>

አንቶኒ ብሊነክ፣ ዐብይ አሕመድ፣ ተመስገን ጥሩነህና ፋኖ!  (መስፍን አረጋ)

አንቶኒ ብሊነክ፣ ዐብይ አሕመድ፣ ተመስገን ጥሩነህና ፋኖ!

‹‹ጠመንጃየን የምትወስደው ከሬሳየ ላይ ፈልቅቀህ ነው››

(I will give you my gun when you pry it from my cold, dead body)

 

መስፍን አረጋ

ፋኖ ከወያኔ ጋር አንገት ላንገት ተናንቆ የማረከውን መሣርያ በዐብይ አሕመድ ጃንደረባ በተመስገን ጥሩነህ በኩል ለኦነግ ከሚያስረክብ ቢሞት ይሻለዋል፡፡  ዐብይ አሕመድ ከወያኔ ጋር በመመሳጠርና በመተባበር መከላከያን ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ስላፈራረሰው፣ መከላከያ ተብየው የቀረው በስም ብቻ ነው፡፡  ብርሃኑ ጁላንና መሰሎቹን በማዕረግ ሲያንበሸብሻቸው ምንም ያልሰጋው፣ ትእዛዛቸውን የሚቀበል ይህ ነው የሚባል ጦር ስለሌላቸው ነው፡፡  ስለዚህም ዐብይ አሕመድ ፋኖን በኃይል ትጥቅ አስፈታለሁ ካለ፣ ማዝመት የሚችለው የሚተማመንባቸውን ጦሮቹን የኦሮምያን ፖሊስ፣ ልዩ ኃይልንና ሸኔን ነው፡፡  ለነዚህ ደግሞ የሸዋ ፋኖ ብቻውን በቂ ነው፡፡  

____________________________________

በአቶ ብሊንከን (Anthony Blinken) የሚመራው ያሜሪቃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ‹‹የኢትዮጵያን ግጭት ባስቸኳይ የማቆም አስፈላጊነት›› (The Urgent Need to End the Conflict in Ethiopia) በሚል ርዕስ ጥቅምት 18፣ 2014 ዓ.ም (November 4, 2021) ላይ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡  የመግለጫው ጭብጥ ደግሞ አንድና አንድ ብቻ ሲሆን፣ እሱም ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ዘር ተኮር ሚሊሻወችን ክተት ማለቱን እንዲያቆም›› (We call on the Government of Ethiopia to halt its … mobilization of ethnic militias) የሚለው ነው፡፡

እኔ መስፍን አረጋ ደግሞ የብሊንከን መግለጫ በወጣ ሰሞን፣ ስለ መግለጫው ያለኝን እይታ ‹‹የአንቶኒ ብሊንከን መግለጫ ዋና ጭብጥና የዐበይ አሕመድ ሚና›› በሚል ርዕስ በተጦመረ ጦማር ለመግለጽ ሞክሬ ነበር፡፡  የጦማሩ ፍሬ ነገሮች ደግሞ የሚከተሉት ነበሩ፡፡ 

ወያኔና ኦነግ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዘር ተኮር ሚሊሻወችን (ethnic militia) በደንብና አሰልጥነው፣ እስካፍንጫቸው አስታጥቀው፣ እነዚህን ዘር ተኮር ሚሊሻወቻቸውን ባማራ ሕዝብ ላይ በየጊዜው እያዘመቱ የዘር ጭፍጨፋ እንደሚፈጽሙ አንቶኒ ብሊንከን አሳምሮ ያውቃል፡፡  ስለዚህም የብሊንከን መግለጫ የሚመለከተው አማራንና አማራን ብቻ ነው ማለት ነው፡፡  

