ብልፅግና ሆይ ራስህን ከሰቀልክበት ጉም በጊዜ አውርድ፣ ነገ ሌላ ቀን ነውና!!
መስፍን ማሞ ተሰማ
የብልፅግና መንግሥት ሆይ! ናዚስት ህወሃትን እንደ ድርጅትና እንደ ‘ክልላዊ’ መንግሥት ከኢትዮጵያ ካንሰርነት የማስወገድ ፍላጎትህም አላማህም ስላልሆነ ናዚስቱ በከፈተብን ጦርነት ላይ ያለማሰለስ በተደጋጋሚ እንደ መንግሥት የወሰድካቸው ናዚስት ህወሃትን ከሞት የማዳን/የመታደግ ተግባራት ሲያረጋግጡ የአማራና የአፋር ህዝብን በዋናነት የናዚስቶች የዘር ፍጅት መፈፀማያ የጦር አውድማ አድርገኻቸዋል።
የቀድሞው የወያኔ ፍጡር ኢህአዴግ ህወሃትን አውጥቶ ኢህአዴጋዊ መዋቅራዊ ግንባታውንና እሳቤውን – ዘር ተኮር መንግሥትነቱን – በአደረጃጀቱ ጠብቆ ብልፅግና ሆኖ ሲከሰት (ፀረ ወያኔ ኢህአዴግ ሀይላት የለውጥ ተስፋ ብንሰንቅምና ለብልፅግና ፓርቲ አዎንታዊ ተግባራት ቀና ብንሆንምና ድጋፋችንን ብንሰጥም) በዚህ ደረጃና ጥልቀት ወያኔ ራሱ በከፈተብን ጦርነት በሰጠነው ሀገራዊ የህልውና ምላሽ ናዚስት ህወሃትን ከሞት አፋፍ በተደጋጋሚ የማዳን ስውርና ግልፅ ርብርብ መንግሥት ያደርጋል ብለን ባለመገመታችን ጦርነቱን በሙሉ ሀገራዊ ወኔና ስሜት ከውጪም ከውስጥም በምንችለው ሁሉ ስንደግፍና ስንሳተፍም (በተለይ ከውጪ በኢኮኖሚም በማቴሪያልም) ቆይተናል። የጦር ሀይሉ የበላይ ጠ/ሚር አብይ ወደ ግንባር ሲሄድ ከጎኑ ቆመናል። የአውሮፓውያንንና የአሜሪካንን ዓለም ዐቀፍ ሽብር በውጪው ዓለም ሀገራት ከተሞችና አደባባዮች ያለማሰለስ ተሰልፈን ድምፃችንን ስለ ኢትዮጵያ አሰምተናል። NO MORE ብለን በዓለም ዙሪያ የኢትዮጵያ ወዳጆችን አሰልፈን ታግለናል። የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ወጣቱ የህይወት መሥዋዕትነትን ከፍሏል የአካል ገዳተኝነትንም ወርሷል። የዚህ ሁሉ ትግል ግብ የኢትዮጵያ ካንሰር የሆነውን ህወሃት እንደ ድርጅትና እንደ ጦር ሀይል እንደ ጀርመኑ ናዚ ፓርቲና እንደ ጣሊያኑ ፋሽስት ፓርቲ ከፖለቲካ፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ሀይልም ማንኮታኮትና ወንጀለኛ መሪዎቹንም ለፍርድ ለማቅረብ ነበር። ይህ ግን በኢትዮጵያ ምድር በብልፅግና መንግሥት ህወሃት ላይ ከቶም ዕውን እንደማይሆን የተረዳነው ከዘገየ ነው። የብልፅግና መንግሥት ናዚስት ወያኔ በአማራውና በአፋሩ ህዝባችን ላይ የሚያካሂደውን የዘር ፍጅት፣ የማፈናቀል፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ ወይ ከዳር ቆሞ ይመለከታል፣ ወይ እንደ ገላጋይ መኻል ገብቶ “በየቦታችሁ” ቁሙ ይላል። ይህ አዙሪታዊ የብልፅግና ዥዋዥዌ ትላንት ነበር ነገም ተመልሶ ይከሰታል።
በግልፅና በተደጋጋሚ እንዳየነው ብልፅግና ናዚስት ህወሃትን (ወያኔን) እንደ ድርጅትና እንደ ፖለቲካዊ ተቋም ከነኢኮኖሚያዊ ጡንቻው (ለምሳሌ ኤፈርት) ጭምር ከኢትዮጵያ የፖለቲካና መንግሥታዊ ማዕቀፍ/ምህዳር የማስወገድ ፍላጎት ከቶም የለውም። ይህ ዕውነታ በተግባርም በመታየት ላይ ነው።
ከናዚስት ወያኔ ጋር እንደ ሀገር በተለይ ደግሞ በአማራና በአፋር ክልሎች የገባንበትን የህልውና ጦርነት ቢያንስ በአማራውና በአፋሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ማባሪያ ያጣ የዘር ፍጅትና ምድራዊ ሠቆቃ የንብረት ውድመትና የአርሶ አደሩና የከተሜው መፈናቀል (በወለጋ ምድር በንፁሀን ኢትዮጵያውያን ላይ በማንነት ተኮር ዘረኝነት በኦነግ የሚፈፀመውን ፋሽስታዊ ፍጅትንም ልብ ይሏል) ማቆም የምንችለው እንዴት ነው?!
የብልፅግና መንግሥት ሆይ፤ አንተ ብቻ ስለ ኢትዮጵያ ትንሳዔ የምታውቀው ወይም የተገለጠልህና ለእኛ ግን የተሰወረብን ምሥጢር ምንድን ነው?! ስለምን ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ የዛሬና የነገውን ህልውናዋን ሠላሟንና ዕድገቷን አስመልክቶ እንደ ዜጋ የያገባናል መብታችንን እና በጎ ተስፋችንን እንድናሟጥጥና በተስፋ መቁረጥ ፊታችንን እና የዜግነት ግዴታችንን ለአንተ ጥለን እንድንገለል ግልፅና ረቂቅ ደባ ታካሂዳለህ?! ብልፅግና ሆይ፤ ነገ ሌላ ቀን ነው። ህዝብን ስማ!! ህዝብ አንተን ብቻ እንዲሰማ ይቻለው ዘንድ እንደማይቻለው ራስህ የመጣህበት የሥልጣን መሰላል እንደምን ትምህርት ሊሆንህ አልቻለም?! ብልፅግና ሆይ ፀሀይና ንፋስ መኖራቸውን አትርሳና ራስህን ከሰቀልክበት ጉም በጊዜ አውርድ !!!! ነገ ሌላ ቀን ነውና . . . !!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !!!