሆነዉ ኦህዴድ ህገ መንግስቱ የሚለወጠዉ በመቃብሬ ላይ ነዉ ብሏል::ህገ መንግስቱ ተቀይሮ የአከካለል መሰረቱ ካልተለወጠ ደግሞ ህገ መንግስቱን በተዋረዳዊ ህጎች በመሻር የይገባኛል ጥያቄ መሰረቱ በህግ ጸና የሚያስብል ርምጃ አይሆንም::
እና መፍትሄዉ ምን ሊሆን ነዉ?ጠሚዉስ ጉዳዩ በህግ ይፈታል ሲል ምን ማለቱ ነዉ?ምንስ መሰረት አድርጎ ነዉ? በተለይም በአሜሪካኖቹ ተወጥሮ የተያዘዉ የአቢይ መንግስት ወያኔ ተያዘብኝ የሚለዉን የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ በምን መልክ ሊፈታዉ ነዉ?ህግ ሲልስ ምን ማለቱ ነዉ?
—–
የአቢይ መንግስት የአሜሪካኖቹን ጫና ወደ ጎን መግፋት ሳይሆን ለአሜሪካኖቹ ጫና ሸብረክ ማለትን እንደ መረጠ ከዲያስፖራዎቹ ጋር ባደረገዉ ዉይይት ግልጽ አድርጓል::እና ለአሜሪካ ሸብረክ ካለ ደግሞ የህዉሃትን ጥያቄ የሚደግፉት አሜሪካኖች የሚያነሱትን በሀይል ከያዝካቸዉ ቦታዎች ለቀህ ዉጣ ምላሽ መስጠት ያስፈልገዋል::ግን እንዴት ይሄን ማድረግ ይችላል?
—–
ቀጥታ የአማራዉን ሀይል ከወልቃይት እንዲሁም ራያ ለቀህ ዉጣ ማለት አይችልም::ይሄን ያለ ቀን ከፍተኛ ብጥብጥ እንደሚነሳበት የአቢይ መንግስት ያዉቃል::ስለሆነም አማራጩ ህዉሃት እየተዋጋች ወደ እነዚህ አካባቢዎች ተስባ እንድትገባ ማድረግ ነዉ::ህዉሃት ወደ እነዚህ አካባቢዎች ከገባች ብኋላ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጉዳዩን ህግ ይፍታዉ የሚል ድርድር እንዲደረግበት ወደሚል ሂደት ዉስጥ ይገባል ማለት ነዉ::
—————
ይሄን ለማሳካት አሁን በአፋርም በኩል ሆነ በአማራ ክልል በኩል ፌደራል መንግስቱ ሳይሆን ህዉሃትን እየተዋጋት ያለዉ የክልሎቹ ሀይል ብቻ ነዉ::ህዉሃት በዚህ ፍጥነት አንሰራርቶ ጦር በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል ላይ ለማወጅ የተነሳበት ዋናዉ ምክንያት የምዕራባዉያኑን ደጀንነት እና የፌደራል መንግስቱም በስልት ዉጊያው ዉስጥ ሳይገባ የክልል ሀይሎች ብቻቸዉን ከህዉሃት ገጥመዉ እንዲዋጉ ብሎም በሂደትም ህዉሃት ወደ እነዚህ አካባቢዎች እንዲሳብ ለማድረግ ሊሆን ይችላል::
————–
መንግስት ለህዝብ ግልጽ መረጃዎችን ስለማያደርስ ኢትዮጵያዉያን ያላቸዉ አማራጭ በሀገራቸዉ የፖለቲካ ጉዳይ የተለያዩ መላ ምቶችን ለማድረግ ጨለማ ስፍራ ዉስጥ የተጣሉ ህዝቦች ናቸዉና ማንኛዉም መላ ምት የቢሆን አለምም ወይም የእዉነት የተጨባጭ መረጃ ቅኝትም ተብሎ የሚደበደምበት ሁኔታ የለም::
የመንግስት ግልጽነት ለአንድ ማህበረሰብ ግልጽ አስተሳሰብ ወሳኝ ነዉ የሚባለዉም ለዚህ ነዉ::ስለዚህ መንግስት ምን እየተከናወነ እንደሆነ ግልጽ መረጃ ለህዝብ የማድረስ ግዴታዉን ቢወጣ ይሻለዉ ነበር::ሆኖም ግዴታዉን ግልጽነት በተላበሰ መልክ ስለማይወጣ ከዬአቅጣጫዉ በርካታ ጥያቄዎች አሉ::
ለዚህ ማሳያም አሎ ያዮ Allo Yayo Abu Hisham   የሚባል የአፋር ልሂቅ ይሄኑን ጥያቄ በማንሳት የአፋር ህዝብ ብቻዉን እንዲዋጋ ፌደራል መንግስቱ ትቶታል::የአፋር ህዝብ ከህዉሃት ጋር እየተፋለመ ሳለ የፌደራል መንግስቱ ግን ጦርነት ጨርሻለሁ ወደ ልማታችን ተመልሰናል ሲል ይቀልዳል ሲል አምርሮ ይተቻል::
የአሎ ያዮ ትችት ግን የአሎ ብቻ አይደለም::የመላዉ ኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ነዉ::
——–
ፌደራል መንግስቱ ምን እያደረገ ነዉ? እስካሁን የወደሙ የአፋር እና የአማራ አካባቢዎችን መልሶ እየገነባ ነዉ? አሁንስ ህዉሃት በአማራ እና በአፋር ክልል ላይ ጦርነት አዉጃበት ሳለ ፌደራል መንግስቱ ጦርነት ጨርሻለሁ ማለቱ ተጨማሪ አካባቢዎች በህዉሃት እንዲወድሙ ፈልጎ ነዉ? ነዉ ወይስ ቦታዎችን በመልቀቅ ከህዉሃት ጋር ለማካሂያድ የታሰበ ድርድር ኖሮ ነዉ?
Filed in: Amharic