>

"ዴቦ....!!!" (ታምራት ነገራ)

“ዴቦ….!!!” 

ታምራት ነገራ

“…. አስመራ ነው፡፡ ቦታውን ባላውቀውም  እኔ ነገራ እና እናቴ  ዎክ እያደረግን  ነገራ “ይሄን ልጅ ለምን ዴቢሳ ስትሉ ሰየማችሁት?” ሲል ይጠይቃል ፡፡ እኔ ስም ሲወጣልኝ እሱ ጦር ሜዳ ነበር እና ስም የማውጣት ሂደቱ ላይ የእናቴ ቤተሰቦች ብቻ ነበር የተሳተፉት፡፡  እናቴም “እትዬ ነች አንተ ለጦርነት ከቤት ወጥተህ መወለዱን አይታ ወደቤትህ በሰላም እንዲመልስህ ዴቢሳ ስትል የሰየመችው” ትላለች፡፡ ዴቢሳ ማለት በኦሮሚፋ ሰፊ ትርጉም ቢኖረውም ለእኔ ሲሰጠኝ ግን ከቤት የወጣውን አባትህን በድል፤ በሽልማት፤በሰላም እንዲመጣ ጥራው እንደማለት ነው፡፡ እትዬ ማለት የእናቴ ታላቅ እህት ስትሆን እናቴም አባቴን የተዳረችው እሷው ቤት ውስጥ ነው፡፡ ትንሽ ዝም አለ እና “አኔን ግን ብትጠይቁኝ ኖሮ ታሪኩ ወይንም ታምራት ነበር የምለው” አለ፡፡ እናቴም ለምን ስትል ትጠይቃለች፡፡ “ምክንያቱም ይሄ ጦርነት አያልቅም፡፡ ተዓምረኛ እና ታሪካዊ ጦርነት ነው፡፡ ለዚህ ልጅ የማወርሰውም ነገር ቢኖረኝ ይሄንኑ ጦርነት ነው” ይላል፡፡
ይህንን በተናገረ በሦስተኛው ዓመት ማለትም 1978ዓ.ም ባረንቱ በኤርትራ ነጻ አውጭዎች ቁትጥር ስር ስትውል በውጊያ መሃል ሞተ፡፡ እኔም አባቴን ለአምስት ቀን ብቻ በቆየ ትዝታ ይዤ ቀረሑኝ፡፡ የእናቴ ቤተሰብም የእኛ ፈቃድ ሳይሆን የሙት ፈቃድ ይሁን ሲሉ ስሜን ከዴቢሳ ወደ ታምራት ቀየሩት፡፡ አባቴ ስለአለው የቤተሰብ ዝርዝር ስሜን ያስመዘገበው ታምራት ብሎ ነበር፡፡ በዚህ የስም ለውጥ ዙሪያ ግን አክስቴ ፈጽሞ ደስተኛ አልነበረችም፡፡ አንድ ቀን የስሜ ነገር ወሬ ተነሳ እና “ዴቦ እኔ እኮ አንተን ዴቢሳ ያልኩት አባትህን ብቻ አስቤ አልነበረም አንተ እና እኩዮችህ የተወለዳችሁ ሰሞን ከቤት ወጥተው የቀሩትን ሁሉ ተመለሱ ብላችሁ ትጠራላችሁ ብዬ” ነበር ስትል አጫውጣታኛለች፡፡መስፍኔ ዴቢሳ የኔ ብቻ ሳይሆን ያንተም ስም ነው፡፡ በዴቢሳም በታምራትም የትንቢት ልጅ ነኝ፡፡ የትንቢት ትውልድ ነን፡፡ የሚገርመው አክስቴ እንደተነበየችው ከቤት ወጥተው የቀሩትን ከመጥራት ይልቅ እኛው ከቤት ወጥተን ቀረነው፡፡ ይልቁኑ ነገራ እንደተነበየው የኤርትራን የማያልቅ ጦርነት ወረስን፡፡”
ታምራት ነገራ “ዴቦ” ከአስር አመት በፊት የፃፈው ነው፡፡  
የታምራትን ህሊና እና አካሉን ፍቱት !
#freetameratnegera !
Filed in: Amharic