>

ከ 31አመታት በፊት ደርግ ከህወሓት፤ ኦነግና ሻቢያ ጋር ያደረገው ድርድር ለምን ሳይሳካ ቀረ...??? (አወድ መሀመድ)

ከ 31አመታት በፊት ደርግ ከህወሓት፤ ኦነግና ሻቢያ ጋር ያደረገው ድርድር ለምን ሳይሳካ ቀረ…???

አወድ መሀመድ

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት (ኢህዲሪ)፣ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኤርትራ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ህግሓኤ) በ1983 ዓ.ም በእንግሊዝ ሀገር ድርድር ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞላቸው ነበር፡፡
ለንደን ላይ ሊካሄድ የነበረው ድርድርም ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 1983 ዓ.ም እንዲካሄድ ታስቦ ነበር፡፡
የኢህዲሪ መንግሥት ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ከሀገር ከወጡ ከሶስት ቀናት በኋላ ማለትም ግንቦት 16 ቀን ህወሃት ደሴን ተቆጣጥሮ፤ በአምቦ፣ በወሊሶና በደብረዘይት እንዲሁም በለሚ በኩል አዲስ አበባን ቀለበት ውስጥ ማስገባቱ ይነገራል፡፡
የኤርትራ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ህግሓኤ) ም በተመሳሳይ ግንቦት 16 ቀን 1983 አስመራ ከተማን ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ ህወሃት እና ህግሓኤ በዚህ መልኩ ግስጋሴ ላይ እያሉ ነበር የደርግ ባለስልጣናት ለድርድር ወደ ውጭ ያመሩት፡፡
በኢህዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ተስፋዬ ዲንቃ የተመራው የደርግ ተደራዳሪ ቡድን ዶ/ር አሻግሬ ይግለጡን፣ ቢልልኝ ማንደፍሮን፣ዶ/ር ግርማ ወልደ ስላሴን፣ ሜ/ ጄነራል መስፍን ገብረቃልንና ፍሥሃ ዘውዴን ያካተተ ነበር፡፡
ይህ ተደራዳሪ ቡድንም ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 1983 ዓ.ም ወደ ለንደን መጓዙ የሚታወስ ነው፡፡
በወቅቱ መንግስት በነበረው ኢህዲሪና ተቃዋሚ በነበሩት ህወሃት፣ ኦነግ እና ህግሓኤ መካከል ለንደን ይደረጋል ተብሎ የነበረውን ድርድር ያመቻቸችው አሜሪካ እንደነበረች የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት (ኢህዲሪ) ም/ፕሬዝዳንት ኮ/ል ፍስሃ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ላይ ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ በድርድሩ ከነበሩ ድርጅቶች አንዱ የነበረው የኦነግ ሲሆን የዚህ ግንባር የድርድር ቡድን አባል የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ ያሉት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ከለንደኑ በፊት የኢህዲሪ መንግስት፤ ከህወሃት እና ህግሓኤ ጋር በጣሊያን ሮም ድርድር አድርጎ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
ዶ/ር ዲማ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አሜሪካ ጦርነት ይቁምና መንግስትና ተቃዋሚ ኃይሎች ሰላማዊ ሽግግር ማቋቋም እንዳለባቸው አሳስባ ነበር ብለዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት፣ መንግስትና ሁሉም ተቃዋሚ ወገኖች የሽግግር መንግስት እንዲያቋቁሙ፤ የሽግግር መንግስቱ ሰላምና መረጋጋትን እንዲያሰፍን ፤ ግልጽ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ተቋማት እንዲመሰረቱ ፤ የሕገ መንግስት ማርቀቅ ስራ እንዲጀመር እንዲሁም ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ተካሂዶ የሽግግር መንግስቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመረጠው ወገን ስልጠኑን እንዲያስረክብ የሚል ሃሳብ አቅርቦ ከዚህ ውጭ ያለውን ግን እንደማይቀበል አስታውቆ ነበር፡፡
የኮ/ል መንግስቱን ከሀገር መውጣት ተከትሎ የሪፕብሊኩን ም/ፕሬዝዳንት ጄ/ል ተስፋዬ ገ/ኪዳን የፕሬዝዳንቱን ስራ ተክተው እንዲሰሩ ከመንግስት ምክር ቤት በተሰጠመግለጫ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን በወቅቱ የዋሸንግተን ባለስጣናት ከላይ የተገለጹትን ቅድመ ሁኔታ ቢያቀርቡም፤ “ህወሃት ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ ፍቀዱለት፤ ከፍተኛ ችግር ሊከሰት ይችላል፣ አዲስ አበባም እንደ ሞቃዲሾ እንዳይሆን” የሚሉ ማስፈራሪያዎችን በማንሳት ጄ/ል ተስፋዬ ገ/ኪዳንን ይወተውቱ እንደነበር፤ በወቅቱ የነበሩት የኦነግ ድርድር አባል ዶ/ር ዲማ ነገዎ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ አሜሪካኖች የኢህአዴግ ጦር አዲስ አበባ እንዲገባ በአንድ ወገን እየጠየቁ በሌላ ወገን ደግሞ በለንደን ድርድር እንዲደረግ ሲወተውቱ እንደነበርም ዶ/ር ዲማ ነገዎ ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት ድርድሩም ሳይካሄድ ኢህአደግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ከአንድ ወር በኋላ የሽግግር መንግስት አቋቁሙ የሚል ነገር እንደነበርም ተገልጿል፡፡
