>
5:13 pm - Monday April 19, 1976

ባልደራስ ያቀረበውን የጅምላ ፍጅት ሰነድ የተባበሩት መንግሥታት ለመመርመር ቃል ገባ!

ባልደራስ ያቀረበውን የጅምላ ፍጅት ሰነድ የተባበሩት መንግሥታት ለመመርመር ቃል ገባ!

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) በጅምላ ስለተጨፈጨፉ፣ ዛሬም በወለጋ እና በምዕራብ ሸዋ በጅምላ ጨፍጫፊዎች ተከበው ስለሚገኙ  አማሮች ለተባበሩት መንግሥታት፣ ዛሬ፣ አርብ፣ የካቲት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ማብራሪያ ሰጥቷል። የተባበሩት መንግሥታት የዘር ጭፍጨፋዎችን (Genocide) ለመከላከል በገባው ቃል መሠረትም እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል። የዘር ጭፍጨፋዎቹን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችንም በተንቀሳቃሽ ምስልና ድምፅ (Vedio)  አቅርቧል።
የፓርቲው ፕሬዚደንት እስክንድር ነጋ፣ የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል እና የባልደራስ የውጭ ጉዳይ ሓላፊው ዶክተር ሰሎሞን ተሰማ፣  ማስረጃውን ይዘው አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት  ቅጥር ግቢ ተገኝተው ጉዳዩን አብራርተዋል።
በዚህም መሠረት፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ምክትል ሓላፊ እና የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ባለሙያዎችን አነጋግረዋል።
በውይይታቸው፣ በአሁኑ ወቅት በወለጋና ምዕራብ ሸዋ በአማራነታቸው ብቻ ተፈርጀው በጅምላ ጨፍጫፊዎች ተከበው ስለሚገኙት 60 ሺህ አማሮች በአፅንኦት ተነጋግረዋል። ተከበው ከሚገኙ አማሮች መካከል፣ በምስራቅ ወለጋ የሚገኙ አንድ ሰው የባልደራስ አመራሮችና የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎችን በስልክ አነጋግረዋል። እኒህ ሰው በሲቦሲሬ ወረዳ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ አማሮች ታግተው እንደሚገኙ አረጋግጠዋል። ትናንት ከቀኑ በ10 ሰዓት ገደማ ቦምብ ተወርውሮ ሰዎች መቁሰላቸውንና መገደላቸውምን አረጋግጠዋል።
እንደ ሰውየው ማብራሪያ፣ አማሮች እንዲጨፈጨፉ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹና በጭፍጨፋው በቀጥታ የሚሳተፉ የኦሮሚያ መስተዳድራዊ መንግሥት የሥራ ሓላፊዎች አሉ።     “አሁን መንግሥት ወዳለበት (አዲስ አበባ ማለታቸው ነው) ነው መሄድ የምንፈልገው።  እንዳንወጣ ግን ሁላችንም ታግተናል። ለማምለጥ የሚሞክር በሞት ነው የሚቀጣው። ከአካባቢው የሚነሱ መኪኖች እየተፈተሹ፣ ዐማራ ከተገኘ በቀጥታ ይገደላል። መታወቂያ እያዩ አማራነታችንን ያረጋግጣሉ። ያለነው ሜዳ ላይ ነው። የሚበላ የለንም፣ መጠለያ የለንም፣ የምንለብሰው የለንም። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን፣ እርዳታ እንዳይደርሰን ተከልክሏል። የተባበሩት መንግሥታትም እንዳይመጣ ተከልክሏል። መንገዱን ዘግተው አላስገባ ስላሉ ሊደርሱልን አልቻሉም። ዛሬ ነገ እንጨፈጨፋለን ብለን ስጋት ላይ ነን” ብለዋል በስልክ ያነጋገሯቸው ተፈናቃይ።
የተባበሩት መንግሥታት በኦሮሚያ መስተዳድር የዘር ፍጅት አደጋ መከሰቱን ተቀብሎ፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር አባላትና በኦነግ/ሸኔ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚደንት እስክንድር ነጋ ጠይቀዋል።
 የፓርቲው ልዑክ ቡድን ከኦሮሚያ መስተዳድር፣ በተለይም ከወለጋና ምዕራብ ሸዋ ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን፤ ጠባሴ ‘ቻይና ካምፕ’ ተብሎ በሚጠራ መጠለያ  የሚገኙ አማሮችን በጎበኘበት ወቅት፣ ከራሳቸው ከተፈናቃዮች የሰሙትንና ያዩትን ለመንግሥታቱ ድርጅት አብራርተዋል።  ተፈናቃዮች ደብረ ብርሃን ከመሄዳቸው በፊት፣ የተሻለ ትኩረት በሚያገኙባት ዓለም አቀፋዊዋ ከተማ አዲስ አበባ መቆየት ቢፈልጉም ተደብድበው እንደተባረሩ አስረድተዋል።
ከጅምላ ጭፍጨፋ ከተረፉ አማሮች  መካከል፣ ማጅራታቸው ታርዶ ነፍሳቸው የተረፈ እና እጃቸው የተቆረጠ ይገኙበታል። በጅምላ ከተገደሉት መካከል ደግሞ፣ ጡታቸው የተቆረጠ ሴቶች እና ብልታቸው የተቆረጠ ወንዶች እንደሚገኙበት የዐይን ምስክሮች ተናግረዋል። ይህ ምስክርነት ለመንግሥታቱ ድርጅት በቀረበው ማስረጃ ውስጥም ተካቷል።
በመጨረሻም፣ ባልደራስና የተባበሩት መንግሥታት በኦሮሚያ ያለውን የዘር ፍጅት በጋራ ክትትል ስለሚያደርጉበትና ስለሚመረምሩበት ሁኔታ ተነጋግረዋል።
Filed in: Amharic