>

ከእግዚአብሔር ጋር እስኪጣላ እንጠብቀው!! (የዓለም ሰላም)

ከእግዚአብሔር ጋር እስኪጣላ እንጠብቀው!!

የዓለም ሰላም


ያኔ ነው ቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘውድ ጭነው ንጉሥ ከመሰኘታቸው ቀደም ብሎ በአልጋ ወራሽነት ዘመናቸው ላይ እያሉ ይህንን ሥልጣናቸውን ያልወደዱላቸውና በክፉ የፈለጓቸው አንዳንድ ሰዎች ክስ መስርተውባቸው በጥቅምት ወር 1912 ለንግሥት ዘውዲቱ ክስ አቀርበውባቸው ነበር፡፡ 

የክሱም ይዘት እንዲህ የሚል ነበር፤ አልጋ ወራሹ በራሳቸው ስልጣን ሙሴ ባየር ለተባለ ፈረንሳዊ ወርቅ፣ ብር፣ ብረትና የድንጋይ ከሰል ማዕድናትን ከመሬት እንዲያወጣ ፍቃድና የማይገባ ውል ሰጡት የሚል እና ሌሎች የዚህ ዓይነት ፍቃድ የመስጠት ክሶች ነበሩ። 

ነገሩም አገር እንደመሸጥ ያለ ነገር ነው እየተባለ በብዙ ተጋኖ ለንግስቲቱ ቀረበ። በከሳሾቹ ሐሳብ አልጋ ወራሽ ተከሳሽ እነርሱ ከሳሾች ሆነው በንግሥት ችሎት ላይ የሚቀርቡ መስሏቸው ነበር። በዳኝነትም ጊዜ ንግሥት የእነርሱን ክስ ደግፈው እንደሚፈርዱላቸው ገምተው ነበር ይባላል። ዳሩ ግን ነገሩ ሁሉ ተለዋወጠ። 

ወደ መንፈሳዊነቱና ወደዝምታው የሚያዘነብሉት ንግሥቲቱ የክሱን ጽሑፍ አሳልፈው ለአልጋ ወራሻቸው ሰጧቸው አልጋ ወራሹም ቃሉን ተመልክተው ይህን የሐሰት ወሬ ያወሩ ሰዎች ሁሉ እጃቸው ተይዞ እንዲጠየቁ ይገባል አሉና ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ተይዘው በከሰሷቸው አልጋ ወራሽ፣ ተፈሪ እጅ ላይ ወደቁ። 

የሆነው ሆኖ በዚህ ታሪክ ላይ የሚገርመኝ ከክሱ ኅብረት ውስጥ የነበሩበትና ነገሩን አውጥተው አውርደው ካጤኑት በኋላ (ወይም ተገልፆላቸው) ከጉዳዩ እራሳቸውን ያገለሉት አንድ ሰው ከእነርሱ ሲለዩ የተናገሯቸው የምክር ቃል ነው። 

ቃሉም፦  “ወንድሞቼ ሆይ ይህ ሰዉ (አልጋ ወራሹ) ከእግዚአብሔር ጋር ገና አልተጣላምና አሁን በከንቱ አንድከም። እግዚአብሔር ሳይጣላው በርሱ ላይ ብንነሳ እኛ እራሳችን እንጠፋለን እንጂ እርሱን አንጎዳውም። እስቲ ተመልከቱት ይቆርባል ፣ ይሰግዳል፣ ይጸልያል፣ ቤተክርስቲያን ይስማል፣ ለድሃ የመፀውታል፣ ታዲያ እንዴት አድርገን እንጎዳዋለን እንግዲህ ከእግዚአብሔር ጋር እስኪጣላ ድረስ እንጠብቅ እንጂ አሁን ይቅርብን፤” ብለው ተናግረው ከምክሩ ተለዩ። 

ከእግዚአብሔር ጋር ገና አልተጣላምና አሁን በከንቱ አንድከም፤ እስኪጣላ እንጠብቀው።

እንዲህ አይነት በውስጡ ብዙ ዓይነት መልክቶች የታጨቁበት ገላጭ ምክር  ከወዴት ይኖር ይሆን?!

እንዲፈረድባቸው እና ከመንበረ ሥልጣናቸው እንዲሽቀነጠሩ የተከሰሱት አልጋ ወራሽ መካሪው እንዳሉት ያኔ ገና፣ ሰው በማይሰሙበት፣ ግፍ በማያበዙበት፣ እኔን ብቻ ስሙኝ፣ ፈላጭ ቆራጭ እኔ ብቻ ነኝ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ተራው የኔ (የኛ ) ነው ባላሉበት አፍላ ጊዜያቸው ላይ ነበሩና ገና ከእግዚአብሔር አልተጣሉም፤ ስለዚህ በሥልጣን ላይ ሥልጣን እየጫኑ ንጉሠ ነገሥት ድረስ በመጓዝ አገራችንን ለብዙ ዓመታት ገዙ። 