 በ1981ዓ.ም በህወሓት መሪነት ኢሕዴን የተሰኘ ጥምረት መመስረት
ኢሕአዴግ የተመሠረተው በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ጥምረት ግንቦት ወር 1981 ዓ.ም ነበር።
መጋቢት 17 ቀን 1982 ዓ.ም. የተመሠረተው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና በመስከረም 1985 ዓ.ም. የ”አስራ ስድስት የብሔረሰብ የፖለቲካ ድርጅቶች” ጥምረት የሆነው ደኢሕዴን ግንባሩን የተቀላቀሉት ዘግይተው ነበር፡፡
በግንቦት 1983 ዓ.ም በተካሔደ ጉባዔ 86 አባላት ያሉት እና በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያሳተፈ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ሲመሰረት ቁልፍ ሥልጣኖች በኢሕአዴግ እጅ እንደነበሩ ይታወሳል።
ድርድሩ ለምን አልተሳካም?
የአሜሪካን ጉዳይ ፈጻሚ የነበረው ሚስተር ሁዴክ በየደቂቃው ከኢትዮጵያ መንግስት አመራሮች ጋር ግንኙነት ያደርግ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን “የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አደጋ ላይ ስለሆነች ድርድሩ እስኪያልቅ ድረስ ኢሕአዲግ ገብቶ ፀጥታውን ያስከብር” የሚል ሐሳብ በመሰንራቸው ይህንንም ጄ/ል ተስፋዬ በመቀበላቸውን የኢሕአዲግ ጦር እንዲገባ መደረጉን፤ የኢህዲሪ ም/ፕሬዝዳንት ኮ/ል ፍስሃ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” በሚለው መጽሀፋቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
በወቅቱ የነበረው ድርድር ሳይሳካ ኢህአዴግ አዲስ አበባን መቆጣጠሩ የሚታወስ ሲሆን ይህ ድርድር እንዳይሳካ ያደረጉ ምክንያቶች እንዳሉ ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ ኦነግን ወክለው በድርድሩ ላይ የነበሩት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በደርግ ወደ ድርድር የገባው የኃይል ሚዛኑ ካጋደለ በኃላ መሆኑን ገልጸው ሌሎቹ ቡድኖች ግን ድርድሩን ጊዜ ለመግዛት የተጠቀሙበት እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ድርድር ሲደረግ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ግምት ውስጥ በማስገባት መሆን እንዳለበት የሚገልጹት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በወቅት የደርግ ስህተት የነበረው በመሬት ላይ ያለው እውነታ ከተቀየረ በኋላ ወደ ድርድር መግባቱ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በወቅቱ ደርግ በኩል የቀረበው መደራደሪያ በሚቋቋመው የሽግግር መንግስት ውስጥ 60 መቶ ለደርግ ፤ ቀሪው ደግሞ ለሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች ይሁን የሚል እንደነበር የገለጹት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ይህ ደግሞ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚገናኝ እንዳልነበር አንስተዋል፡፡
“በወታደራዊ ጉዳይ ብዙ ነገር ተበላሽቷል” የሚሉት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በ1981 ዓ.ም በነበረው መፈንቅለ መንግስት በኋላ ጦሩ “አልነበረም” ማለት ይቻላል ብለዋል፡፡ በመፈንቅለ መንግስቱ ጄነራሎች ሲያልቁ ጦሩ በጣም መድከሙንና ይህም ለደርግም መውደቅ ትልቁ መንስኤ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
የኢህዲሪ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮ/ል መንግስቱ ሀገር ጥለው መሄዳቸውም ጦሩ አመራር እንዳይኖረው አድርጎታል ያሉት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) አሁን ያለው ሁኔታ ያኔ ከነበረው ጋር እንደሚለያይ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ አንስተዋል፡፡
ድርድሩም ሳይሳካ ጄ/ተስፋዬ በሰጡት ትዕዛዝ ትዕዛዝ ጦሩ መሳሪያውን እያነገበ ወደ አዲስ አበባና ወደ ሌሎች ቦታዎች ጉዘውን በመቀጠል ኢሕአዴግም ግንቦት 20 በደብረዘይት፣ በአምቦና በጎጃም መንገድ በኩል አዲስ አበባ መግባቱ ይታወሳል፡፡
ኢህአዴግ አዲስ አበባ በገባበት በዛን ምሽት “ብሶት የወለደው ጀግው የኢሕአዲግ ሠራዊት ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ሲባል ፋሽስቱ ደርግ ይጠቀምበት የነበረውን ሬድዮ ጣብያ በቁጥጥር ሥር አውሎታል” የሚል ዜና ማስተላለፉ ይነገራል፡፡