አቶ ብሊንከን ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ዘር ተኮር ሚሊሻወችን ክተት ማለቱን እንዲያቆም›› ሲል፣ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ማለት የፈለገው የኢትዮጵያ መንግስት ፋኖን ትጥቅ አስፈትቶ ይበታትን ነው፡፡  ይህ ማለት ደግሞ የአማራ ሕዝብ ክተት ዝመት ማለቱን አቁሞ፣ እጁን አጣጥፎ ይቀመጥና አስቀድመው በከተቱትና በዘመቱት በወያኔና በኦነግ ይጨፍጨፍ ማለት ነው፡፡  ከዚህ ውጭ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም፡፡  

  የብሊንከን ፀራማራ መግለጫ ፍሬ ሐሳብ ሊመነጭ የሚችለው ደግሞ ከሌላ ከማንም ሳይሆን ወያኔና ኦነግ እስካፍንጫቸው እስኪታጠቁና አማራን ለማጥፋት በወለጋና በወሎ አቅጣጫ እስኪዘምቱ ድረስ ድምጹን ካጠፋ በኋላ፣ አማራ ራሱን ለመከላከል መነሳሳት ሲጀምር፣ ባደባባይ ወጥቶ አትክተት፣ አትዝመት ካለው ከኦነጋዊው ከዐብይ አሕመድ ነው፡፡  

በተደጋጋሚ ለማሳሰብ እንደሞከርኩት፣ አቶ ብሊንከን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተን ማናቸውንም መግለጫ የሚያወጣው ከዐብይ አሕመድ ጋር ከተመካከረና ከሞላ ጎደል ሙሉ ስምምነት ላይ ከደረሰ በኋላ ብቻ ነው፡፡  የአቶ ብሊንከን መልዕከተኞች አዲስ አበባ ሲመጡ፣ ዐብይ አሕመድ በአካል አግኝቶ የማያነጋግራቸው፣ በስልክ የጨረሰውን ሻጥር ለማስተባበልና የአማራን ሕዝብ ለማታለል ሲል ብቻ ነው፡፡   

እነሆ ዐብይ አሕመድና አንቶኒ ብሊንከን አስቀድመው የተስማሙበት ፋኖን ትጥቅ አስፈትቶ በመበታተን የአማራን ሕዝብ ለኦነግና ለወያኔ ጅቦች አሳልፎ የመስጠቱ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር የብአዴኑ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለኦነግና ለወያኔ በትናንትናው ዕለት (ዐርብ፣ ጥር 28፣ 2014 ኢ.ዮ) አብስሯቸዋል፡፡  ለመሆኑ፣ የአማራን ሕዝብ ለኦነግና ለወያኔ ጅቦች አሳልፎ የመስጠቱን ሥራ በበላይነት እንዲመራው በዐብይ አሕመድ የተመረጠው አቶ ተመስገን ጥሩነህ ማነው? 

ዐብይ አሕመድ አማራን ቆረጣጥሞ እየበላ ያለ ኦነጋዊ አውሬ ቢሆንም ጥርሶቹ ግን ሙሉ በሙሉ ብአዴኖች ናቸው፡፡  ከጥርሶቹ ውስጥ ደግሞ ክራንቻወቹ (ማለትም አማራን የሚዘነጣጥልባቸው ሁለቱ የፊት ጥርሶቹ) ደመቀ መኮንን እና ተመስገን ጥሩነህ ናቸው፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን የሐሳዊውን ተዋኝ (con artist) የዐብይ አሕመድን ፀራማራ ስብከት አሚን ብሎ ተቀብሎ (convinced) ወይም ደግሞ  ማንነቱ ተምታቶበት (confused) አንድኛውን ተጠቃሎ ሕቡዕ ኦነጋዊ ሁኗል ማለት ይቀላል፡፡  የዐብይ አሕመድ ደቀመዝሙር ከሆነ በኋላ ደግሞ ከመምህሩ ከዐብይ አሕመድ በላይ ጽንፈኛ ኦነጋዊ ሁኗል ማለት ይቻላል፡፡ የአማራ ሐዝብ መሪ ነኝ እያለ፣ ይህ ሁሉ የኦነግና የወያኔ መርገምት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲወርድበት ዝንብ የሞተ ሳይመስለው ድመጹን አጥፍቶ የሚቀመጥበት ሌላ ምንም ምክኒያት የለውም፡፡

