>

እውነቱን "እውነት" ሀሰቱንም "ሀሰት" በሉ...!!! (ዮሐንስ መኮንን)

እውነቱን “እውነት” ሀሰቱንም “ሀሰት” በሉ…!!!

ዮሐንስ መኮንን


*…. እንኳንስ አባቶች እንመጣለን ባላላቡት ጉባኤ ይቅርና “እንመጣለን” ብለው ቢቀሩ እንኳን የከንቲባ ጽ/ቤት በዚህ ደረጃ የወረደ ዜና መሥራቱ ክብር አይጨምርለትም። ከንቲባዋ አባቶችን በእምነት ባይመስሏቸው እንኳን ሽምግልናቸውን እና ተቋሟን ማክበር ያስመሰግናቸው ይሆን እንጂ አያዋርዳቸውም ነበር።
“መንግሥት የቤተክርስቲያኒቱን መብቶች እና ጥቅሞች እያከበረም ሆነ እያስከበረ አይደለም፤ ክብሯንም እየተጋፋ ነው” በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ ከንቲባ አዳነች አቤቤን በደብዳቤ ለውይይት ጠርቶ ነበር።
በትናንትናው እለት (24-05-14) ማምሻው ላይ ከንቲባዋ ቀሲስ በላይን ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በመላክ ቤተ ክህነት እንደማይመጡ ውይይቱ መካሄድ የሚችለው ሸራተን ሆቴል እንደሆነ ለጠቅላይ ቤተክህነት በመልእክተኛ ያሳውቃሉ። መልእክቱን የሰሙት ሊቀጳጳስ “ይህንን በግሌ የምወስነው አይደለም። ነገ ጠዋት የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ተወያይተን መልሳችንን እናሳውቃለን” በማለት ቀሲስ በላይን የነግሩታል። (ቀሲሱ ተመልሰው ለከንቲባዋ የነገሯትን እግዜር እና እነርሱ ብቻ ናቸው የሚያውቁት)
ዛሬ ጠዋት (25-05-14) አባቶች ተሰብስበው  “በቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ሲኖዶስ ሆቴል አይሄድም። ትውፊቱም አይፈቅድልንም” የሚል አቋማቸውን ዛሬ ጠዋት ለከንቲባ ጽ/ቤት አሳውቀዋል። እንዲያውም ሲኖዶሱ አባላት “ቀሲስ በላይንስ ከንቲባዋ ጋር በዚህ ጉዳይ እንዲያወያዩ ሲኖዶስ መች ወከላቸው?” የሚል ቅሬታም ነበራቸው። ከንቲባ አዳነችም በአቋማቸው በመጽናት ያልተቀጠሩበት ሆቴል በመሄድ “እኛ መጥተን እነርሱ ቀሩ” ከሚል አሳሳች ዜና ጋር ፎቶ ተነስተው ለጥፈዋል።
እንኳንስ አባቶች እንመጣለን ባላላቡት ጉባኤ ይቅርና “እንመጣለን” ብለው ቢቀሩ እንኳን የከንቲባ ጽ/ቤት በዚህ ደረጃ የወረደ ዜና መሥራቱ ክብር አይጨምርለትም። ከንቲባዋ አባቶችን በእምነት ባይመስሏቸው እንኳን ሽምግልናቸውን እና ተቋሟን ማክበር ያስመሰግናቸው ይሆን እንጂ አያዋርዳቸውም ነበር።
በመሠረቱ እንደተቋም ለተጻፈ ደብዳቤ ተቋማዊ መልስ ይሰጣል እንጂ በሲኖዶስ ደረጃ ለተያዘን ጉዳይ ግለሰብን ጉዳይ አመላላሽ አድርጎ አሾልኮ ማስገባት ተገቢ አልነበረም።
በእኔ አስተያየት መንግሥት አገልጋይ እንደመሆኑ በየተቋማቱ በአካል እየተገኘ ቢወያይ እና ችግር ቢፈታ ያስመሰግነዋል እንጂ ክብሩ አይቀነስበትም። ምነው ለምርጫ ቅስቀሳ እና ለምረጡኝ ዘመቻ ሲሆን በየመንደሩ እና በየግለሰቡ ቤት እየዞርን በር እናንኳኳ አልነበረም እንዴ? “ስንመረጥ” እና “ኑ ችግር ፍቱልን” ስንባል ወገቤን ማለት የአገልጋይ (Servant) ባለሥልጣን መገለጫ ነው?
————————–
ማስታወሻ
በቤተክርሲቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት ሲኖዶስ ቋሚ መንበር አለው። ሀገር ካልፈረሰ እና ቤተክርስቲያኒቱ ካልተሰደደች በስተቀር የሲኖዶስ ስብሰባ በመንበሩ ብቻ ነው የሚካሄደው።

ከንቲባይቱ መሰልጠን ሰው ማክበር በተለይ ለሃገር የሚፀልዩ አባቶችን ማክበርም እንደሆነ ቢረዱልን…!!!

መስከረም አበራ
ኢትዮጵያን ለመምራት ኢትዮጵያን ማከል ያስፈልጋል! አዲስ አበባን ለመምራትም ደግሞ እንደ አዲስ አበባ መሰልጠን-መሰልጠን በዲዛይነር መልበስ ብቻ አይደለም፡፡ የሰለጠነ ቱታ ለብሶም ያስታውቃል- ሰው ሲያከብር፣ሃገር ማለት የእሱ ዘውግ/ሃይማኖት ብቻ እንዳልሆነ ሲያውቅ፣መሪ ሲሆን የሚወደውን ብቻ ሳይሆን የማይወደውንም ማገልገል እንዳለበት ሲያውቅ ወዘተ፡፡
 ከንቲባ አዳነች አዲስ አበባን ለመምራት መሰልጠን እንደሚፈልግ በግማሽ ገብቷቸዋል ለዚህም ነው የመሰልጠን ምልክት የመሰሏቸውን ውጫዊ ግብዓቶች ለማሟላት የሚሟሟቱት፡፡ ይህ ጥሩ ሆኖ መሰልጠን ሰው ማክበር በተለይ ለሃገር የሚፀልዩ አባቶችን ማክበርም እንደሆነ ቢረዱ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል፡፡
Filed in: Amharic