በመጨረሻ ረጅም የነበረውን እና ከአገር ውስጥ ገልባጭ እስከ ወራሪ የውጭ ጠላት ሳይነጠቁ ያቆዩትን ወንበራቸውን እሳቸውም ሆኑ የሳቸው የሆኑ ሰዎቻቸው ደሃው ላይ የግፍ ቀንበራቸውን ባከበዱበት ሰዓት፣ የሰው ምክር አንሰማም ባሉበት ጊዜ፣ ሌላውን በናቁበት ወቅት፣ እኛ ብቻ ነን ኃያል ባሉበት ዘመናቸው ላይ ያኔ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣሉና ስንት መኳንንት፣ ስንት ትልልቅ የጦር ጀነራሎች፣ ብዙ የተማሩ ትልልቅ ሰዎች በሞሉባት አገር ላይ ማንም በማያውቃቸው እና ትኩረት በተነፈጋቸው ጥቂት መኮንኖችና የበታች ሹሞች ተገፍትረው ወንበራቸውን ለቀቁ፤ በዚህም ሳይበቃ እንደ ሰው ለመሞት እንኳን ክብር ተነፍጓቸው እንደ ትቢያ የትም ስርቻ ተወረወሩ። 

ድሮም ጀምሮ የአፍሪካ  ባለስልጣኖች ጠዋት ወደ ሥልጣን ሲመጡና በእርጥቡ የሥልጣን ዘመናቸው ደሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ የሚሉ ናቸው። አልፈው ተርፈው ምሕረት አድራጊዎች፣ ሕዝቡን ያሳዘነ ያስቀየመ ባለስልጣናቸውን ከስልጣኑ ሻሪዎች የታመመ (ተራዎቹን ሰዎች ሳይቀር) ጠያቂዎች ፣ ሕዝብ ባለበት ሁሉ አለን ባዮች ናቸውና ያኔ ከእግዚአብሔር ጋር አይጣሉም። 

ጉዱ የሚጀምረውና ከአምላክ ጋር ጠብ የሚጀምሩት እርጥቡ ስልጣናቸው መጠጥ ሲል ነው። እግራቸው በደንብ ሲረግጥ፣ “ከእርሶ በላይ ማን ኖሮ” የሚላቸው ሲበዛ፣ በባለፀጋ ሲከበቡ፣ ከክብ ካቡ ውጪ ያለውን ደሃ ማየት ሲረሱ፣ የዲታውን አጥር ሲያሰፉ፣ የምስኪኑን ጎጆ ሲያፈርሱ ወይም ሲፈርስ እየሰሙና እያዩ ዝም ሲሉ፣ ያኔ የገደሉን ጠርዝ ይይዙታል የገቡትን ቃል ይረሱታል፣ ሰፊውን ሕዝብ ይንቁታል እናም ያኔ ከፈጣሪ ጋር ይጣሉና እነሱ ሲመጡ እንዳረጉት መጪውም አንሸራቶ አሊያም ጎትቶ ከወንበራቸው ላይ ይፈጠፍጣቸውና መሬት አይንካን ባሉበት ግዛታቸው ላይ መሬት ላይ እያንደባለለ በናቁት ሕዝብ ፊት ያዋርዳቸዋል፤ መለመላቸውን ወይም እራፊ ጨርቅ አልብሶ እንደ ከብት እየነዳ ወደ መቃብራቸው ይሸኛቸዋል፣ ወይም ቀሪ ዘመናቸውን በስደት እንዲኖሩ ይዳርጋቸዋል። 

ይኸው ነዉ። መሪዎቹም ሆኑ በነ እርሱ ስር ያሉት ባለስልጣኖቻቸው ወንበራቸው እስኪ ፀና እና እስኪደላደሉ ብዙም ግፍ አያበዙም እናም ከፈጣሪያቸው አይጣሉም። አንቱታ ሲጎርፍና “ከእርሳቸው አመራር ጋር ወደፊት” የምትለዋ ዓይነት የማሽቃበጥ ሙገሳ ስትበዛ ግን ሰዎች ናቸውና መታበይ ይወለዳል ያኔ እነሱም ይቀብጣሉ፣ ሕዝቡንም ያቆስላሉ፣ ከፈጣሪም ይጣላሉ ከዚያም ፅዋቸው ትሞላና ወደ ግዞት ወይም ወደ ስደት ወይም ወደ ሞት አሊያም ነገራቸውን ላላየሚያደርግ ከገጠማቸው (ብዙ ጊዜ በእኛ አህጉር አይገጥምም) ወደ ትግል ጫካ ይወርዱና አማፂ (አሸባሪ) ተሰኝተው ከአውራጃቸው ጋር ጦርነት ይገጥማሉ። 

ከፈጣሪ ጋር መጣላት . . .!!

Filed in: Amharic