አቶ ተመስገን ጡሩነህ ደግሞ ነገረ ሥራው ሁሉ የረዥም ጊዜ ባልደረባውን ዐብይ አሕመድን ለማስደሰት ጠብ እርገፍ ማለት ስለሆነ፣ ከዐብይ አሕመድ ጋር የተለየ ግንኙነት ያለው ያስመስልበታል፡፡  ባጭሩ ለመናገር ይህ ግለሰብ የዐብይ አሕመድ ባልደረባ ብቻ ሳይሆን ጃንደረባም ጭምር ነው፡፡   ለቋንቋየ ይቅርታ ይደረግልኝና ግለሰቡ የዐብይ አሕመድ የጭን ገረድ ነው ማለትም ይቻላል፡፡  ለዚህ ይሆናል ወዳጁ ዐብይ አሕመድ ከባሕርዳሩ ጭፍጨፋ በኋላ ለሱ በማይገባው በዶክተር አምባቸው ወንበር ላይ ያስቀመጠው፡፡  በዲባቶ አምባቸው ወንበር ላይ በተቀመጠ ማግስት ደግሞ ፋኖን እያሳደደ መግደልን ዋና ሥራው አድርጎ ተያያዝከው፡፡  የጀነራል አሳምነውን ልዩ ኃይል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በማፈራረስ፣ የአማራ ብሔርተኝነት ያሰጋኛል ያለውን ዐብይ አሕመድን ለማስደሰት ብዙ ርቀት ተጓዘ፡፡  ሽመልስ አብዲሳ የዝዋይና የሻሸመኔ አማሮችን ቆዳ ስላስገፈፈ ብቻ አድናቆቱን ለመግለጽ ባሕርዳር ድረስ ጠርቶ ካባ ደረበለት፡፡  የአማራን ሕዝብ እነ ሽመልስ አብዲሳና ታየ ደንድኣ የሚዘልፉት ሳይበቃ፣ ራሱ አቶ ተመስገን ደግሞ ‹‹ወንጀለኞችን የሚያወድስ ማሕበረሰብ›› በማለት በብአዴን ምክር ቤት ውስጥ ተሳለቀበትና የአለምነው መኮንንን ስድብ ደገመው፡፡     

ወያኔና ኦነግ እስካፍንጫቸው በሚታጠቁበት ጊዜ የአማራ ሕዝብ ራሱን ለመከላከል እንዳይታጠቅ አንቆ መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ የታጠቀውንም እንዲፈታ የቻለውን ሁሉ አደረገ፡፡  ይህን ሁሉ ካደረገ በኋላ ደግሞ የአማራ ሕዝብ ዱላ ብቻ ይዞ ድሽቃ ከታጠቀው ከወያኔ ጋር ሲፋለምና እንደ ቅጠል ሲረግፍ ለማየት የቋመጠ ይመስል፣ ከጦርነቱ አስቀድሞ ወያኔን እንሰብረዋለን፣ እንቀብረዋለን እያለ የፌስቡክ ጉራውን እያከታተለ ነዛ፡፡  በዚያ ደረጃ ሲፎክር የነበረ ሰው ደግሞ ወያኔ የአማራን ድንበር ጥሶ ደብረብርሃን እስኪደርስ ድረስ፣ ከጌታው ከዐብይ አሕመድ ጋር እተሰወረበት ተሰውሮ፣ ድምጹን አጥፍቶ፣ አድፍጦ ተቀመጠ፡፡  የአማራ ሕዝብ ወያኔን ወደ መቃበሩ የመሸኘት ዘመቻ ሲጀምር ደግሞ ካደፈጠበት ቡትርፍ ብሎ ወጥቶ ዘመቻውን ባጭሩ ለማስቀረት መልከስከስ ጀመረ፡፡  

