>

ከባልደራስ መግለጫ.: *...ፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም፣ ሕዝብን ያላማከለ ድርድርም አገርን አይጠቅምም...!!!

ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ…!!!

*…ፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም፣ ሕዝብን ያላማከለ ድርድርም አገርን አይጠቅምም…!!!


ፋኖ በጭንቅ ጊዜ አገርን ከወረራ እና ከብተና የሚታደግ፣ በሠላም ጊዜ በየሙያ ዘርፉ ተሰማርቶ ሠላማዊ ኑሮውን የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዚህም መሠረት፣ ፋኖ፣ በጊዜያዊነት ተሰባስቦ በአገር ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሙሉ በሙሉ እስከሚወገድ በዱር በገደሉ እየተሰማራ፣ አካባቢውንና አገሩን ከጥቃት የሚከላከል ህዝባዊ ኃይል እንጂ፣ቋሚ የሆነ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን ብንጠቅስ እንኳን፣ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርሮ በነበረበት ጊዜ ይህ እውነታ በውል ታይቷል፡፡
ሐቁ ይህ ሆኖ እያለ፣ ለሀገሩ ሉአላዊነት የደም መስዋዕትነት ለመክፈል በከፍተኛ ወኔ ዝግጁ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረውን የዘመናችንን ፋኖ፣ “ኢ-መደበኛ አደረጃጀት” በሚል ፍረጃ ወከባና ትንኮሳ እየተፈፀመበት ይገኛል፡፡
ይህ ድርጊት ባልተቋጨው ጦርነት በየምሽጉ በተጠንቀቅ የሚገኙትን ፋኖዎች የሚነካ ብቻ ሳይሆን፣ የመከላከያ፣ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላትን አንድነት፣ ሞራልና ቅስም የሚሰብር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጫናውና ትንኮሳው ህወሓትን፣ ኦነግ/ሸኔን እና ሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ቡድኖች እና ኃይሎችን ተጠቃሚ እና ደስተኛ፣ እንዲሁም ሞራላቸውን የሚያነቃቃ ነው፡፡
ከፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ኃይል ውጭ ያሉትን ታጣቂዎች ዕጣ ፈንታ በሚመለከት፣ ከጦርነቱ በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚቀረጽ ፖሊሲ መወሰን ይገባል፡፡ እስከዚያው ድረስ፣ በፋኖ ላይ በተጠናጠል የሚፈፀሙ ትንኮሳዎች እንዲቆሙ በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡ ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መስዕዋትነት ከፍለው የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ በተጠንቀቅ የቆሙ ልጆቹን ማንም እንዲነካበት አይፈልግም፡፡
በተጨማሪም፣ በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በጎረቤት አገር ድርድር እየተካሄደ መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተገለፀ ይገኛል፡፡ ድርድሩን ከጥርጣሬ ነፃ ለማድረግ የሚከተሉትን ሰባት ምክረ-ሃሳቦች  እናቀርባለን፡-
1/ ድርድሩ ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን፣ ሂደቱንም ሊከታተል በሚችልበት አውድ እንዲደረግ፣
2/ የአፋር እና የአማራ ክልላዊ መስተዳድሮች በድርድሩ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው የሚያስችል አካሄድ እንዲኖር፣
3/ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረክ በኩል በቂ መረጃ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች፣
4/ የአገር ሽማግሌዎች ሂደቱን በታዛቢነት እንዲከታተሉ፣
5/ የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን በማህበሮቻቸው በኩል ሂደቱን በታዛቢነት እንዲከታተሉ፣
6/ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሂደቱን በታዛቢነት እንዲከታተል፣
7/ ለመገናኛ ብዙሃን በቂ መረጃ የሚደርስበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚሉት ናቸው፡፡
የአገራችን ህልውና አደጋ ላይ ወድቆ በነበረበት ጊዜ፣ መንግሥት በተደጋጋሚ የድረሱልኝ ጥሪ  አቅርቦ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ምላሽ እንደሰጠው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ አደጋው በተወሰነ ደረጃ ከተቀለበሰ በኋላ፣ መንግሥት ሕዝቡን በአገለለ መልኩ ለመጓዝ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ መጨረሻው መንግሥትንም ሆነ አገርን የሚጠቅም ባለመሆኑ፣ አስቸኳይ እርምት እንዲረግበት በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
ድል ለኢትዮጵያ!!!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
አዲስ አበባ    ኢትዮጵያ
ጥር 27/2014 ዓ.ም.
Filed in: Amharic