የኢህዲሪ ም/ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮ/ል ፍስሃ ደስታ፣ ኮ/ል መንግስቱ በኋላ ለሰባት ቀናት ሀገሪቷን የመሩት ሌ/ጄነራል ተስፋዬ፤ የኢሕዲሪ ባለሥልጣናት አደጋ እንዳይደርስባቸው የሙውጫ በር ወይም በቅድመ ሁኔታ እጅን መስጠት ላይ ከመደራደር ይልቅ ለራሳቸው እና ለጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል አዲስ ተድላ ሲደራደሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ም/ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ተስፋዬ፤ ጦሩን አሰናብተው፤ ጓደኞቻቸው እንዳይወጡ ማገዳቸውን ይነሳል፡፡ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ከሀገሪቱ ከወጡ በኋላ ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩት የኢህዲሪ ም/ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ተስፋዬ፤ ጣልያን ኤምባሲ ስደተኛ ሆነው ከቆዩ በኋላ የኢህዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከነበሩት ብርሃኑ ባይህ ጋር ሲታገሉ ወድቀው ሕይወታቸው አልፏል።
አሁን ይደረጋል ስለሚባለው ድርድር ጉዳይ የዲማ (ዶ/ር) አስተያየት፦
የኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የፈረጀው ህወሃት ሊቀመንበር ደብረ ጺዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ መንግስት በሌሎት አካላት በኩል ከመንግስት ንግግር መጀመራቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር፡፡ ሊቀመንሩ በንግግሩ ጥሩ ነገሮች መኖራቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
 እየተወራ ያለውን የድርድር ጉዳይ በተመለከተ አል ዐይን አማርኛ ጥያቄ ያቀረበላቸው ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ህወሃትን ለ45 ዓመት ያህል እንደሚውቁትና፤ የድርድር ጠባይ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
ድርድር ሰጥቶ በመቀበልና በማቻቻል ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ህወሃት ግን በሰጥቶ መቀበል ከማመን ይልቅ “እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን” የሚል ቡድን ነው ሱሉ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ዲማ ነገዎ፤ የህወሃት ቡድን በጦርነት ይህንን መንግስት ገልብጦ ድሮ የነበረበት ቦታ ላይ መመለስ የማይችልበት ቦታ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ የትግራይ ክልል እንደማንኛውም የኢትዮጵያ አካል በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ መብቱ እንደተጠበቀ ነው የሚሉት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በምን አይነት ደረጃ እንደሚሳተፍ ግን መደራደር የሚቻል እንደሚመስላቸው ተናግረዋል፡፡
ህወሃት በሽብር መፈረጁን ተከትሎ እንደት መንግስት ከሽብርኛ ቡድን ጋር ይደራደራል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ይሄ ወደፊት ሊታይ ይችላል፤ ድርድሩ የደረሰበት ደረጃ ነው የሚወስነው፤ በሽብር ተፈርጇል፤ ግን ድርድር መጀመሩ በህወሃት በኩል ተገልጿል፤ ስለዚህ ድርድር ከተጀመረ እንግዲህ ሞዳሊቲው ምንድነው የሚሆነው እና መጨረሻ ላይ ወደ ስምምነት የሚደረስ ከሆነ ሊነሳ ይችላል” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) መንግስት ለሰላም አማራጭ ዝግጁ ቢሆንም “ከህወሃት ጋር ስለመደራደር እስካሁን ድረስ በመንግስት በኩል የተወሰደ አቋም የለም” ሲሉ በትናንትናው እለት ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
በ2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ኑሯቸው እንዲመሰቃቀል ምክንያት ሆኗል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ ከ8 ወር በኋላ የፌደራል መንግስት ጦሩን ከትግራይ ሲያስወጣ የትግራይ ኃይሎች ወደ አፋር እና አማራ ክልል በመግባት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ መጠነ ሰፊ ውድመት ማድረሳቸውን የአፋር እና የአማራ ክልል መንግስታት ገልጸዋል፡፡
መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ የህወሓት ኃይሎች ተሸንፈው ከሁለቱ ክልሎች መውጣታቸውን መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ነገርግን ህወሓት ከምስራቅ አማራ ከአፋር የወጡት ለሰላም እድል ለመስጠት ነው ሲል መግለጹ ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ የመንግስት ጦር በአማራ እና አፋር ድንበር አካባቢ ከህወሓት ኃይሎች ጋር ተፋጦ የሚገኝ ሲሆን መንግስት የህወሓት ኃይሎች ትንኮስ እያደረጉ መሆኑንና እርምጃም እየወሰደ መሆኑን ገልጿል፡፡(ከአል ዐይን)
Filed in: Amharic