ሸኔ ሠላሳ ባንክ ሲዘርፍ፣ ከተሞችን ሲያወድም፣ የአማራ ነፍሰጡሮችን ማሕጸን ሲዘረግፍ፣ አማሮችን ቀን በቀን ባደባባይ ሲረሽን፣ ዘቅዝቆ ሲሰቅል፣ ቆዳቸውን ሲገፍ፣ ሬሳቸውን በሞተር ሳይክል ሲገትት፣ ካስከሬናቸው ላይ የቆረጣቸውን እጅና እግሮች እንደ ዱላ ሲጨፍርባቸው፣  ሕጻናትን ሰብስቦ፣ ጉጆ ውስጥ ዘግቶ፣ እሳት ለኩሶ ሲያንጨረጭራቸው አንድም ቃል ሳይተነፍስ፣ የጦቢያን ሕልውና ያስቀጠሉትን የአማራን ጀግኖች ግን ዘራፊወች ብሎ ባደባባይ ተሳድቦ ትጥቃቸውን ለማስፈታት ፎከረ፡፡   በአማራ ሕዝብ ላይ ሲሳለቅ ደግሞ ፋኖን አደብ እንዳስገዛለት ሕዝቡ ጠይቆኛል አለ፡፡  

የአማራ ሕዝብ የተመስገን ጡረነህና የደመቀ መኮንን ዓይነቶችን፣ የራሳቸውን ነፍስ በዐብይ አሕመድ እጅ ያስቀመጡ ብአዴናዊ ሙትቻወችን ከሰው ቆጥሮ የሚጠይቃቸው ካለ የሚጠይቃቸው ከጫንቃው ላይ እንዲወርዱለት ብቻ ነው፡፡  ብአዴኖችን ከጫንቃው ላይ በማውረድ፣ በብአዴን የታዘለውን ዐብይ አሕመድን አሽቀንጥሮ ከጣለ ደግሞ፣ ወያኔና ኦነግ እዳቸው ገብስ ነው፡፡    

አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፋኖን ትጥቅ አስፈታለሁ ብሎ ቢፎክርም፣ ሙትቻ ስለሆነ ግን ፉከራው ተግባራዊ የሚሆንለት ራሱ ፋኖ በራሱ ፈቃድ ትጥቁን ከፈታለት ብቻ ነው፡፡  ፋኖ ደግሞ ከወያኔ ጋር አንገት ላንገት ተናንቆ የማረከውን መሣርያ በዐብይ አሕመድ ጃንደረባ በተመስገን ጥሩነህ በኩል ለኦነግ ከሚያስረክብ ቢሞት ይሻለዋል፡፡  ስለዚህም ለተመስገን ፉከራ፣ ፋኖ መስጠት ያለበት አንድና አንድ መልስ ብቻ ነው፡፡  ‹‹ጠመንጃየን የምትወስደው ደሙ ከቀዘቀዘው እጀ ላይ ፈልቅቀህ ነው››  (I will give you my gun when you pry it from my cold, dead body) ቢለው፣ የተመስገን ፉከራ ውሃ ይበላዋል፡፡ 

ዐብይ አሕመድ ከወያኔ ጋር በመመሳጠርና በመተባበርና መከላከያን ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ስላፈራረሰው፣ መከላከያ ተብየው የቀረው በስም ብቻ ነው፡፡ ብርሃኑ ጁላንና መሰሎቹን በማዕረግ ሲያንበሸብሻቸው ምንም ያልሰጋው፣ ትእዛዛቸውን የሚቀበል ይህ ነው የሚባል ጦር ስለሌላቸው ነው፡፡  ስለዚህም፣ ዐብይ አሕመድ ፋኖን በኃይል ትጥቅ አስፈታለሁ ካለ፣ ማዝመት የሚችለው የሚተማመንባቸውን ጦሮቹን የኦሮምያን ፖሊስ፣ ልዩ ኃይልንና ሸኔን ነው፡፡  ለነዚህ ደግሞ የሸዋ ፋኖ ብቻውን በቂ ነው፡፡  

Email: Mesfin Arega mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic