ቴዎድሮስ ታደሰ በላይ
በፋኖ ጉዳይ (ከስያሜ ጀምሮ) ሊሰሩ የሚገባቸው በርካታ የቤት ስራዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ከአንድ ቤት ሁለት አንበሳ አያድርም በሚል ፈሊጥ ትላንት አማራን ያስከበረ ኃይል ዛሬ በኢ-መደበኛ ኃይልነት ፈርጆ ለአማራ ህዝብ ሰላምና ፀጥታ በስጋትነት መመልከት ግን ፍፁም ተገቢ ካለመሆን ባሻገር የቁርጥ ቀን ባለውለታን አመድ አፋሽ ማድረግ ነው።
ሌላው ቢቀር በአሁኑ ሰዓት ከአማራ ክልል መንግስት በተሻለ ሁኔታ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋና የወሎ አራሹ፣ ቀዳሹ፣ ተኳሹ ፋኖ ህዝባዊ አመኔታ (public trust) በደምና አጥንቱ ገንብቷል። ይህ ደምና አጥንት የተከፈለበት አመኔታ እንዲሁ እንደዘበት በብጣሽ ወረቀት በፍረጃ የማይናድ ነው። የአማራ ክልል መንግስትም ይህኑ የሚረዳ ይመስለኛል። የአቋም መግለጫውም ይህኑ በማገናዘብ የሚያትት ነው።
ይልቁንስ በፋኖ ጉዳይ ግን ሊታሰብና ሊሰራበት የሚገባውና ጤነኛው አካሄድ ይህ ነው፦
ፋኖን በምን መልኩ ተገቢውን ወታደራዊ ስልጠና መስጠት ይቻላል? እንዴት አድርጎ በወታደራዊ ብቃትና ስነምግባር ማነፅ ይቻላል?
በክልሉ በተለያየ ደረጃ ባልማከለ ሁኔታ የተደራጀውን ኃይል እንዴት ወደ አንድ መዋቅር አምጥቶ በማደራጀት በራሱ የእዝ ሰንሰለት እንዲመራ ማድረግ ይቻላል?
የወታደራዊ ተቋም ምልመላ መስፈርት የሚያሟሉና በመንግስት የፀጥታ ኃይል ውስጥ ገብቶ የመስራት ፍላጎት ያላቸውን እንዴት አድርጎ ማስተናገድ ይቻላል?
መቸስ እንኳን አረር የታጠቀ ይቅርና መስቀል ያነገተ እንኳን ፍፁም ስለማይሆን በፋኖ ስም በትጥቅ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ለህግ የበላይነት ተገዥ ያልሆኑ አልያ ያለመሆን አዝማሚያ ያላቸውን በወል ስሙ ከሚነግዱበት ኃይል እንዴት አድርጎ መነጠልና ስርዓት ማስያዝ ይቻላል?
በግለሰብ ደረጃ ሊያዙ የማይችሉ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እንዴት አድርጎ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ማስተዳደር ይቻላል? የሚለው እና
በህዝብና አገር ላይ አሁንም ድረስ ያልተቀረፈን የህልውና አደገ በገጠመ ግዜ በጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት ተነሳስተው፣ ግንባር ወርደው፣ ያለምንም ክፍያና ጥቅማ ጥቅም፣ ህይወታቸውን አሲዘው፣ አገር የታደጉትን የህዝብ ልጆች እንዴት አድርጎ ህይወታቸውን እና ኑሯቸውን መደገፍ የሚያስችል፣ ቋሚና ዘለቄታዊ ማህበራዊ ዋስትና በመስጠት፣ ተረጋግተውና ቤተሰብ መስርተው/ተቀላቅለው መኖር ይቻላሉ የሚለው ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ መስራቱ፣ መምከሩ፣ ማጥናቱ ለሁሉም ይበጃል!
***
ተኳሹ ቀዳሹ አራሹ ፋኖ
Thank you for your service!
⇑ምስሉ እስካሁን ድረስ በቀበሮ ጉድጓድ ምሽግ ይዘው ህልውናችን የሚያስከብሩ የወልቃይት ሚሊሻና ፋኖ ነው!